የዝንጀሮ ፈንጣጣ፡ የዝንጀሮ ፈንጣጣን በሚመለከት የሚነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎችና መልሳቸው

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library
በኮቪድ ወረርሽኝ፣ በድርቅ እና በጦርነት እየተፈተነች ያለችው ዓለም አሁን ደግሞ የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ሞንኪፖክስ) ሌላ ስጋት ሆኖባታል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ከ50 ዓመታት በኋላ ከአፍሪካ ውጪ የተከሰተ ወረርሽኝ ነው ተብሏል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ወረርሽኙ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ በርካታ የአውሮፓ አገራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አረጋግጠዋል።
እስካሁን ቫይረሱ ከተገኘባቸው አገራት መካከል ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድስ፣ ጣሊያን፣ ኦስትሪያ፣ ስዊትዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ካናዳ፣ አሜሪካ እና አውስትራሊያ ይገኙበታል።
እሁድ ዕለት የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ 92 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 28 ሰዎች በቫይረሱ ተጠርጥረዋል።
የተለያዩ አገራትም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን እያሳወቁ ነው።
አንዳንድ አገራትም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ለሦስት ሳምንት እንዲያገሉ መክረዋል። ከእነዚህ አገራት መካከል ቤልጂየምና ዩኬ ይጠቀሳሉ።
የጤና ባለሥልጣናት ቫይረሱ በቀላሉ የመሰራጨት ዕድሉ ዝቅተኛ ነው ያሉ ሲሆን፣ የበሽታው ምልክቶችም የከፉ እንዳልሆኑ እየገለጹ ነው።
ይሁን እንጂ ቫይረሱን በተመለከተ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ግርታን ፈጥረዋል። ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከል የተወሰኑትን እናንሳ።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ አሁን ለምን ተከሰተ?
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ አይተላለፍም። አሁን ላይ በቫይረሱ የተያዙ በርካታ ሰዎች መገኘታቸው በምን ምክንያት እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።
ይሁን እንጂ ቫይረሱ በዚህ ወቅት ለመከሰቱ ሦስት መላ ምቶች ተሰጥተዋል።
አንደኛው ቫይረሱ የተለየ ዝርያ ነው የሚል ነው። ተመራማሪዎች የዝንጀሮ ፈንጣጣ በቀላሉ እንዲተላለፍ የሚያስችል የመለወጥ ሂደት እንዳለው ዝርያውን እያጠኑ ነው፤ ነገር ግን እስካሁን ቫይረሱ ራሱን ለውጦ ስለመሆኑ የሚያሳይ መረጃ አልተገኝም።
ሌላኛው ደካማ ተፈጥሯዊ የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። በመላው ዓለም የስሞልፖክስን (ፈንጣጣ) በሽታ ለማጥፋት ስሞልፖክስ ክትባት ጥቅም ላይ ውሏል።
ክትባቱ የዝንጀሮ ፈንጣጣንም (ሞንኪፖክስን) ይከላከላል። ነገር ግን በወቅቱ ከ50 ዓመት በታች ያለ ሰው በሽታው አጋጥሞታል። ስለዚህ አሁን እኛ ይበልጥ ተጋላጭ ነን ማለት ነው? ሲሉም የሚጠይቁ አሉ።
የመጨረሻውና ሦስተኛው መላምት ቫይረሱ በአጋጣሚ ወይም በዕድል የተከሰተ ሊሆን ይችላል የሚል ነው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ እንዴት ይተላለፋል?
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ከሌሎች የተወሰኑ ተላላፊ በሽታዎች ጋር ሲነጻጻር በቀላሉ የሚተላለፍ አይደለም። በአብዛኛው በሽታው የሚተላለፈው በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ለረዘመ ጊዜ አካላዊ ንክኪ ሲኖር ነው።
በዋናነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በሳል እና በንጥሻ እንዲሁም ሰውነት ላይ በሚወጣ ሽፍታ አማካይነት ነው።
ቫይረሱ በዓይን፣ በአፍንጫ ወይም በአፍ አሊያም ቆዳ የተሰነጠቀ ከሆነ በዚያ ሊገባ ይችላል።
በበሽታው የተያዘ ሰው የተጠቀመባቸው አልባሳትን መጋራት ለበሽታው ያጋልጣል።
በበሽታው የተያዘ ሰው በቫይረሱ ስለመያዙ ወዲያው ላያውቅ ይችላል። ምክንያቱም ምልክቶቹ ለመታየት አንድ ወይም ሁለት ሳምንት ሊወስድ ይችላል።
በተለያየ ጊዜ ወረርሽኙ በሚከሰትበት በምዕራብና ማዕከላዊ አፍሪካ በአብዛኛው በሽታው የሚዛመተው በአይጦች አማካኝነት ነው።
ቫይረሱም በእንስሳቱ ንክሻ፣ በደንብ ያልበሰለ በቫይረሱ የተያዘን የእንስሳ ሥጋ በመመገብ ይተላለፋል።

የፎቶው ባለመብት, UKSA
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ይተላለፋል?
በበሽታው የተያዘ ሰው የተገኘባት የመጀመሪያ አገር ዩኬ፣ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ይገኙበታል። ይህም ቫይረሱ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ይተላልፍ ይሆን የሚል ጥያቄን አጭሯል።
የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች እንደሚሉት የዝንጀሮ ፈንጣጣ የአባላዘር በሽታ አይደለም። ይሁን እንጂ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት በሚኖር አካላዊ ቅርበትና ንክኪ ጉንፋን ሊይዝ እንደሚችለው ሁሉ የዝንጀሮ ፈንጣጣም ሊተላለፍ ይችላል።
ይህ ማለት ግን የዝንጀሮ ፈንጣጣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ይተላለፋል ማለት እንዳልሆነ የድርጅቱ ባለሙያ ኤንዲ ሴል አስረድተዋል።
ኤንዲ እንደሚሉት የአባላዘር በሽታዎች በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ሲሆን የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለማስተላለፍ ግን የግድ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ አይጠበቅም። አካላዊ ንክኪ በቂ ነው።
ታዲያ ለተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች በተለየ ለምን ስጋት ሆነ?
በዩናይትድ ኪንግደም ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ይገኙበታል። ይህም የዩኬ ጤና ደኅንነት ተቋምን ከወንድ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ወንዶች በሰውነታቸው ላይ ስለሚያጋጥማቸው ያልተለመደ ሽፍታ ወይም ቁስለት ልብ እንዲሉ እንዲያሳስብ ምክንያት ሆኗል።
የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያው ኤንዲ ሴል እንደሚሉት ቀደም ብሎም እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች በግብረ ሥጋ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ጋር በተያያዘ የጤና ምርመራ የማድረግ ልማድ አላቸው።
በመሆኑም እነዚህ ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ወንዶች በሰውነታቸው ላይ ያልተለመደ የበሽታ ምልክት ሲያዩ ቶሎ ወደ ሕክምና ተቋም መሄዳቸው በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ እነርሱ ለመሆናቸው አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ መገለልን ያስከትል ይሆን?
የዓለም ጤና ድርጅት በበሽታው ዙሪያ ባካሄደው ጉባኤ አንድ ግለሰብ ድርጊት ዓለም ለበሽታው የሚሰጠው ምላሽ መገለል ሊያስከትል እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።
በድርጅቱ የኤችአይቪ፣ ሄፒታይተስ እና የአባላዘር በሽታዎች አማካሪ የሆኑት ኤንዲ ሴል፣ አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ጥሩ መረጃ እየሰጡ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግን እንዲህ ዓይነት ክስተት ሲያጋጥም የተሳሳቱ መረጃዎችን፣ መገለልና መድሎን ያስከትላል ብለዋል።
"ይህ ሊያጋጥም የሚችለው ወንድ ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ላይ ብቻ ሳይሆን ምን አልባት በሚሰሩ ዘገባዎች ላይ የጥቁሮችን ቆዳ የሚያሳዩ ምስሎችን ብቻ መጠቀም የአፍሪካ በሽታ ተደርጎ እንዲታሰብ ሊያደርግ ይችላል" ሲሉም ምሳሌ ሰጥተዋል።
በመሆኑም ድርጅቱ ከዚህ በፊት ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ አጋጥሞ ከነበረው መገለልና መድልዎን የመዋጋት የዘመናት ልምድ ትምህርት መውሰድ እንደሚፈልግ ኤንዲ አክለዋል።
አማካሪው አክለውም ከዝንጀሮ ፈንጣጣ ጋር በተያያዘ ማኅበረሰቦች ትክክለኛ መረጃዎችን እየተለዋወጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ቫይረሱን በቀላሉ መቆጣጠር ይቻላል?
የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሌሎች ሰዎች ሊገኙ ስለሚችሉ አገራት መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ይህ ማለት ግን ሥርጭቱ አስከፊ እየሆነ ነው ማለት አይደለም ወይም ደግሞ በሽታው ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል ማለት አይደለም። የጤና ባለሥልጣናት የበሽታውን ሥርጭት መቆጣጠር እንደሚቻል እምነት አላቸው።
ምክንያቱም ምንም እንኳን የታየው ወረርሽኝ ያልተለመደ ቢሆንም ልክ እንደ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው አይተላለፍም።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ከሰው ወደ ሰው ለመተላለፍ የቅርብ ንክኪ ሊኖር ይገባል። ብዙ ጊዜ የሚተላለፈውም በቆዳ ንክኪ ነው።
ከዚህም ባሻገር እንደ ኮቪድ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ምልክት ላይኖራቸው አይችልም። በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች ህመም ይሰማቸዋል፤ በሰውነታቸው ላይም ሽፍታን ያያሉ።
የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለመቆጣጠር እና ለማከም የሚውሉ መድኃኒቶችና ክትባቶች አሉ።
ከሞንኪፖክስ ጋር ተመሳሳይ ዝርያ ላለው እና ከዚህ ቀደም ተከስቶ ለነበረው ስሞልፖክስ ቫይረስ የተሰራው ክትባት 85 በመቶ በሽታውን የመከላከል አቅም አለው።
"ሌላኛው ኮቪድ-19 አይደለም። ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር የሚያመሳስላቸው የሕብረተሰብ ትኩረት በመሳባቸው ነው" ብለዋል ባለሙያዎች።
ቢሆንም ግን ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ ውጪ በስፋት የተከሰተ ወረርሽኝ ነው።














