ስቶክሆልም ሲንድረም፡ ታጋች ከአጋች ጋር መቀራረብ እና ከአጋች ጋር የመደራደር ጥበብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አወዛጋቢውን ‘ስቶኮልም ሲንድሮም’ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የጀመረው ልክ የዛሬ 51 ዓመት ለቀናት የዘለቀ ባንክ ቤት ውስጥ የተፈጸመ እገታን ተከትሎ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1973 አራት የባንክ ሠራተኞች ለስድስት ቀናት ሲታገቱ ከመካከላቸው አንዷ የ23 ዓመቷ ክሪስቲና ኤንማርክ ትገኝበታለች።
በሁለተኛው የአገታ ቀን ከዘራፊዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ያን-ኤሪክ ኦልሰን ለፖሊስ አንድ ጠንካራ መልክ ለማስተላለፍ አስቦ የክርስቲና የሥራ ባልደረባ የሆነውን ሳቬን ሳፍስትሮምን በጥይት ለመምታት መዘጋጀት ጀመረ።
ክርስቲና ኤንማርክ ከክስተቱ ከረዥም ዓመታት በኋላ እአአ 2016 ላይ ለቢቢሲ ስትናገር፤ አጋቹ ያን የሥራ ባልደረባዬን “በጥይት ስመታህ እግር ውስጥ ያለውን አጥንት አልጎዳም። በጥይት የምመታህ እግርህ ላይ ከባድ ጉዳት ያማያስከትል ቦታ ነው” ብሎ መናገሩን ታስታውሳለች።
“በዚያን ወቅት እንዴት እንደሆነ ባላውቅም የሥራ ባልደረባዬ እግሩን እንዲመታ ባለመፈቀዱ እንደ ፈሪ አድርጌ ነበር የተመለከትኩት። ይህን እንዴት እንዳሰብኩ አላውቅም። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መግባት የሚፈጥረው ጫና ከባድ እንደሆነ ብረዳም እንደዚያ ማሰቤ በጣም ያሳርረኛል” ብላ ነበር።
የባንክ ሠራተኛው ሳቬን ሳፍስትሮም በዕለቱ በጥይት አልተመታም። ሳፍስትሮም ሽጉጥ የመዘዙበትን አጋቾቹን ጉዳት ሊያደርሱበት የመጡ ሰዎች አድርጎ ሳይሆን ጓደኛው እንደሆኑ አድርጎ አስቦ ነበር።
ይህን ክስተት ተከትሎ ስቶክሆልም ሲንድረም የተባለ ጽንሰ ሐሳብ ተወለደ። ስቶክሆልም ሲንድረም ታጋች ለአጋቹ አንዳች ዓይነት የፍቅር ወይም ሐዘኔታ ሲያዳብር የሚከሰት ነው።
የሥነ አእምሮ ባለሙያ ኒል በሄሮት “ታጋቾች ለአጋቾቻቸው ምክያታዊ ያለሆነ አዎንታዊ ስሜት ሲያዳብሩ የሚከሰት ነው” ይላሉ።
ይህ ጽንሰ ሐሳብን የሚያጠናክር ሌላ ክስተት በአሜሪካ አጋጠመ።
ፓቲ ሄራስት የተባለች የካሊፎርኒያ ባለጸጎች የ19 ዓመት ሴት ልጅ ታገተች። ፓቲ ግን ለአጋቾቿ ምክንያታዊ የልሆነ ርህራሄ በማዳበር አብራቸው በዘረፋ እስከመሳተፍ ደርሳ ነበር።
በመጨረሻም ታዳጊዋ በቁጥጥር ሥር ውላ ለፈጸመችው የወንጀል ተግባር የእስር ቅጣት ተላልፎባት ነበር።
ጠበቆቿ ግን ወጣቷ አስተሳሰቧን እንድትቀይር መደረጓን እና በስቶክሆልም ሲንድረም እንደተጠቃች ተከራክረዋል።
ከአጋቾች ጋር የሚደረግ የድርድር ጥበብ ተግባራዊ በማድረግ ቀዳሚ ናቸው ከሚባሉት መካከል የኒው ዮርክ ፖሊስ አባል የሆኑት ፍራንክ ቦልዝ እና ጋርቪይ ስችሎስበርግ ይገኙበታል።
ከአጋች ጋር ድርድር የማድረግ ሐሳብ የመጣው እአአ 1972 በሚዩኒክ ኦሊምፒክ ላይ 11 የእስራኤል አትሌቶች በፍልስጤም የሚሊሻ ቡድን ታግተው ከተገደሉ በኋላ ነው።
በ1980 ሁለቱ የኒው ዮርክ ፖሊስ አባላት መሰል እገታ በከተማው እንዳይከሰት በማሰብ እና በእገታ ወቅት ጦር መሳሪያ ይዞ ታጋቾችን ለማስቀቅ በሚደረግ ጥረት ውጥረት እንዳያያል ማድረግ ዓላማ ያደረገ ነው።
የሥነ-አእምሮ ባለሙያ እና የፖሊስ አባል የሆኑት ስችሎስበርግ ስቶክሆልም ሲንድረሰም ማለት በቀላል ቋንቋ “ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ወደ አንድ መጥተው ግንኙነት ሲመሠርቱ የሚከሰት ነው” ይላሉ።
“ሁኔታው ውጥረት የበዛበት ስለሆነ ወዳጅነቱ በፍጥነት ይመሠረታል። ሰዎች ቀውስ ውስጥ ሲገቡ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አያውቁም። አንድ ሁላችንም የምንፈራው ነገር እራሳችንን መቆጣጠር ተስኖን አእምሯችንን መሳት ነው” ይላሉ።
ቦልዝ ደግሞ አጋቾች የሚጠይቁትን ነገር በፍጥነት ማግኘት እንደማይችሉ መናገር ስህተት ነው ይላሉ። “በምንም ተዓምር አይሆንም ማለት የለብንም። በተመሳሳይም ጥያቄው ተፈጻሚ ይሆናል ብለን መናገር የለብንም። ሁሌም ማለት ያለብን ‘ምን ላደርግልህ እንደምችል ላሰብ’ የሚል ነው መሆን ያለበት።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በስዊድን መዲና በሚገኘው ባንክ ላይ እገታ ሲፈጸም ግን የስቶክሆልም ፖሊስ ይህ መረጃ አልነበረውም ነበር። በዚህም ምክንያት ዛሬ ላይ ሊፈጸሙ የማይችሉ ብዙ ስህተቶች ተፈጥረዋል።
ኦለሰን የተባለው አጋች ወደ ባንክ በኃይል ገብቶ ሠራተኞችን ካገተ በኋላ 3 ሚሊዮን የስዊድን ክሮነር፣ ከአካባቢው የሚያመልጥበት መኪና እና በእስር ቤት የሚገኝ ጓደኛው ተለቆ ወደ እርሱ እንዲመጣ ጠይቆ ነበር።
አጋቹ የጠየቀውን ገንዘብ እና መኪና ባይሰጠውም፤ በእስር ቤት የነበረው ተዋቂ ወንጀለኛ ወደ ባንኩ ተልኮ ነበር።
ወንጀለኛው ወደ ባንኩ ቅርንጫ የተላከው የአጋቹን ፍላጎት ለማሟላት ሳይሆን ወንጀለኛው ከፖሊስ ጋር ተባብሮ የእስር ጊዜው እንዲቀነስለት ከስምምነት በመድረሱ ነበር።
ይሁን እንጂ ሁለት አጋቾች እና አራት ታጋቾች በስድስት ቀናት ቆይታቸው አንዳቸው ለሌላኛው ርህራሄ አዳበሩ።
አጋቾች ለታጋቾች ትሁት እና ሩህሩህ ሆኑ። ታጋቾች ደግሞ የፖሊስ ኃይልን መፍራት ጀመሩ። ፖሊስ ነጻ ሊያወጣቸው በሚያደርገው ጥረት ሊገደሉ እንደሚችሉ ጠንካራ እምነት አዳበሩ።
ታጋቿ ክሪስቲን ኤንማርክ በአጋቿ ኦሎፍሰን ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በስልክ እንድታወራ ጫና ተደረገባት።
ክርስቲን ከአጋቾቹ ጋር ከአካባቢው በመኪና እንዲያመልጡ እንዲፈቀድላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተማጸነች።
“እርስዎ በቢሮዎ ተቀመጠው በሕይወታችን ላይ ዳማ የሚጫወቱ ይመስለኛል። አጋቾቹን አምናቸዋለን። ምንም አላደረጉንም። በአንጻሩ ለእኛ በጣም ጥሩ ናቸው። እኔ እየፈራሁ ያለሁት ፖሊሶች ጥቃት ከፍተው ልንገደል እንችላለን የሚለው ነው” ስትል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግራ ነበር።
ከረዥም ዓመታት በኋላ እአአ 2016 ላይ ክርስቲን ኤንማርክ ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ፤ “ያ የስልክ ንግግር ባልኖረ ኖሮ ብዬ እመኛለሁ። ምክንያቱም ትርጉም የሌለው ንግግር ነው” ብላለች።
ለበርካታ ቀናት ታጋቾች በባንኩ ግዙፍ ካዝና ውስጥ በኃይል በታጠቁ ፖሊስ ተከበው ቆዩ።
በመጨረሻ ፖሊስ ጣራውን ቀዶ በመግባት አጋቾችን ትጥቅ ለማስጣል አስለቀሽ ጭስ ተኮሱ።
ፖሊስ በቅድሚያ ታጋቾች እንዲወጡ በድምጽ ማጉያዎች መልዕክት አስተላለፈ። ታጋቾች ግን እነርሱ ቀድመው የሚወጡ ከሆነ አጋቾቻቸው በጥይት ተመትተው ሊገደሉ ይችላሉ በሚል ጥለናቸው አንወጣም አሉ።
ከዚያም አጋቾች ቀድመው ከወጡ በኋላ በባንኩ መተላለፊያ ኮሪዶር ላይ ከታጋቾች ለስንብት ሲተቃቀፉ ታዩ።
ይህም በባንኩ የተከሰተውን የአጋች ታጋች ድራማ ጉዳይ በአንክሮ ሲከታተል የነበረን የስዊድን ሕዝብ ጉድ አሰኘ።
ከዚህ ክስተት በኋላ ክርስቲን በአጋቹ ጥያቄ ከእስር ቤት ውጥቶ ከነበረው የአጋች ተባባሪ ከነበረው ኦሎፍሰን ጋር ጓደኝነት መመሥረቷን ተናግራለች።
ክርስቲን ስቶክሆልም ሲንደረም ከሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ጋር ፈጽሞ አትስማማም። “ይህ ተራ ሃሐብ ነው። ይህ ተጎጂን መልሶ ተጠያቂ ለማድረግ የሚቀርብ ማሳሳቻ ነው። እኔ ሕይወቴን ለማዳን ያደረኩትን አድርጊያለሁ” ብላለች።












