ሄዝቦላህ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መኖሪያ ቤት ላይ የድሮን ጥቃት ተፈጸመ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁን የግል መኖሪያ ቤትን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት በሊባኖሱ ቡድን ሄዝቦላህ መፈጸሙን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ሲዛሪያ በተባለችው በሰሜናዊ እስራኤል በምትገኘው የወደብ ከተማ ውስጥ ያለው የኔታኒያሁ የግል መኖሪያ ቤት ላይ የተሰነዘረው የድሮን ጥቃት ይፋ የሆነው የእስራኤል ጦር ከሊባኖስ ሦስት ድሮኖች መወንጨፋቸውን ካሳወቀ በኋላ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የድሮን ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ “ኔታኒያሁም ሆኑ ባለቤታቸው በስፍራው አልነበሩም፤ እንዲሁም በጥቃቱ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም” ብሏል።
ኔታኒያሁ በግል መኖሪያ ቤታቸው ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ እያካሄዱ ካሉት የጦርነት ዓላማ ምንም ነገር እንደማያስቆማቸው በመጥቀስ “በእስራኤል ዜጎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚሞከር የትኛውም ወገን ከባድ ዋጋ ይከፍላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “የኢራን ቅጥረኛ የሆነው ሄዝቦላህ እኔን እና ባለቤቴን ለመግደል ያደረገው ሙከራ ከባድ ስህተት ነበር” ብለዋል።
የኢራን መንግሥት የዜና አገልግሎት የሆነው ኢርና የድሮን ጥቃቱ በሄዝቦላህ የተፈጸመ መሆኑን ገልጿል።
በተባበሩት መንግሥታት የኢራን ተልዕኮ “እያነጋገረ ያለው እርምጃ የተወሰደው ሊባኖስ በሚገኘው ሄዝቦላህ ነው” ማለቱም ተጠቅሷል።
ከሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኘው የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል እንዳለው ቅዳሜ ዕለት በተፈጸመው የድሮኖች ጥቃት አንዱ በሲዛሪያ ከተማ የሚገኝ አንድ ሕንጻን መትቷል።
ነገር ግን የእስራኤል መንግሥት በድሮን የተመታው ሕንጻ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖሪያ ቤት አካል ስለመሆኑም ሆነ፣ በጥቃቱ ስለደረሰው የጉዳት መጠን ያለው ነገር የለም።
የአሜሪካው የበይነ መረብ ዜና ምንጭ የሆነው አክሲዮስ እንደዘገበው በሄዝቦላህ የተፈጸመው የድሮን ጥቃት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቤት መትቷል።
ቅዳሜ ጠዋት ላይ “ሦስት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ከሊባኖስ ተነስተው ወደ አገሪቱ ገብተዋል። ከመካከላቸው ሁለቱ ድሮኖች እንዲከሽፉ ሲደረግ፣ አንደኛው ሕንጻ ቢመታም በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም” ብሏል የእስራኤል ጦር።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ አሁን ጥቃት በተፈጸመባት ሲዛሪያ እና ኢየሩሳሌም ከተሞች ሁለት የግል መኖሪያ ቤት አሏቸው። በተጨማሪም በአሁኑ ጉዜ በእድሳት ላይ በሚገኘው አጊዮን በሚባለው ኢየሩሳሌም በሚገኘው መንግሥታዊ ቤታቸው ውስጥ ይኖራሉ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል እንዳስታወቀው ቅዳሜ ዕለት እስከ 200 የሚደርሱ ሮኬቶች በሄዝቦላህ ከሊባኖስ ወደ እስራኤል ተተኩሰዋል።
እስራኤልም በበኩሏ በኢራን ከሚደገፈው ሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን የቀጠለች ሲሆን፣ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣንት አስታውቀዋል።
በኔታኒያሁ ቤት ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙ ከተገለጸ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ምንም ዓይነት ነገር እርሳቸውን እና አገራቸውን በሐማስ ላይ “እስከ ድል ድረስ” የሚያካሂዱትን ዘመቻ እንዳማያስቆመው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚደያ ባሠራጩት ቪዲዮ “ዋነኛው ነፍሰ ገዳይ የሆነውን ያህያ ሲንዋርን አስወግደነዋል” በማለት፤ “የምናካሂደው የትንሳኤ ጦርነት እስከ መጨረሻው የሚቀጥል ነው” ሲሉ አክለዋል።
የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር መገደልን ተከትሎ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ እስራኤልን ለመበቀል አዲስ እና ከባድ ጥቃት እንሚፈጽም አሳውቆ የነበረ ሲሆን፣ ቡድኑ ስለጥቃቱ ያለው ነገር ባይኖርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖሪያ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት የዚሁ አካል ሊሆን ይችላል ተብሏል።















