የደቡብ ኮሪያ ጦር ሠራዊት በዝቅተኛ የወሊድ ምጣኔ የተነሳ በ20 በመቶ ቀነሰ

የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች ወታደራዊ ሰላምታ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለሙያዎች እንደሚሉት ደቡብ ኮሪያ ያላት ጦር ሠራዊት ቁጥር ከ500,000 በታች ወርዷል

የደቡብ ኮሪያ ጦር ሠራዊት ባለፉት ስድስት ዓመታት በ20 በመቶ ቀንሶ አሁን 450,000 ወታደሮች ብቻ እንዳሉት የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር እሁድ ዕለት ባወጣው ሪፖርት ገለፀ።

ሚኒስቴሩ የሠራዊቱ ቁጥር የቀነሰው በአገሪቱ ካለው ከፍተኛ የሆነ ዝቅተኛ የወሊድ ምጣኔ የተነሳ ነው መሆኑን አመልክቷል።

በደቡብ ኮሪያ ከዓለም አገራት ሁሉ ዝቅተኛ የሆነ የወሊድ ምጣኔ ያለባት አገር ናት።

ደቡብ ኮሪያ አሁንም ዜጎቿ ብሔራዊ ወታድርና አገልግሎት ውስጥ እንዲሳተፉ የምታደርግ ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያቷ ከጎረቤቷ ሰሜን ኮሪያ ጋር ይፋዊ ያልሆነ ጦርነት ውስጥ መሆኗን ነው።

ተመራማሪዎች በሐምሌ ወር ይፋ ያደረጉት ጥናት አገሪቱ 1.3 ሚሊዮን መደበኛ ወታደሮች እንዳሏት ከሚታመነው ከሰሜን ኮሪያ የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመመከት ቢያንስ 500 ሺህ ወታደሮች እንደሚያስፈልጋት ጠቁመዋል።

በወታደሮች ቁጥር ያለው ልዩነት ደቡብ ኮሪያን "በመከላከያ ረገድ ስኬታማ ለመሆን አስቸጋሪ መዋቅራዊ ሁኔታ ላይ እንድትገኝ" እንዳደረጋት ጥናቱ አመልክቷል።

ደቡብ ኮሪያ ቢያንስ 500 ሺህ ወታደሮች እንዲኖራት "በአገር አቀፍ ደረጃ ቆራጥ እርምጃ" መውሰድ እንደሚያስፈልጋት ተጠቁሟል።

የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር እሁድ ዕለት ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ በደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ኃይል ውስጥ ያሉት ክፍሎች ከ59 ወደ 42 ዝቅ ብለዋል።

ይህም ክፍሎቹ እንዲታጠፉ ወይንም ከሌላ ጋር እንዲዋሀዱ ተደርጎ መሆኑን በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።

ደቡብ ኮሪያ በአካባቢው እየጨመረ ላለው ቀጣናዊ ውጥረት ምላሽ ለመስጠት በሚል የመከላከያ በጀቷን እያሳደገች ነው።

ለ2025 የአገሪቱ መከላከያ የያዘው በጀት 43 ቢሊየን ዶላር ሲሆን፣ ይህም ከሰሜን ኮሪያ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የበለጠ ነው።

በደቡብ ኮሪያ ሁሉም አቅሙ ያላቸው ወንዶች ለ18 ወራት ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

በአገሪቱ ወንዶች ዘንድ የብሔራዊ ወታድርና አገልግሎት ተወዳጅነት የለውም።

አንዳንድ ተቺዎች ይህ ብሔራዊ አገልግሎት የወጣት ወንዶችን ሥራ ያስተጓጉላል ብለው የሚከራከሩ ሲሆን፣ በጉዳዩ ዙሪያ የፆታ እኩልነት ጥያቄም አብሮ ይነሳል።

አንዳንድ ወግ አጥባቂዎች በአገሪቱ እያንዣበበ ባለው የሥነ ሕዝብ ቀውስ ውስጥ ሴቶችም ለውትድርና መመዝገብ አለባቸው ሲሉ ይከራከራሉ።

አገሪቱ በዓለም ዝቅተኛ የወሊድ መጠን በማስመዝገብ የራሷን ክብረ ወሰን ደጋግማ ሰብራለች።

የ2023 አሃዝም ከ8 በመቶ ቀንሶ ወደ 0.7 መውረዱን ያሳያል። ይህ አንዲት ሴት በሕይወቷ ዘመኗ የምትወልዳቸው ልጆች ቁጥር ነው። የአንድ አገር የሕዝብ ቁጥር እንዲረጋጋ አሃዙ 2.1 መሆን አለበት።

የቁጥሩ መቀነስ በዚሁ ከቀጠለ በአውሮፓውያኑ 2100 የሰሜን ኮሪያ ሕዝብ በግማሽ እንደሚቀንስ ይገመታል።