የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በመንግሥት ዕገዳ እንደተጣለበት አስታወቀ

ካርድ

የፎቶው ባለመብት, card

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በኢትዮጵያ መንግሥት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እግድ እንደተጣለበት አስታወቀ።

በሰብአዊ መብቶች እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥበቃ ዙሪያ የሚሠራው ካርድ በአገሪቱ ሲቪል ማኅበራትን በሚመዘግበው እና በሚቆጣጠረው መንግሥታዊ አካል “ከፖለቲካ ገለልተኛ አለመሆኑን እና ከዓላማው ውጪ በመንቀሳቀስ” በሚል ዕግድ እንደተጣለበት ባወጣው መግለጫ አመለከተ።

አገር በቀሉ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ለመታገዱ በባለሥልጣኑ የቀረቡትን ምክንያቶች ያልተቀባላቸው ሲሆን፣ የዕግድ ውሳኔውም ተገቢውን ሕጋዊ ሂደቶች የተከተለ አይደለም ሲል ተቃውሟል።

በተጨማሪም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ውሳኔውን ከሳምንት በፊት በጻፈው ደብዳቤ ከማሳወቁ ውጪ ለዕግዱ በምክንያትነት በቀረቡት ጉዳዮች ላይ አስፈላጊው ምርመራ ስለመካሄዱ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ካርድ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

ካርድ ዕግዱ ከመተላለፉ ቀደም ብሎ ምርመራ መደረግ እንደነበረበት እና በዚህም ሂደት ውስጥ መሳተፍ እና ሊያውቀው ይገባ እንደነበር በመግለጽ ቅሬታውን አሳውቋል።

ካርድ በመንግሥታዊው ተቆጣጣሪ ተቋም የቀረበበት ከፖለቲካ ገለልተኛ ያለመሆን እና ከተነሳለት ዓላማ ውጪ መንቀሳቀስን በተመለከተ “[ካርድ] ከዓላማው ውጪ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ውስጥ አለመሳተፉን እና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ገለልተኛ መሆኑን” በመግለጽ የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።

“ዴሞክራሲን ብቸኛው የጨዋታው ሕግ ማድረግ” በሚለው መሪ ቃሉ በመመራት በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች መፍትሔ እንዲገኝ መሟገቱን እንደሚቀጥል የገለጸው ካርድ፣ ዕግዱ እንዲነሳለት ጥረት እንደሚያደርግ አመልክቷል።

የመብቶች እና ዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) የተጣለበትን ዕግድ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ጋር በመነጋገር ዕግዱ እንዲነሳለት ሕግን መሠረት ባደረገ መንገድ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ በመግለጽ የሌሎችንም ድጋፍ ጠይቋል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት ወጣቶች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ለሰላም፣ ለእኩልነት እና ለሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ ዘብ እንዲቆሙ የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን መስጠቱን እና ምርምሮችን ማካሄዱን አመልክቷል።

በሐምሌ 17/2011 ዓ.ም. ሕጋዊ ዕውቅናን ያገኘው ካርድ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩባት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያበበባት ኢትዮጵያን ለማየት የሚያስችሉ ሥራዎችን በመሥራት አስተዋፅዖ ሲያበረክት መቆየቱን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

በዚህም ከበርካታ አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በመቶ ሺዎች ወደ የሚቆጠሩ ዜጎች የሚደርሱ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጿል።

በተጨማሪም ካርድ ባለፉት ዓመታት በተናጠል እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን በሰላም፣ በሴቶች ጥቃት፣ በፕሬስ ነጻነት እና በሌሎችም የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዙሪያ ዘመቻዎችን ማካሄዱ ይታወሳል።