የውሻ ሥጋ ለምግብነት እንዳይቀርብ ያገደችው ደቡብ ኮሪያ እና ውሻ አርቢዎች

የፎቶው ባለመብት, Hyunjung Kim/BBC News
ሬቨረንድ ጁ ዮንግ-ቦንግ በዋነኛነት የእግዚአብሔርን ቃል ይሰብካሉ። ጎን ለጎን ደግሞ ለእርድ የሚሆኑ ውሾችን ያሳድጋሉ።
ሥራው ጥሩ እየሆነላቸው አይደለም። አሁን ደግሞ ሕገ ወጥ ከመሆን ጫፍ ላይ ደርሷል።
"ካለፈው ክረምት ጀምሮ ውሾቻችንን ለመሸጥ እየሞከርን ነበር። ነጋዴዎቹ ግን ፈቃደኛ አልሆኑም" ሲሉ የ60 ዓመቱ ሰባኪ ለቢቢሲ ተናግረዋል። "አንድ ገዢ እንኳን ብቅ አላለም።"
ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የደቡብ ኮሪያ መንግሥት የውሻ ሥጋ ለምግብነት ሽያጭ ለገበያ እንዳይቀርብ አገር አቀፍ ደረጃ እገዳ ጥሏል።
ባለፈው ጥር ወር የጸደቀው ሕግ እንደ ሬቨረንድ ጁ ያሉ አርቢዎች ሥራቸውን እንዲየቆሙ እና የቀሩትን እንስሶቻቸውን እንዲሸጡ እስከ የካቲት 2027 ድረስ የእፎይታ ጊዜ ተቀምጦላቸዋል።
ብዙዎች ግን ከትውልድ ትውልድ መተዳደሪያ ሆኖ የዘለቀ ሥራን ለማቋረጥ በቂ ጊዜ አልተሰጠም ሲሉ ይሞግታሉ። ባለሥልጣናት ለገበሬዎቹም ሆነ ግማሽ ሚሊዮን ለሚገመቱ ውሾች በቂ መፍትሔ አላቀረቡም በሚል ይተቻሉ።
እገዳውን የሚደግፉ ባለሙያዎች እና የእንስሳት መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ ሌሎችም በአፈጻጸሙ ዙሪያ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, News1
በእፎይታ ጊዜ አጋማሽ ላይ ቢደረስም የውሻ አርቢዎቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ የማይሸጡ እንስሳትን እና ሊዘጉ የማይችሉ እርሻዎችን ይዘው ለመቀመጥ ተገደዋል። ሥራቸው በመሆኑም የገቢ ምንጫቸውም ተቋርጧል።
ኢንዱስትሪውን የሚወክለውን የኮሪያ የምግብ ውሾች ማኅበር በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ሬቨረንድ ጆ "ሰዎች እየተሰቃዩ ነው። ዕዳ ውስጥ ተዘፍቀናል፤ መክፈልም አልቻልንም፤ አንዳንዶች ደግሞ… አዲስ ሥራ ማግኘት አይችሉም" ብለዋል።
"ተስፋ የለሽ ሁኔታ ነው የተከሰተው።"
የተደራረበው እንቅፋት
ቻን-ዎ 600 ውሾችን ለማስወገድ 18 ወራት ብቻ አላቸው።
ከዚያ በኋላ ግን የ33 ዓመቱ ለምግብነት የሚቀርቡ የእንስሳት ሥጋን የሚያጋጁ (ስሙ የተቀየረ) ሰዎች ውሻዎችን ይዘው ከተገኙ እስከ ሁለት ዓመት በእስራት ይቀጣሉ።
"የእፎይታ ጊዜው ሲጠናቀቅ በእርሻዬ ላይ የሚቀሩትን ውሻዎችን ማቆት አልችልም። ሁሉንም ንብረቶቼን (በእርሻው ላይ) ኢንቨስት አድርጌያለሁ። ውሾቹንም አይወስዷቸውም" ብለዋል።
ውሾችን የሚገዙ ነጋዴዎችን እና ሥጋ ቤቶች ከዕገዳው በፊት በአማካይ በሳምንት ግማሽ ደርዘን ውሻ ይገዙ ነበር።
የእንስሳት መብት ተሟጋቾችን እና ባለሥልጣናትን በመጥቀስም የውሻ ሥጋ ንግድን ሕገ-ወጥ ለማድረግ ከፍተኛ ትግል ቢያደርጉም የተረፉትን እንስሳት ምን እንደሚያደርጉ ግልጽ ዕቅድ እንደሌላቸው ጠቅሰዋል። በመንግሥት ግምት መሠረት ወደ 500 ሺህ ይጠጋል።
"እነሱ [ባለሥልጣናቱ] ያለ ምንም ግልጽ ዕቅድ ሕጉን አጽድቀዋል። ውሾቹን ግን መውሰድ እንደማይችሉ እየገለጹሉ ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Hyunjung Kim/BBC News
በሁውማን ዎርልድ ፎር አኒማል ኮሪያ (ኤችዋክ) የዘመቻ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ሊ ሳንግኪዩንግም እነዚህን ስጋቶች ያስተጋባል።
"የውሻ ስጋ እገዳው ቢጸድቅም መንግሥትም ሆነ የሲቪክ ማኅበረሰቦች የቀሩትን ውሾች እንዴት ማዳን እንደሚችሉ አሁንም መፍትሔ እየፈለጉ ነው። አሁንም ክፍተት ያለበት በሚቀሩት ውሾች ዙሪያ ያለው ውይይት ነው" ብለዋል።
የግብርና፣ ምግብ እና የገጠር ጉዳዮች ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የእርሻ ባለቤቶች ውሾቻቸውን ካስረከቡ ባለሥልጣናት ወደ መጠለያ ይወስዷቸዋል።
ለእነሱ መኖሪያ ማግኘት ግን ፈታኝ ሆኗል።
በውሻ ሥጋ ኢንዱስትሪ ውስጥ ክብደት ያላቸው ውሻዎች ጥሩ ዋጋ ስላላቸው እርሻዎች ትላልቅ ዝርያ ያላቸውን ውሻዎች ይመርጣሉ። ብዙ ሰዎች በአፓርታማ ቤቶች ውስጥ በሚኖሩባት ደቡብ ኮሪያ የሚኖረው የከተማ ማኅበረሰብ የሚፈልጋቸው የቤት እንስሳት ባለቤቶች ከዚህ ተቃራኒ የሆኑትን ነው።
ከእርሻዎች ከሚመጡ ውሾች ጋር በተያያዘ ማኅበራዊ መገለል እንዳለ ሊ ይገልጻሉ። በደቡብ ኮሪያ ውስጥ "አደገኛ" ተብሎ የተፈረጀው እና እንደቤት እንስሳ ለመያዝ የመንግሥትን ፍቃድ የሚያስፈልገው ቶሳ-ኢኑ የተባለው ዝርያ ወይም ከዚሁ ዝርያ ጋር የተዳቀሉ መሆናቸው ጉዳዩን የበለጠ የተወሳሰበ ያደርገዋል።
የነፍስ አድን መጠለያዎች ደግሞ ከወዲሁ ተጨናንቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Hyunjung Kim/BBC News
"ይህ የማይታመን ነው" ይላሉ ቻን-ዎ።
"ሕጉ በእነዚህ ቡድኖች ፍላጎት መሠረት ስለተዘጋጀ ለውሾቹም መፍትሄ አዘጋጅተዋል ኃላፊነትንም ይወስዳሉ ብዬ አስቤ ነበር። አሁን ግን የእንስሳት መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጭምር ግድያ ብቸኛው አማራጭ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ።"
የኮሪያ የእንስሳት ደኅንነት ማኅበር ኃላፊ የሆኑት ቾ ሄ-ክዩንግ በመስከረም 2024 የእንስሳት መብት ተሟጋቾች በተቻለ መጠን ብዙ እንስሳትን ለማዳን ቢሞክሩም "የሚቀሩ ውሾች እንደሚኖሩ" አምነዋል።
"የቀሩት 'የጠፉ እና የተጣሉ' ከሆኑ በጣም ያሳዝናል። ነገር ግን ይገደላሉ" ብለዋል።
መንግሥት ከሳምንታት በኋላ እነዚህን ስጋቶች ለማስወገድ እንስሳትን መግደል "በእርግጥ" የዕቅዳቸው አካል አለመሆኑን አስተዋውቋል።
በቅርቡ ማፍራ የእንስሳት መጠለያን ለማስፋት እና የግል ተቋማትን ለመደገፍ በዓመት 4.3 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እያደረገ መሆኑን እና ሥራቸውን ቀደም ብለው ላቆሙ ገበሬዎች እስከ በአንድ ውሻ 450 ዶላር እንደሚሰጥ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Hyunjung Kim/BBC News
በሴዑል ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምና ትምህርት ቢሮ ዳይሬክተር የሆኑት ቹን ሚዩንግ-ሱን ግን መንግሥት ለሚቀሩት ውሻዎች የያዘው ዕቅድ ብዙ ነገር የጎደለው መሆኑን ይስማማሉ።
"ውሾቹን እንዴት 'ማስወገድ' እንደሚቻል የሚያሳይ ተጨባጭ ውይይት መደረግ አለበት" ብለዋል።
"ማሳደግም ሆነ መግደል አማራጭ መሆን አለባቸው። [ነገር ግን] ውሻዎችን ጭካኔ ከተሞላበት እርድ ለማዳን ወደ እነሱን መግደል ብቻ ከዞርን ሰዎች ልባቸው እንደሚሰበር እና እንደሚናደድ መዘንጋት የለበትም።"
መተዳደሪያቸው ይናጋል
አንዳንዶች እንደ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ባሉ አገራት እንስሳቱን ወደ ፍቃደኛ አሳዳጊዎች መላክንም አንዳንዶች እንደ መፍትሔ ያቀርባሉ።
ኤችዋክ 200 የሚደርሱ ውሻዎችን በአውሮፓውያኑ 2023 ከአሳን ከተማ ወደ ካናዳ እና አሜሪካ ልኳል።
የእርሻው ባለቤት የነበሩት የ74 ዓመቱ ያንግ ጆንግ ታኢ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ ውሻዎቻቸውን በጭነት መኪና ላይ ሲጭኑ በተመለከቱት ርህራሄ ተደንቀዋል።
"እንስሳቱን የሚይዙበትን መንገድ ሳይ፤ ሰዎችን እንደሚንከባከቡት በእርጋታ እና በፍቅር መሆኑ በጣም ልቤን ነክቶታል" ብለዋል።
"እኛ እንደዚያ አንንከባከባቸውም። ለእኛ ውሻዎችን ማሳደግ መተዳደሪያችን ነበር። ከእንስሳት ቡድን የተውጣጡት ሰዎች ግን ውሻዎቹን ልክ እንደሰው ያዩዋቸው ነበር። ይህ ደግሞ ልቤን ነክቶታል።"

የፎቶው ባለመብት, Hyunjung Kim/BBC News
ሆኖም ግን ያንግ በውሻ እርባታ ላይ የተጣለውን እገዳ እንደማይቀበሉት ለመጨመር ግን ወደ ኋላ አላሉም።
"ውሾች እንስሳት በመሆናቸው የውሻ ሥጋ ከታገደ ታዲያ ለምንድነው እንደ ላም፣ አሳማ ወይም ዶሮ ያሉትን እንስሳት መብላት ተገቢ የሆነው?" በማለት ተናግረዋል። "አንድ ዓይነት ነገር ነው። እነዚህ ነገሮች ሰዎች እንዲኖሩባቸው በተፈጥሮ የተገኙ ናቸው።"
እንደ ቹን አባባል ግን ውሻ መብላት ከሌሎች ሥጋዎች ጋር አንድ ዓይነት አይደለም። የውሻ ሥጋ ከምግብ ደኅንነት እና ንፅህና አንጻር የበለጠ አደጋ እንደሚያመጣ ጠቁመዋል። ከመደበኛ እና ከተስተካከለ የሥጋ ምርት ሥርዓት ጋር ባልተጣመረበት ደቡብ ኮሪያ ይህ ጉዳይ ይበልጥ አሳሳቢ ነው።
ሥጋው በቻይና፣ በጋና፣ በኢንዶኔዥያ፣ በናይጄሪያ፣ በታይላንድ እና በአንዳንድ የሕንድ አካባቢዎችም ለምግብነት እንደሚውል ሂውማን ወርልድ ፎር አኒማልስ ዘግቧል።
በኮሪያ ታሪክ ውስጥ ለምግብነት የሚውለው የፍጆታ መጠን ሲለዋወጥ ቢቆይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በደቡብ ኮሪያ ውስጥ እንደመጥፎ ልማድ እየተቆጠረ መጥቷል።
በአውሮፓውያኑ 2024 በተደረገ የመንግሥት የሕዝብ አስተያየት 8 በመቶዎቹ ባለፉት 12 ወራት ብቻ የውሻ ሥጋ ሞክረው እንደነበር ገልጸዋል። ይህ አሃዝ በ2015 (እአአ) ከነበረበት 27 በመቶ ቀንሷል።
እገዳው ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ በደቡብ ኮሪያ ከሚገኙት አንድ ሺህ 537 የውሻ እርሻዎች ውስጥ 623ቱ ተዘግተዋል።
"ማኅበረሰብ እና ባህል እየተሻሻለ ሲሄድ የደቡብ ኮሪያ ማኅበረሰብ የውሻ ሥጋ ማምረት ለማቆም ወስኗል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Hyunjung Kim/BBC News
ለብዙዎች ግን ሕይወታቸውን የገነቡበት ኢንዱስትሪ ሆኖ ቆይቷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና በውሻ ሥጋ ንግድ ላይ ለረዥም ጊዜ ሲተዳደሩ የቆዩ ሰዎች ሥራው ሕገወጥ በመሆኑ ራሳቸውን እንዴት አንደሚያስተዳድሩ እርግጠኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
አንዳንዶች የተወለዱት በኮሪያ ጦርነት ወቅት መሆኑን እና በረሃብ መኖር እንደሚችሉ ስለሚያውቁ ለድህነት ሕይወት ራሳቸውን እንዳዘጋጁ ጠቁመዋል። ሌሎች ደግሞ ንግዱ በድብቅ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በርካቶች የሚስማሙበት ደግሞ ለወጣት ገበሬዎች እርምጃው በይበልጥ አሳሳቢ ነው።
"በዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ወጣቶች አስቸጋሪ ነገር እያጋጠማቸው ነው" ብለዋል ጆ። "ውሾቹን መሸጥ ስለማይችሉ በፍጥነት መዝጋትም አይችሉም። ወደፊትም ሆነ ወደ ኋላ ምንም መንገድ ስለሌላቸው በመሐል ተቀርቅረዋል።"
ቻን-ዎ በ23 ዓመቱ ከአሥር ዓመት በፊት በኢንዱስትሪው ውስጥ መሥራት ሲጀምር "የውሻ ሥጋ ያለው ግንዛቤ ያን ያህል አሉታዊ አልነበረም" በማለት ያስታውሳል።
"በዙሪያዬ ካሉ ሰዎች አንዳንድ አስተያየቶች ነበሩ። ስለዚህ በዚያን ጊዜም ቢሆን ቀሪውን ሕይወቴን በሙሉ የምሠራው እንዳልሆነ አውቄ ነበር" ሲሉ አክለዋል።
እገዳው ግን ከተጠበቀው ጊዜ ፈጥኖ መጥቷል። ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ "ኑሮን መግፋት እርግጠኛ ያልሆነ ሆኗል" ብለዋል።
"አሁን የምንጠብቀው የእፎይታ ጊዜ እንዲራዘም እና (ከቀሪዎቹ ውሻዎች ጋር ያለው) ሂደት ቀስ በቀስ እንዲራዘም ብቻ ነው።"
ሌሎችም ይህንኑ ተስፋ ያደርጋሉ።
"በአሁኑ ጊዜ ሰዎች አንድ ነገር ሊለወጥ እንደሚችል ተስፋ በማድረግ አሁንም እየሠሩ ነው። ምናልባት የእፎይታ ጊዜው ሊራዘም ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል ጆ። "በ2027 ግን አንድ አስከፊ ነገር እንደሚከሰት በእውነት አምናለሁ።"
"ሕይወታቸው ሙሉ በሙሉ የሚፈተን ብዙ ሰዎች አሉ።"















