'እንደ ባሪያ' እንዲሠሩ ወደ ሩሲያ የሚላኩት ሰሜን ኮሪያውያን የግንባታ ሠራተኞች

ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ወጣቶቿን ወደ ግንባር ማሰማራቷን ተከትሎ በሥራው ዘርፍ የሰው ኃይል እጥረት ገጥሟታል።
ይህንንም ክፍተት ለመመሙላት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰሜን ኮሪያውያን ወደ ሩሲያ እየሄዱ ነው።
ሆኖም በሩሲያ የሥራ ቅጥራቸው "ባርነት ሆኖብናል" ይላሉ።
ሩሲያ በዚህ ጦርነት የሰሜን ኮሪያ ሚሳዔሎችን ብቻ ሳይሆን ወታደሮችንም በጦር ግንባሮች አሰማርታ ነበር።
ሩሲያ በርካታ ወታደሮቿን በግንባሮች አሰማርታለች የተወሰኑትም ተገድለውባታል፤ ወይም ከአገር የወጡም አሉ።
በዚህም የተነሳ በተፈጠረው የሠራተኛው ኃይል እጥረት ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ በሚመጡ ሠራተኞች እየተማመነች እንደሆነ የደቡብ ኮሪያ የስለላ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ከዚህ አስከፊ የሥራ ሁኔታ እንዲሁም ከሩሲያ የወጡ ስድስት የሰሜን ኮሪያ ሠራተኞችን ከደቡብ ኮሪያ መንግሥት ባለሥልጣናት አስተባባሪነት እንዲሁም ተመራማሪዎች እና ሠራተኞችን ለመታደግ እየሞከሩ ያሉ አካላትን አነጋግሯል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰሜን ኮሪያውያን ሠራተኞች የሥራ ሁኔታቸው ከመክፋቱ በተጨማሪ የሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናት እንዳያመልጡ ቁጥጥራቸውን አጥብቀዋል ይላሉ።
ጂን የተባለው ሰሜን ኮሪያዊ ሩሲያ እንደደረሰ ከአውሮፕላን ማረፊያው ወደ ግንባታ ስፍራው የወሰደው የሰሜን ኮሪያ የፀጥታ ወኪል ነው ይላል።
ይህ የፀጥታ ሠራተኛ ማንንም እንዳያዋራ እንዲሁም የማይመለከተውን እንዳያማትር ትዕዛዝ እንደሰጠው ጂን ያስረዳል።
"የውጭው ዓለም ጠላታችን ነው" ሲል ነበር የነገረው ይኸው ወኪል።
የመኖሪያ ቤት ሕንጻዎች ግንባታ ላይ ወዲያውኑ የተሠማራው ጂን በቀን ከ18 ሰዓታት በላይ መሥራት ሕይወቱ ሆነ።
ስድስቱም ሠራተኞች በዚህ የከፋ የሥራ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ የሚገልጹ ሲሆን፣ ጠዋት 12 ሰዓት ጀምረው እስከ ሌሊት ስምንት ሰዓት ድረስ በግንባታ ሥራ ላይ ያሳልፋሉ።
በዓመት መውሰድ የሚችሉት እረፍት ሁለት ቀናት ብቻ ነው ይላሉ።
ከሩሲያ ማምለጥ የቻለ ታኤ [ስሙ የተቀየረ] የተባለ ሠራተኛ ሌሊት ስምንት ሰዓት ገብቶ ጥዋት 12 ሰዓት ተነስቶ ሥራ ለመሥራት እጁ ሽባ የሆነ ይመስል ይያያዝ እንደነበር ያስረዳል።
"አንዳንዶች ሥራውን አቋርጠው ሄደው ይተኛሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ቆመው የሚተኙም አሉ። ነገር ግን ተቆጣጣሪዎች ያገኙዋቸው እና ይደበድቧቸው ነበር። የሞት ያህል ነበር" ይላል ቻን [ስሙ የተቀየረ] የተባለ ሠራተኛ።
"ሁኔታው በእውነቱ በጣም የከፋ ነው" ይላሉ በደቡብ ኮሪያ ዶንግ ኤ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ካንግ ዶንግ ዋን።

ፕሮፌሰሩ የሰሜን ኮሪያ ሠራተኞችን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ በተደጋጋሚ ወደ ሩሲያ ሄደዋል።
"ሠራተኞቹ በጣም አደገኛ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ነው ሥራቸውን የሚያከናውኑት። ምሸት ላይ መብራቶች ይጠፋሉ እናም ደኅንነታቸው ሳይጠበቅ በጨለማ ውስጥ ይሠራሉ" ሲሉ ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።
ከዚህ የከፋ ሁኔታ ያመለጡ ሠራተኞች ቀን ከሌት የሚያሳልፉት በእነዚህ የግንባታ ቦታዎች ሲሆን፣ የሰሜን ኮሪያ የደኅንነት ሠራተኞች ይከታተሉናል ይላሉ።
የማደሪያ ስፍራዎቻቸው የቆሸሹ፣ የተጨናነቁ የዕቃ ማጓጓዣ ኮንቴይነሮች እና በተባይ የተወረሩ ናቸው። አንዳንድ ማደሪያ ስፍራዎቻቸው ደግሞ ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ ሕንጻዎች ናቸው።
ናም [ስሙ የተቀየረ] የተባለ ሌላ ሰሜን ኮሪያዊ የጉልበት ሠራተኛ በአንድ ወቅት ከግንባታው ስፍራ አራት ሜትር ወደታች ወድቆ ፊቱ ክፉኛ ተጎድቶ ሥራውን መሥራት አልቻለም ነበር።
ሆኖም ተቆጣጣሪዎቹ ሆስፒታል ሄዶ ሕክምና እንዲያገኝ አልፈቀዱለትም።
ቀደም ባሉት ጊዜያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰሜን ኮሪያውያን ሠራተኞች ወደ ሩሲያ አቅንተው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ላለባቸው መሪያቸው ኪም ጆንግ ኡን በሚሊዮን የሚቆጠር ፓውንድ አስገኝተውላቸዋል።
ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2019 የተባበሩት መንግሥታት ፕሬዚዳንት ኪም የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች እንዳይገነቡ ለማድረግ የገንዘብ ምንጫቸውን ለማድረቅ አገራት የሰሜን ኮሪያ ሠራተኞችን እንዳይቀጥሩ እገዳ ጥሏል።
በዚህም የተነሳ በርካታ አገራት ሰሜን ኮሪያውያን ሠራተኞቹን ወደ አገራቸው መለሱ።
ሆኖም ባለፈው ዓመት ከ10 ሺህ የሚበልጡ የጉልበት ሠራተኞች ወደ ሩሲያ መላካቸውን ቢቢሲ ስማቸው እንዳይጠቀስ ከጠየቁ የደቡብ ኮሪያ የደኅንነት ባለሥልጣን ሰምቷል።
በዚህ ዓመትም ተጨማሪ ሠራተኞች ሩሲያ ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ እና በአጠቃላይ ወደ 50 ሺህ ሠራተኞች ዕቅድ መያዙን እኚሁ ባለሥልጣን ይናገራሉ።
አብዛኞቹ በትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች የተሰማሩ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በአልባሳት ፋብሪካዎች እና በአይቲ ማዕከላት መመደባቸውን ገልጸው ይህም የተባበሩት መንግሥታት የሰሜን ኮሪያ ሠራተኞችን በሌሎች አገራት ስምሪት ላይ የጣለውን ማዕቀብ የጣሰ ነው።
የሩሲያ መንግሥት አሃዝ ባለፈው ዓመት 13 ሺህ ሰሜን ኮሪያውያን ወደ አገሪቱ መግባታቸውን ያሳየ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት በ12 እጥፍ ጭማሪ ያሳየ ነው።
ከእነዚህ መካከል 8 ሺህ የሚሆኑት ወደ ሩሲያ የገቡት በተማሪ ቪዛ ሲሆን፣ ይህ እንደ ደኅንነት ባለሥልጣኑ እና ባለሙያዎቹ ከሆነ የተባበሩትን መንግሥታት እገዳ ለማለፍ ሩሲያ የምትጠቀምበት ነው።
ሰኔ ወር ላይ የሩሲያ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሰርጌይ ሾይጉ በዩክሬን ኃይሎች ተይዞ የነበረውን ኩርስክ ግዛት እንደገና ለመገንባት 5 ሺህ ሰሜን ኮሪያውያን እንደሚላኩ ለመጀመሪያ ጊዜ አምነዋል።
"ሩሲያ በአሁኑ ወቅት ከባድ የሰው ኃይል እጥረት ገጥሟታል። ሰሜን ኮሪያውያን ይህንን ክፍተት እየሞሉ ነው። ርካሽ እንዲሁም ታታሪ ናቸው፤ ችግር ውስጥ አይገቡም" ሲሉ በሴዑል የኩክሚን ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት አንድሬይ ላንኮቭ ይገልጻሉ።
እነዚህ የባሕር ማዶ የግንባታ ሥራዎች በሰሜን ኮሪያ ካለው ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ክፍያ ነው በሚል እሳቤ በርካቶች ይፈልጉታል።

በርካቶች ከድህነት ለመውጣት እና ለቤተሰቦቻቸው የተሻለ ሕይወት ለማምጣት ተስፋን ሰንቀው ነው የሚያመሩት።
በጣም የታመኑ ወንዶች እና ያለውን ጥብቅ ማጣሪያ ያለፉ ናቸው ለእነዚህ ሥራዎች የሚመለመሉት።
ቤተሰቦቻቸውንም ይዘው መምጣት አይችሉም። ሆኖም አብዛኛው ገቢያቸው "የታማኝነት ክፍያ" በሚል በቀጥታ ወደ ሰሜን ኮሪያ ነው የሚላከው።
ቀሪው ከ100 አስከ 200 ዶላር የሚሆነው አነስተኛ ገንዘባቸው ይቀመጥላቸዋል።
ሠራተኞቹ ይህንን ገንዘብ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ብቻ ነው የሚሰጣቸው።
ይህም ከዚህ ስፍራ አምልጠው እንዳይሄዱ በቅርብ ጊዜ እየተደረገ ያለ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ወንዶቹ የጉልበት ሠራተኞች የከፋውን የሥራ ሁኔታ እና ደመወዝም ሳያገኙ ሲቀሩ ሁኔታው ሰባሪ ይሆንባቸዋል።
ታኤ ሌሎች እንደሚለው ከመካከለኛው እስያ የመጡ ሌሎች የግንባታ ሠራተኞች ከእሱ በአምስት እጥፍ በልጦ እንደሚከፈላቸው ሲያውቅ "የእፍረት ስሜት ይሰማኛል" ይላል።
"አስገዳጅ የጉልበት ካምፕ ውስጥ እንዳለሁ፤ የእስር ቤት ስሜት አለው" ሲል ነው ሁኔታውን የሚያስረዳው።
ጂን በበኩሉ ሌሎች ሠራተኞች እንዴት ባሪያዎች ብለው ይጠሯቸው እንደነበር ሲያስታውስ አሁንም ተሳቆ ነው።
"እናንተ ወንዶች አይደላችሁም፤ መናገር የሚችሉ ማሽኖች ብቻ" እያሉ ይሳለቁ ነበር ይላል።
ሠራተኞቹ ብቻ ሳይሆን በአንድ ወቀት የጂን ሥራ አስኪያጅ ወደ ሰሜን ኮሪያ ሲመለስ ምንም ዓይነት ገንዘብ ላያገኝ እንደሚችል እና መንግሥት ሊወስደው ይችላል ብሎ ነገረው።
ከዚያም ከነበረበት የከፋ ሕይወት ለማምለጥ በአደጋም ቢሆን ማለፍ እንዳለበት ውሳኔ ላይ ደረሰ።
በደቡብ ኮሪያ ሠራተኞች ምን ያህል ደመወዝ እንደሚከፈላቸው የሚያሳዩ የዩቲዩብ ቪዲዮዎችን ከተመለከተ በኋላ ታይ ሰሜን ኮሪያን ለመክዳት ወሰነ።
አንድ ቀን ምሽት ጓዙን በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ ሸክፎ የተኛ ለማስመሰል ብርድ ልብስ አልጋው ላይ ጎዝጉዞ ከግንባታው ስፍራ ሾልኮ ወጣ።
ወደ ደቡብ ኮሪያዋ መዲና ሴዑል የሚያደርገውን ጉዞ የሚያመቻችለትን የሕግ ባለሙያ ለማግኘት ታክሲ ተኮናትሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ተጓዘ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተወሰኑ ሠራተኞች ለሲጋራ እና ለአልኮል የሚሰጣቸውን አነስተኛ የቀን አበል በመቆጠብ የተከለከሉትን ሞባይል ከሰዎች በመግዛት ማምለጫቸውን ማመቻቸት ችለዋል።
የዶንግ ኤ ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ካንግ እንደሚሉት የሰሜን ኮሪያ አገዛዝ ሠራተኞቹን ለመቆጣጠር የሚሞክርበት አንደኛው መንገድ ተደጋጋሚ የርዕዮተ ዓለም ሥልጠና እንዲሁም ግለ ሂስ በማድረግ ለኪም ጆንግ ኡን ታማኝነታቸውን እንዲገልጹ እንዲሁም ስህተታቸውን እንዲናገሩ ይደረጋሉ።
ከግንባታው ስፍራዎች በወር አንዴ ይወጡ የነበረበት ሁኔታም መቋረጥ በሚባል ሁኔታ አንዳንዴ ብቻ እንደሆነም ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።
የሰሜን ኮሪያ ሠራተኞችን ከሩሲያ ካለው የከፋ ሁኔታ ለመታደግ የሚረዳው እና በሴዑል መቀመጫውን ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ኪም ሴውንግ ቹል "ሠራተኞቹ ከዚህ በፊት ሁለት ሆነው እንዲወጡ ይፈቀድላቸው ነበር፤ ነገር ግን ከአውሮፓውያኑ 2023 ወዲህ በአምስት ተቧድነው በከፍተኛ ቁጥጥር ነው የሚወጡት" ይላል።
ከዚህ የከፋ ቁጥጥር ማምለጥ የቻሉት ጥቂት ሠራተኞች ብቻ ናቸው።
በየዓመቱ ከሩሲያ ወጥተው ወደ ደቡብ ኮሪያ ሴዑል የሚሸሹ የሰሜን ኮሪያውያን ቁጥር ከ2022 ወዲህ በግማሽ የቀነሰ ሲሆን፣ በዚህም ከ20 ወደ አስር ወርዷል።















