የሰላሌ ሕዝብ ልጆቹን ቀንበር አሸክሞ ‘የክብር’ ዕቃዎች ይዞ ለምን አደባባይ ወጣ?

ልጆቻቸውን ቀንበር አሸክመው አደባባይ የወጡት የሰላሌ ነዋሪዎች
የምስሉ መግለጫ, ልጆቻቸውን ቀንበር አሸክመው አደባባይ የወጡት የሰላሌ ነዋሪዎች

በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ባለፉት ሦስት ሳምንታት ልጆቻቸውን ቀንበር አሸክመው እና በማኅብረሰቡ ክብር ያላቸውን ዕቃዎች ይዞ ባልተለመደ ሁኔታ አደባባይ ወጥቷል።

ከዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ ነዋሪዎች አደባባይ የወጡት ከአቅማቸው በላይ ለሆነ ችግሮች ፈጣሪ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ለመማጸን መሆኑን በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ተሳታፊ የነበሩ እና ያስተባበሩ ሰዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ ለዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ቅርብ የሆነው እና በግብርና እንዲሁም በወተት ምርቱ ይታወቅ የነበረው አካባቢ ሰላም ርቆት ነዋሪዎች በሰላም ወጥተው መግባት፣ አርሶ መሰብሰብ፣ መገበያየት እና ልጆቻቸውን ትምህር ቤት መላክ ካቃታቸው ዓመታት ማለፋቸውን ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ ምክንያትም ላለፉት ሁለት ተከታታይ የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በአካባቢው ባሕል መሠረት ነዋሪዎች “ማለቂያ የሌለው ሰቆቃ” እንዲያበቃ ልጆቻቸው እና በሬዎቻቸው ላይ ሞፈር ጠምደው እንዲሁም የክብር የሆኑ መገልገያዎቻቸውን ይዘው በመውጣት ፈጣሪያቸውን ተማጽነዋል።

በዞኑ የሚገኙት ኩዩ፣ ደገም፣ ሂዳቡ አቦቴ፣ ወረ ጃርሶ፣ ግራር ጃርሶ፣ ደራ እና ያያ ጉለሌ ወረዳዎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ከሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ተጠቃሽ መሆናቸው ይነገራል።

በታጣቂዎች እንቅስቃሴ እና መንግሥት በሚወስዳቸው እርምጃዎች ምክንያት የሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች ሰላም ከራቃቸው ዓመታት አልፈዋል።

በዞኑ የሰላማዊ ሰዎች ግድያ፣ ዘረፋ፣ መፈናቀል እና እገታ ነዋሪውን ዕለት ከዕለት እየረበሸው የሚገኝ ጉዳይ ሆኗል።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የኩዩ ወረዳ አስተባባሪ አዛውንት ይህ ሥነ ሥርዓት “ለምህረት ወደ ፈጣሪ ማልቀስ” ይባላል ይላሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ሰላሌ ድሮ ድሮ ጥሩ ስም ነበረው። ትናንት አባቶቻችን እና የሰላሌ ጀግኖች የባርነት ሥርዓትን በመዋጋት ለኦሮሞ ሕዝብ ትልቅ መሠረት ጥለዋል። ዛሬ እየሆነ ያለው ግን ተቃራኒው ነው። የእኛ ሕዝብ እርስ በእርሱ ከመገዳዳሉ አልፎ የተገደለን የሚቀብር እንኳ ጠፍቷል። ሕይወታችን በጣም ተበላሽቷል። ሕዝቡ እየተፈናቀለ ነው” ብለዋል።

የደብረ ሊባኖስ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ሃደ ሲቄ ፈይቱ ወዳጆ በሰላሌ እየተገዳደሉ ያሉት ወንድማማቾች መሆናቸውን ይናገራሉ።

“በሁለት ወንድማማቾች መካከል ባለው መጠፋፋት ማንኛው ጥፋተኛ ነው የሚለውን ለይተን አናውቅም። ነገር ግን እያለቅን ነው። ትምህርት ቤቶች እየተቃጠሉ ነው። ወላድን ወደ ሐኪም ወስዳ የምታገለግል አምቡላንስ እየተቃጠለች ነው” ብለዋል።

ነዋሪዎቹ በአካባቢው ከአቅም በላይ ለሆነው ችግር መፍትሄ ፍለጋ በባሕላቸው መሠረት ፈጣሪን ለመመጸን በጋራ አደባባይ መውጣታቸውን ይናገራሉ።

“በሬ ጠምደን፣ ፈረስ ጭነን፣ ከለቸ (ግንባር ላይ የሚታሰር ምልክት) እና ጫጩ (ሴቶች በእጃቸው የሚያንጠለጥሉ ጌጥ) ይዘን ‘እግዚኦ’ ብለን ለምነናል።”

“የከበርከው ፈጣሪ እርዳን፤ እባክህ ታረቀን” በማለት ፈጣሪያቸውን መማጸናቸውን ሃደ ሲቄ ፈይቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሰላሌ ነዋሪዎች አደባባይ በወጡ ጊዜ ልጆች ልክ እንደ በሬ ተጠምደው ወንድ ልጆቻቸውን እንደ ሴት አልብሰው፤ ሴቶችን ደግሞ እንደ ወንዶች አልብሰው ታይተዋል።

ወንድ እና ሴት አለባበሳቸውን ተቀያይረው አደባባይ የታዩት “የሥርዓቱን መበላሸት” ለማሳየት ነው ሲሉ የሰሜን ሸዋ ዞን የባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ባለሙያ የሆኑት ሽመልስ ጣፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ክብር ያለው ዕቃ አደባባይ መውጣቱ፤ ሰዎች እና በሬዎች ላይ ቀንበር መደረጉ እንዲሁም መስቀል ይዘው መውጣታቸው የገጠማቸው ችግር ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ለማሳየት ነው” ብለዋል።

እንደ አቶ ሽመልስ ከሆነ በአካባቢው ባሕል መሠረት ሕዝቡ ፈጣሪውን ለምኖ ለውጥ የማያገኝ ከሆነ ቀጣዩ እርምጃ የችግሩ መንስዔ የሚባለውን መርገም ነው ይላሉ።

“አልፎ የሚሄድ ከሆነ ይህ አካል (ችግር ያስከተለው) የእኛ አካል አይደለም ተብሎ ይታወጃል። ሥርዓት ሲጣስ እርግማን ይከተላል” ሲሉ አቶ ሽመልስ ያስረዳሉ።

ሰሜን ሸዋን ጨምሮ በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች እየተጠናከረ የመጣው በታጣቂዎች የሚፈጽም ጥቃት፣ ግድያ፣ እገታ እና የንብረት ውድመት የነዋሪዎችን የዕለት ከዕለት ሕይወት ባለፉት ዓመታት ማመሳቀሉን ነዋሪዎች ይናጋራሉ።

መንግሥት ለዚህ ችግር ተጠያቂው ሽብርተኛ የሚለውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ተጠያቂ ሲያደርግ ቡድኑ ደግሞ ይህንን ክስ ያስተባብላል። ነገር ግን ነዋሪው ከሁለቱም ወገን በሚወሰዱ እርምጃዎች ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን ይናገራል።