ሰሜን ኮሪያ ለፕሮፓጋንዳ የምትጠቀምባቸውን ድምጽ ማጉያዎች አነሳች መባሉን አስተባበለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰሜን ኮሪያው መሪ የኪም ጆንግ ኡን እህት ደቡብ ኮሪያ ፒዮንግያንግ በድንበር አካባቢ ለፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ የምትጠቀምባቸውን ድምጽ ማጉያዎቿን አንስታለች መባሉን አስተባብለች።
ኪም ዮ ጆንግ ሐሙስ ዕለት የአገሪቱ ብሔራዊ የመገናኛ ብዙኃን ኬሲኤንኤ ባተመው መግለጫቸው ላይ ሰሜን ኮሪያ ድምጽ ማጉያዎቹን "ፈጽሞ አላነሳችም" እና "ለማንሳት ፈቃደኛ አይደለችም" ብለዋል።
"ከደቡብ ኮሪያ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሻሻል ፍላጎት እንደሌለን በተለያዩ አጋጣሚዎች አብራርተናል" በማለት ይህ አቋም "ወደፊት በሕገ መንግሥታችን ላይ ይካተታል" ሲሉ ተናግረዋል።
የደቡብ ኮሪያ ጦር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሰሜን ኮሪያ በድንበር አካባቢ የሚገኙ የተወሰኑ ድምጽ ማጉያዎቿን እንዳነሳች ተናግሮ ነበር።
ደቡብ ኮሪያ በድንበር አካባቢ ለፕሮፓጋንዳ ማሰራጫነት የተከለቻቸውን የተወሰኑ ድምጽ ማጎያዎች ማንሳቷ ይታወቃል።
የሰሜን ኮሪያ የፕሮፓጋንዳ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር ኪም የሴኡል መረጃ "በአንድ ወገን ግምት ላይ የተመረኮዘ መሠረተ ቢስ የአንድ ወገን ግምት እና አሳሳች" ነው ብለዋል።
ከፕሮፓጋንዳ መልዕክቶች በተጨማሪ፣ ደቡብ ኮሪያ በድምጽ ማጉያዎቹ ብዙውን ጊዜ የኬ-ፖፕ ዘፈኖችን ያስደምጣሉ።
ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ እንደ እንስሳት ማላዘን ያሉ የሚረብሹ ድምጾችን ትለቅቃለች።
በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የደቡብ ኮሪያ ነዋሪዎች ከሁለቱም ወገኖች አንዳንዴ በእኩለ ለሊት ጭምር በሚለቀቁ ድምጾች ሕይወታቸው መረበሹን በመግለጽ ቅሬታ ያሰማሉ።
ፒዮንግያንግ የሴኡልን ፕሮፓጋንዳ የጦርነት ድርጊት አድርጋ የምትቆጥረው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ድምጽ ማጉያዎቹን ለመምታት ዝታ ታውቃለች።
የደቡብ ኮሪያ ድምጽ ማጉያ ስርጭቱ ዳግም የጀመረው ከስድስት ዓመታት እረፍት በኋላ በሰኔ 2024 ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ ዮል በሰሜን ኮሪያ ላይ ያላቸው የከረረ አቋም ይፋ ከሆነ በኋላ ነው።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት እየተካረረ ሲመጣ ፒዮንግያንግ በቆሻሻ የተሞሉ ፊኛዎችን ወደ ደቡብ ልካለች።
አዲሱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ሊ ጄይ ሚዩንግ በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ያለውን ግንኙነትን ለማሻሻል ጥረት ለማድረግ ተናግረዋል።
ደቡብ ኮሪያ በሰኔ ወር ሊ ስልጣን እንደያዙ የፕሮፓጋንዳ ስርጭቱን አቋርጣለች።
በዚህም የአገሪቱ ጦር እርምጃው የተወሰደው "የነበረውን እምነት ለመመለስ" እና "በኮሪያ ልሳነ ምድር ሰላምን ለማስፈን" በሚል መሆኑን ገልጿል።
አሁንም በሁለቱ ጎረቤቶች መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት የተሞላበት ነው።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ በጋራ ወታደራዊ ልምምዶች ለማድረግ ማቀዳቸውን ተከትሎ ሰሜን ኮሪያ "ቆራጥ ምላሽ" እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች።















