ሰሜን ኮሪያ በደቡብ ኮሪያ ድንበር ላይ የነበሩትን የድምጽ ማጉያዎች አነሳች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የደቡብ ኮሪያ ጦር ሰሜን ኮሪያ በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ ፕሮፓጋንዳ ለማሰራጨት የሚያገለግሉትን አንዳንድ የድምጽ ማጉያዎችን ማንሳት መጀመሯን አስታውቋል።
ይህ የሰሜን ኮሪያ እርምጃ በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ዘመቻ ሲያደርጉ ለነበሩት አዲሱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚደንት ሊ ጃይ ሚዩንግ አዎንታዊ ምላሽ ይመስላል ።
ደቡብ ኮሪያ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አንዳንድ ለፕሮፓጋንዳ የምትጠቀምባቸውን ድምጽ ማጉያዎች አንስታለች።
በሰኔ ወር ሊ ሥልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ከወታደራዊ ነፃ በሆነው ቀጠና ስርጭቱን አስቁመው ነበር፤አሁን ደግሞ ሰሜን ኮሪያ ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥታለች።
የደቡብ ኮሪያ ስርጭቶች ብዙ ጊዜ የኬ ፖፕ ሙዚቃዎችን እና ዜናዎችን ያቀርብ ነበር።
ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ እንደ እንስሳት ማላዘን ያሉ የሚረብሹ ድምፆችን ታጫውት ነበር ተብሏል።
የደቡብ ኮሪያ ጦር ቅዳሜ ዕለት በሰጠው መግለጫ "የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ በድንበር ላይ ባሉ በአንዳንድ አካባቢዎች የፕሮፓጋንዳ ማስተላለፊያ ድምጽ ማጉያዎችን እያነሱ ነው" ብሏል።
አክሎም "መሳሪያዎቹ በሁሉም ክልሎች መወገዳቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤እንዲሁም ጦሩ ተያያዥ እንቅስቃሴዎችን መከታተሉን ይቀጥላል።"
ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያየ ጊዜ በድምጽ ማጉያዎቹ የሚተላለፉት ስርጭቶች ቆመው ያውቃሉ።
ነገር ግን ከስድስት ዓመት ፋታ በኋላ፣እአአ በሰኔ 2024 ፒዮንግያንግ በቆሻሻ የተሞሉ ፊኛዎችን ወደ ደቡብ ኮሪያ መላኳን ተከትሎ በድጋሚ ተጀምረዋል።
በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ከሁለቱም ወገኖች በሚመጣው ድምጽ የተነሳ፣አንዳንዴም እኩለ ሌሊት ላይ ጨምሮ፣ ሕይወታቸውን እንዳመሳቀለው በመግለጽ ቅሬታ ያቀርባሉ።
ሴኡል ስርጭቱ በቀን እስከ 10 ኪ.ሜ. በሌሊት ደግሞ እስከ 24 ኪ.ሜ. ድረስ ሊሰማ እንደሚችል ተናግራለች።
ነገር ግን ደቡብ ኮሪያ በሰኔ ወር ስርጭቷን ካቋረጠች በኋላ፣ የሰሜን ኮሪያውያን ሰብዓዊ መብት እንዲሻሻል የሚሟገቱ ድርጅቶች እርምጃውን ተችተዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በሰሜን እና በደቡብ ኮሪያ መካከል ያለው ግንኙነት እያሽቆለቆለ የመጣው በፒዮንግያንግ ላይ የከረረ አቋም በነበራቸው በፕሬዚዳንት ዩን ሱክ ዮል የሥልጣን ዘመን ነው።
ዩን በታህሳስ ወር ላይ ከፀረ መንግሥት ኃይሎች እና ከሰሜን ኮሪያ ደጋፊዎች ዛቻዎችን አደርሰዋል በሚል ደቡብ ኮሪያን ለአጭር ጊዜ በወታደራዊ ሕግ ለማስተዳደር ከሞከሩ በኋላ ከሥልጣን ተወግደዋል።
ምንም እንኳ እውን ለመሆን ሩቅ ቢሆንም ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያውያንን ማቀራረብ የረዥም ጊዜ ሕልም ነው። ነገር ግን ከአገሪቱ ምስረታ ጀምሮ የዘለቀው የሰሜኑ ርዕዮተ ዓለም እስከ አሁኑ የአገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ድረስ ቀጥሎ በስተመጨረሻም የማቀራረብ ሃሳቡን እአአ በ2024 እርግፍ አድርገው ትተውታል።
እአአ በ1953 ያለ የሰላም ስምምነት የኮሪያ ጦርነት ያበቃ ቢሆንም ሁለቱም ሀገራት አሁንም በጦርነት መንፈስ ውስጥ ናቸው።















