ሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን በቅርበት የተከታተሉት የሚሳዔል ሙከራ ማድረጓን ገለፀች

የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰሜን ኮሪያ ሁለት የአየር መቃወሚያ ሚሳዔሎችን በፕሬዚዳንቱ ኪም ጆንግ ኡን የቅርብ ክትትል መሞከሯን የአገሪቱ ብሔራዊ የመገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

የኮሪያ ማዕከላዊ የዜና አገልግሎት (KCNA) የጦር መሳሪያዎቹ "ከፍተኛ የውጊያ አቅም" ያላቸው እና "ልዩ ቴክኖሎጂ" የተገጠመላቸው መሆናቸውን ተጨማሪ ማብራሪያ ሳይሰጥ ዘግቧል።

ሙከራው የተካሄደው ቅዳሜ ዕለት ሲሆን "ሁለቱ የአየር መቃወሚያዎች ላይ የተገጠመው ቴክኖሎጂ ድሮኖችን እና ክሩዝ ሚሳኤሎችን ጨምሮ የተለያዩ የአየር ላይ ዒላማዎችን ለመምታት በጣም ተስማሚ መሆኑን አረጋግጧል" ሲል የዜና ተቋሙ ገልጿል።

ሙከራው የተካሄደው ደቡብ ኮሪያ ማክሰኞ ዕለት የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሁለቱን አገራት የሚለየውን ነጻ ወታደራዊ ቀጠና ለአጭር ጊዜ ማቋረጣቸውን ተከትሎ የማስጠንቀቂያ ጥይት መተኮሷን ካረጋገጠች ከሰዓታት በኋላ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕዝ ወደ 30 የሚጠጉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሰሜን እና በደቡብ መካከል ያለውን ድንበር አቋርጠዋል ሲል መናገሩን ዮንሃፕ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ፒዮንግያንግ ሴኡል "ሆን ብላ ትንኮሳ አካሄዳለች" ስትል ከስሳለች።

ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ደቡብ ኮሪያ እና ዩናይትድ ስቴትስ በአካባቢው ሰፊ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን እያደረጉ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት በዋሽንግተን በሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ሊ ጄ ሚዩንግ ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አዲስ የተመረጡት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ጥሪ ሲያደርጉ ነበር።

ነገር ግን፣ የኪም እህት በ ሊ መንግሥት የቀረበውን 'ሰላም እናውርድ፣ እርቅ እንፍጠር' የሚል ጥሪ ውድቅ አድርጋዋለች።

ኪም በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያን የጋራ ወታደራዊ ልምምዶች "በጣም ጠብ አጫሪ እና ግጭት ቀስቃሽ" ሲሉ ፈርጀውታል።

የሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት የአገሪቱን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ክምችት ከፍ ለማድረግ የያዙትን ዓላማ ለማፋጠን ቃል ገብተዋል።

በጥር ወር ሰሜን ኮሪያ ሃይፐርሶኒክ አረር የተገጠመለት አዲስ መካከለኛ መጠን ያለው ባለስቲክ ሚሳኤል ለሙከራ ማስወንጨፏን የገለፀች ሲሆን "በፓስፊክ ክልል ውስጥ ያሉ ተቀናቃኞችን በአስተማማኝ ሁኔታ ይመታል" ስትል ተናግራለች።

የደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሰሜን ኮሪያ ሩሲያን በመደገፍ ወደ ዩክሬን ወታደሮቿን በመላኳ የተነሳ የሚሳኤል ቴክኖሎጂን ከሞስኮ አግኝታለች ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የቀድሞው የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሺን ዎንሲክ ባለፈው ዓመት እንደተናገሩት፣ ሞስኮ ለፒዮንግያንግ የአየር መከላከያዋን ለማጠናከር የሚረዱ ሚሳኤሎችን እና ሌሎች መሳሪያዎችን ሰጥታለች።

ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ የሞከረቻቸው ሚሳዔሎች የትኛውን የሩስያ ቴክኖሎጂ ይዘዋል የሚለው ግልጽ አይደለም።

ሰሜን ኮሪያ በዓለም ላይ እጅግ ጨቋኝ ከሆኑ አምባገነን መንግሥታት መካከል አንዷ ስትሆን ኪም እና ቤተሰባቸው ለብዙ አስርተ ዓመታት የአገሪቱን ሥልጣን ይዘይ ይገኛሉ።

እአአ በ1953 የኮሪያ ጦርነት ካበቃ በኋላ ደቡብ እና ሰሜን ኮሪያ ሁለት የተለያዩ አገራት ሆነዋል።

ሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነትን ያልፈረሙ ሲሆን፣ ምንም እንኳ እስካሁን ድረስ አንዳቸው ሌላኛቸውን ለማጥቃት ተኩስ ባይከፍቱም እስከዛሬ ድረስ በጦርነት መንፈስ ውስጥ ናቸው።