አቶ ጌታቸው የትግራይ ክልል መዋቅሮች ጽህፈት ቤታቸው የማያውቀውን ስብሰባ እንዳያደርጉ አዘዙ

አቶ ጌታቸው ረዳ
የምስሉ መግለጫ, የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የክልሉ መንግሥት መዋቅሮች የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የማያውቀውን ስብሰባ እንዳያደርጉ አዘዙ።

ስብሰባ ለማድረግ የሚፈልጉ የክልሉ መንግሥት መዋቅሮች አስቀድመው ከፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ጋር “መግባባት” እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

አቶ ጌታቸውን ይህንን ማሳሰቢያ ያስተላለፉት ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም. ለክልሉ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ከተማዎች፣ ክፍለ ከተማዎች እና የወረዳ ምክር ቤቶች በጻፉት ደብዳቤ ነው።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች መካከል መከፋፈል የፈጠረው እና አቶ ጌታቸውንን ጨምሮ ሌሎች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከፓርቲ ኃላፊነት የተነሱበት ድርጅታዊ ጉባኤ በተጠናቀቀ ማግስት የተጻፈው ይህ ደብዳቤ፤ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ ይገልጻል።

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የተቋቋመው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር “በርከት ያሉ ስራዎችን እያከናወነ” እንደሚገኝ በደብዳቤው የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፤ “የተቀሩትንም ስራዎች ለመፈጸም ‘በጊዜ የለም’ መንፈስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት” እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው፤ “በተለይ በክረምት ወቅት ለመፈጸም፤ እንደ ኮሌራን ማከም እና መከለከል፣ የተፈናቀለ ህዝብን እና ግዛታዊ አንድነትን ማስመለስ፣ በጀት መዝጋት እና በጀት ማጽደቅ፣ የ2017 እቅድ ማዘጋጀት እና ሌሎች በርከት ያሉ መንግሥታዊ እና ህዝባዊ እቅዶች [ተይዘዋል]” ሲሉ የሚመሩትን ጊዜያዊ አስተዳደር ውጥኖች ዘርዝረዋል።

እነዚህን እቅዶች “ወደ ጎን በማለት የሚካሄድ ማንኛውም አይነት ስብሰባ የጊዜያዊ አስተዳደሩን እቅዶች እንደሚጎዳ” የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህም ምክንያት “ማንኛውም የተቀናጀ ስብሰባ መካሄድ እንደሌለበት” አሳስበዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅሮች ስብሰባ ማካሄድ “ሲያስፈልጋቸው” ማከናወን የሚችሉት “ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ተግባብተው” እንደሆነ አስታውቀዋል።

“ከዚህ ውጪ የሚጠራ ማንኛውም አይነት ስብሰባ ተቀባይነት እንደሌለው” የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ “የክላስተር አስተባባሪዎች” እና የክልሉ ቢሮዎች “ቁጥጥር እና ክትትል” እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በቅርቡ የተጠናቀቀው የህወሓት ጉባኤ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ሊቀመንበር አድርጎ መሾሙ ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, tplf

የምስሉ መግለጫ, በቅርቡ የተጠናቀቀው የህወሓት ጉባኤ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ሊቀመንበር አድርጎ መሾሙ ይታወሳል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት፤ ከክረምቱ ወራት ጀምሮ ዝግጅት እያደረገ ያለባቸው እና በሚቀጥለው ዓመት ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ከጠቀሷቸው ጉዳዮች መካከል “ያልተመለሰውን መሬት እና ተፈናቃይ ሕዝብ ወደነበረበት መመለስ፣ ሰላም ማፅናት እና የመልሶ ግንባታ ስራዎች ማከናወን” የሚሉት ይገኙበታል።

አቶ ጌታቸው ይህንን ትዕዛዝ ከማስተላለፋቸው ከጥቂት ቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ፤ በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል “የሚመራ ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን ለመንጠቅ ሙከራ ሊያደርግ እንደሚችል” ተናግረው ነበር።

አቶ ጌታቸው ቅዳሜ ዕለት ይህንን የተናገሩት፤ ራሳቸውን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ያልተሳተፉበት እና በምርጫ ቦርድ እውቅና ያልተሰጠው የፓርቲው ድርጅታዊ ጉባኤ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ነው።

ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው፤ አራት የፓርቲው አመራሮች ይህንን ጉባኤ እያደረጉ ያሉት “ከጀርባችን ደጀን ይሆነናል፣ ይደግፈናል በሚሉት ባልታወቀ የውጭ ኃይል ተማምነው” ነው ሲሉ ከስሰው ነበር። ይህ እርምጃም ወደ አልተፈለገ ችግር ሊመራን ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።

ጉባኤውን እያካሄዱ ያሉት የህወሓት አመራሮች ከጀርባቸው የተማመኑበት ኃይል እንዳለ የተናገሩት አቶ ጌታቸው፤ በእርሳቸው እየተመራ ያለውን “ጊዜያዊ አስተዳደር ሥልጣንን ለመንጠቅ የተለያዩ ሴራዎችን እንደሚያደርጉ እንጠብቃለን” ብለውም ነበር።

ይሁንና ከትናን በስቲያ ጉባኤውን ሲያጠናቀቅ አቶ ጌታቸውን ጨምሮ ራሳቸውን ከጉባኤው ባገለሉ 17 የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምትክ አዲስ ሰዎችን መርጧል። አቶ ጌታቸው የነበራቸውን የምክትል ሊቀመንበርነት ቦታም የፓርቲው ቃል አቀባይ ለነበሩት አቶ አማኑኤል አሰፋ ተሰጥቷል።

ጉባኤውን በመቃወም ራሳቸውን ያገለሉት የፓርቲው የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትም በተመሳሳይ በሌሎች ተተክተዋል።