የቀድሞው የመከላከያ ሠራዊት የምድር ኃይል ዋና አዛዥ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሾሙ

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defense Force
ላለፉት ሰባት ዓመታት ገደማ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ጌቱ አርጋው እና ሁለት ምክትል ኮሚሽነሮች ከኃላፊነት ተነሱ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተነሱት አመራሮች ምትክ የቀድሞው የመከላከያ የምድር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናንት ጄነራል አስራት ደኔሮን እና ሁለት ምክትል ኮሚሽነሮችን ሾመዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 2/2018 ዓ.ም. ባወጣው መረጃ ዐቢይ ሌተናንት ጄነራል አስራት ደኔሮን የአዲስ አበባ ፖሊስን በኮሚሽነርነት እንዲመሩ መሾማቸውን ገልጿል።
አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙ ሌተናንት ጄነራል አስራት፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ረጅም ጊዜ የቆዩ ወታደራዊ አዛዥ ናቸው።
ሌተናንት ጄነራል አስራት፤ ከዚህ ቀደም የመከላከያ ሠራዊት የምድር ኃይል ዋና አዛዥ ሆነው አገልግለዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ለመቆጣጠር የተቋቋመውን የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት በመምራት ይታወቃሉ።
የብርጋዴር ጄነራልነት ማዕረግ የነበራቸው አስራት ወደ ሌተናንት ጄነራልነት ያደጉት ከስድስት ዓመት በፊት በጥር 2012 ዓ.ም. ነው። ሌተናንት ጄነራል አስራት፤ የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል።
በየካቲት 2014 ዓ.ም. ደግሞ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የደቡብ ሱዳን ተወካይ ሆነው ተሾመዋል። በዚህ ሹመት ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ያሰማራው የተኩስ አቁም እና የሽግግር ደኅንነት ሂደት ቁጥጥር መካኒዝምን በሰብሳቢነት መርተዋል።
በተጨማሪም ሌተናንት ጄነራል አስራት የመከላከያ ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ዘርፍ ኃላፊም ሆነው አገልግለዋል።

የፎቶው ባለመብት, addis ababa police
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምክትል ኮሚሽነት የሾሟቸው ረዳት ኮሚሽነር ቶፊቅ መደድ እና እርዚቅ ኢሳን ነው።
አዲሱ ምክትል ኮሚሽነር እርዚቅ፤ የአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድር ሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ነበሩ። የአማካሪነት ሹመቱን ጥቅምት ላይ ከማግኘታቸው አስቀድሞ ደግሞ የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ነበሩ።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባ እንዲሁም በገበታ ለሀገር ፕሮጀት የተገነባው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ግንባታ አስተባባሪም ነበሩ።
ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነርነት የተነሱት ጌቱ አርጋው ኃላፊነቱን የተረከቡት ከሰባት ዓመት ገደማ በፊት በሚያዝያ 2011 ዓ.ም. ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዋና ከተማዋን ፖሊስ እንዲመሩ ለዋና ኮሚሽነር እና ምክትል ኮሚሽነርነት ቦታ ባለሥልጣናት መሾማቸውን ከማሳወቅ ውጪ፣ ሹም ሽሩ ለምን እንዳስፈለገ እና ስለቀድሞው ኮሚሽነር የተባለ ነገር የለም።















