“ያህያ ሲንዋር የተገደለበት ቤት የእኔ ነው” የጋዛው ስደተኛ

የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ረቡዕ ደቡባዊ ጋዛ ውስጥ በሚገኝ ቤት በእስራኤል ወታደሮች የተገደለው የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር

ከጋዛ የተሰደደው ፍልስጤማዊ የቀድሞው የሐማስ መሪ የተገደለበት ቤት ከመሰደዱ በፊት ይኖርበት የነበረ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናገረ።

አሽራፍ አቡ ጠሃ እንደሚለው ያህያ ሲንዋር የተገደለበት ቤት ባለፈው ግንቦት የእስራኤል ጥቃትን ሽሽት ቤት ንብረቱን ጥሎ እስኪወጣ ድረስ ላለፉት 15 ዓመታት የኖረበት ቤት ነው።

አሽራፍ የእስራኤል ድሮን በቀረፀው ቪድዮ ላይ በግማሽ የወደመውን ቤቱን ሲመለከት “እጅግ ደንግጦ” ነበር። ቤቱ በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ አካባቢ ኢብን ሴና መንገድ ላይ የሚገኝ ነው።

ባለፈው ዓመት መስከረም እስራኤል ላይ በሐማስ የተፈጸመው ጥቃት ዋነኛ አቀነባባሪ ነው የተባለው ያህያ ሲንዋር ረቡዕ ዕለት በእስራኤሎች ተገድሏል።

የእስራኤል መከላከያ ባሠራጨው የድሮን ቪድዮ ሲንዋር ከመገደሉ ከደቂቃዎች በፊት በአንድ በግማሽ በፈራረሰ ሕንፃ ውስጥ ካለ ሶፋ ላይ ተቀምጦ ይታያል።

አሽራፍ አቡ ጠሃ ለቢቢሲ አረብኛ እንደተናገረው ባለፈው ግንቦት መኖሪያ ቤቱን ጥሎ ወደ ኻን ዩኒስ ከተሰደደ በኋላ ስለቤቱ ምንም ነገር ሰምቶ አያውቅም።

አሽራፍ ሴት ልጁ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተመለከተችውን የሲንዋርን የመጨረሻ ሰዓታት የሚያሳይ ቪድዮ ስታሳየው ነው ቤቱ መሆኑን ያወቀው። ወንድሙ ቤታቸው መሆኑን እስኪያረጋግጥለት ድረስ አላመነም ነበር።

“ከዚያ ነው 'አዎ ይሄ የእኔ ቤት ነው' ያልኩት። ምሥሉን ሳየው በጣም ነበር የደነገጥኩት” ይላል አሽራፍ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሲንዋር እሱ ቤት ለምን እንደተደበቀ እና እንዴት እዚያ ሊገኝ እንደቻለ የሚያውቀው ነገር እንደሌለም ይናገራል።

“እኔም ሆንኩ ወንደሞቼ እና ልጆቼ ስለዚህ ጉዳይ በፍፁም የምናውቀው ነገር የለም።”

ቢቢሲ አሽራፍ ያቀረበውን የቀድሞ የቤቱን ይዞታ የሚያሳይ ቪድዮ እና ፎቶ ሲንዋር ከተገደለበት ጋር አነፃፅሮ ተመሳሳይነት እንዳለው ማረጋገጥ ችሏል። ነገር ግን ቤቱ የአሽራፍ ስለመሆኑ ቢቢሲ በግሉ ማረጋገጥ አልቻለም።

የእስራኤል መከላከያ ያሠራጨው የድሮን ቪድዮ ሲንዋር የተገደለበት የመኖሪያ ቤት ሕንፃ በአካባቢው ከሚገኙ በከፊል ከወደሙ ሕንፃዎች መካከል አንዱ መሆኑን ያሳያል።

እስራኤል ባለፈው ግንቦት ራፋህ ላይ በፈፀመችው ጥቃት ምክንያት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ትችት ሲደርስባት ነበር። የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ራፋህ ላይ በተከፈተው ጦርነት ምክንያት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማዊያን ተሰደዋል።

አብዛኛዎቹ ስደተኞች ለሁለተኛ እና ለሦስተኛ ጊዜ የተሰደዱ ሲሆን፣ ብዙዎቹ መጠለያ ፍለጋ ከሌሎች የጋዛ ክፍሎች ወደ ራፋህ የመጡ ነበሩ።

አሽራፍ እንደሚለው በራፋህ የሚገኘውን ቤቱን የገነባው ከወንድሞቹ ጋር በመሆን ነው። በወቅቱ 200 ሺህ ሼክል (የእስራኤል ገንዘብ) አውጥቶ የገነባው ቤቱ እስኪሰደድ ድረስ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነበር።

ሳሎን ውስጥ የነበሩትን ብርቱካናማ ሶፋዎች እንደሚያስታውሳቸው የሚናገረው አሽራፍ፣ ለመጨረሻ ጊዜ ያያቸው ከቤቱ ሲፈናቀል ነበር።

“ይህ ለእኔ ትልቅ ትውስታ ነው። ምክንያቱም ቤቱ ውስጥ ከነበሩት ዕቃዎች የተወሰኑትን የገዛችልኝ እናቴ ነበረች። ለእኔ ትልቅ ዋጋ ነበራቸው” ይላል።

“የተፈጠረው ነገር በጣም አሳዝኖኛል። የገነባሁት ቤቴ ወድሟል፤ የከፈልኩት ዋጋ እንዳይሆን ሆኗል። ፈጣሪ ብቻ ነው ሊክሰኝ የሚችለው።”

እስራኤል ከአንድ ዓመት በላይ በጋዛ ላይ እያካሄደችው ያለው ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን፣ በዚህም ከ42 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ አብዛኛው የጋዛ ቤቶች ወድመዋል።