በድብቅ ለምዕራባውያን ኩባንያዎች እየሠሩ ለመንግሥታቸው ገንዘብ የሚልኩ ሰሜን ኮሪያውያን የአይቲ ባለሙያዎች

ከሰሜን ኮሪያ ባንዲራ ፊት ለፊት ተቀምጦ ላፕቶፕ ላይ እየሰራ ያለ ኮፍያ ያደረገ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጂን ሱ ባለፉት ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሐሰተኛ መንነቶችን በመጠቀም በምዕራባውያን ኩባንያዎች ውስጥ ከርቀት የአይቲ ሥራ ለማግኘት ማመልከቱን ይናገራል።

ለሰሜን ኮሪያ መንግሥት ገንዘብ ለማሰባሰብ የተዘረጋው ስውር ዕቅድ አካል ነበር።

በዩናይትድ ስቴትስ እና በአውሮፓ ውስጥ ብዙ ሥራዎችን እያፈራረቀ የሠራው ጂን ሱ፣ በወር ቢያንስ 5,000 ዶላር ይከፈለው እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።

አንዳንድ ባልደረቦቹ ከዚህ ሻል ያለ ተጨማሪ ገቢ እንደሚያገኙ ይገልጻል።

ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረው ጂን ሱ፣ ከአገሩ ከመውጣቱ በፊት ወደ ቻይና፣ ሩሲያ ወይም ወደ አፍሪካ እና ሌሎች አገራት በምሥጢር ተልከው ሰሜን ኮሪያ በምታካሂደው ስውር ተግባራት ላይ ይሳተፉ ነበር ከሚባሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነው።

የሰሜን ኮሪያ የአይቲ ባለሙያዎች የቅርብ ክትትል የሚደረግባቸው ሲሆን፣ ወደ መገናኛ ብዙኃን ቀርበው አይናገሩም ጂን ሱ ግን ለቢቢሲ ሰፊ ምስክርነቶችን ሰጥቷል።

በዚህ ማጭበርበር ላይ የተሰማሩ ሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ምን እንደሚመስል እና አሠራራቸው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ መረጃን አጋርቷል።

የእሱ ምስክርነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የሳይበር ደኅንነት ሪፖርቶች ውስጥ የተቀመጡ አብዛኞቹን መረጃዎች ያረጋግጣል።

ከሚያገኘው ደመወዝ ውስጥ 85 በመቶው ለሰሜን ኮሪያ መንግሥት ድጋፍ እንደሚሰጥም ጨምሮ ገልጿል።

ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ያለባት ሰሜን ኮሪያ ለዓመታት የዓለም አቀፍ ማዕቀብ ተጥሎባታል።

"ዝርፊያ እንደሆነ እናውቃለን፤ ግን ዕጣ ፈንታችን ነው ብለን ነው የምንቀበለው" የሚለው ጂን ሱ አክሎም "አሁንም በሰሜን ኮሪያ ከነበርንበት ጊዜ በጣም የተሻለ ነው" ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በመጋቢት 2024 ላይ ባወጣው ሪፖርት ምሥጢራዊ የአይቲ ሠራተኞች ከ250 ሚሊዮን እስከ 600 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ያስገኛሉ።

ይህ የማጭበርበር ሥራ በተለይ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ ከቤት መሥራት የተለመደ በመሆኑ በስፋት የተዛመተ ሲሆን፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እየጨመረ መሆኑን ባለሥልጣናት እና የሳይበር መብት ተሟጋቾች ያስጠነቅቃሉ።

አብዛኛው ሠራተኛ ቋሚ ደሞዝ እየተከፈለው ወደ መንግሥት ለመላክ ነው የሚያስበው፤ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ የኩባንያዎቹን መረጃዎች ሰርቀው ወይም ጠልፈው አሠሪዎቻቸውን ገንዘብ የሚጠይቁም አሉ።

ባለፈው ዓመት የዩናይትድ ስቴትስ ፍርድ ቤት ለስድስት ዓመት ያህል የአሜሪካ ኩባንያዎችን በማጭበርበር እና በመበዝበዝ 88 ሚሊዮን ዶላር አግኝተዋል ያላቸውን 14 ሰሜን ኮሪያውያን ላይ ክስ መሥርቷል።

በአሜሪካ ለሚገኝ ክሪፕቶከረንሲ ኩባንያ ከርቀት የአይቲ ሥራን ለመሥራት ሐሰተኛ መታወቂያዎችን ተጠቅመዋል የተባሉ አራት ተጨማሪ ሰሜን ኮሪያውያን ባለፈው ወር ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ሥራውን ማግኘት

ጂን ሱ ከአገሩን ከመኮብለሉ በፊት በቻይና ውስጥ ለሰሜን ኮሪያ የአይቲ ሠራተኛ ነበር።

እሱ እና ባልደረቦቹ አብዛኛውን ጊዜ 10 ሆነው በቡድን እንደሚሠሩ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የኢንተርኔት አገልግሎት በሰሜን ኮሪያ የተገደበ ቢሆንም በውጭ አገር ግን እነዚህ የአይቲ ሠራተኞች በቀላሉ መሥራት ይችላሉ።

ዜግነታቸውን መደበቅ የሚያስፈልጋቸው ምዕራባውያንን በመምሰል የበለጠ ክፍያ ስለሚያገኙ ብቻ ሳይሆን፣ ሰሜን ኮሪያ በዋናነት በኒውክሌር ጦር መሳሪያዋ እና በባለስቲክ ሚሳኤል መረሃ ግብቶቿ የተነሳ በተጣለባት ሰፊ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ምክንያት ነው።

ይህ ዕቅድ ለአገሪቱ ገዥ አካል ገንዘብ ከሚሰበስቡት የሰሜን ኮሪያ የመረጃ መረብ ጠለፋ ሠራተኞች የተለየ ነው።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከሰሜን ኮሪያ እንደሚሠራ የሚታመነው ዝነኛ የመረጃ ጠለፋ ቡድን፣ ላዛሩስ፣ ምንም እንኳን ወንጀሉን ስለመፈጸሙ አምኖ ባያውቁም 1.5 ቢሊዮን ዶላር ከክሪፕቶፕ ባይቢት ኩባንያ እንደሰረቀ ይገመታል።

ላፕቶፕ ላይ እየሰራች ፈገግ ያለች ሴት፤ ሌላ ሴት ከአጠገቧ ተቀምጣ
የምስሉ መግለጫ, ቢቢሲ ጂን ሱን ከለንደን በቪዲዮ ነው ያነጋገረው። ለደኅንነቱ ሲባል ትክክለኛ ማንነቱ አልተገለጸም
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጂን ሱ አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው ሐሰተኛ ማንነቶችን ለማግኘት በመጣር ነው። ይህንንም ሥራ ለማመልከት ይጠቀምበታል።

መጀመሪያ ቻይናዊ ነኝ በማለት በሃንጋሪ፣ በቱርክ እና በሌሎች አገራት ያሉ ሰዎችን በማነጋገር በእነርሱ ማስረጃ ከሚያገኘው ገቢ በመቶኛ ለመክፈል እንደሚደራደር ለቢቢሲ ተናግሯል።

"በሥራ ማመልከቻ መዘርዝር ላይ 'የእስያዊ ገጽታ' ያለው ፎቶ ካደረግክ በጭራሽ ሥራ አታገኝም።"

ከዚያም በዚያ በብድር ባገኘው ማንነት ተጠቅሞ በምዕራብ አውሮፓ ያሉ ሰዎችን በመቅረብ ማንነታቸውን እንዲሰጡት እና አሜሪካ እና አውሮፓ ሥራ ለማግኘት እንዲገለገልበት ይጠይቃል።

ጂን ሱ ብዙውን ጊዜ በዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች ላይ ያደረገው ሙከራ ስኬት አስገኝቶለታል።

"በጥቂት ውይይት፣ በዩናይትድ ኪንግደም የሚኖሩ ሰዎች በቀላሉ ማንነታቸውን አሳልፈው ሰጥተውኛል" ብሏል።

የተሻለ እንግሊዝኛ የሚናገሩ የአይቲ ሠራተኞች አንዳንድ ጊዜ የማመልከቻውን ሂደት የተቀላጠፈ ይሆንል።

ነገር ግን በጊዜያዊነት በድረ ገጾች ላይ የሚሠሩ ሥራዎች የገጽ ለገጽ ቃለ መጠይቆች አያስፈልጋቸውም።

ስለዚህም ብዙ ጊዜ የዕለት ተዕለት ግንኙነቶች እንደ ስላክ (Slack) ባሉ መድረኮች ላይ ይካሄዳሉ። ይህም ያልሆኑትን ሰው ለመምሰል ቀላል ያደርገዋል።

ጂን ሱ ለቢቢሲ እንደገለፀው በአብዛኛው ጊዜ ትኩረት የሚያደርጉት በአሜሪካን ገበያ ላይ ነው።

"ምክንያቱም የአሜሪካ ኩባንያዎች ደሞዝ ከፍተኛ ነው" ብዙ የአይቲ ሠራተኞች ሥራ እያገኙ እንደነበርም ተናግሯል።

ብዙውን ጊዜ ኩባንያዎች ሳያውቁ ከአንድ በላይ ሰሜን ኮሪያዊ ይቀጥራሉ ያለው ጂን ሱ "ይህ ብዙ ጊዜ ይከሰታል" ሲል ያለውን ልምድ አጋርቷል።

የአይቲ ሠራተኞች ገቢያቸውን የሚቀበሉት በምዕራብ አገራት እና በቻይና በሚገኙ አመቻቾች በኩል እንደሆነ ይታወቃል።

ከሳምንት በፊት አንዲት አሜሪካዊት የሰሜን ኮሪያ የአይቲ ሠራተኞች ሥራ እንዲያገኙ በመርዳት እና ገንዘብ ከመላክ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ከስምንት ዓመት በላይ ተፈርዶባታል።

ቢቢሲ የጂን ሱን ምስክርነት ከገለልተኛ ወገን ሊያረጋግጥ አልቻለም።

ነገር ግን ለሰሜን ኮሪያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በሆነው ፒስኮር (PSCORE) በኩል፣ የጂን ሱን መረጃ የሚደግፍ ሌላ የአይቲ ሠራተኛ የሰጠውን ምስክርነት አግኝተናል።

ቢቢሲ ሂዩን ሴንግ ሊ የተባለ ሌላ ከመንግሥትን የኮበለለ ሰሜን ኮሪያዊ አግኝቶ በቻይና ውስጥ ነጋዴ መስሎ ለመንግሥት ሲሠራ በነበረበት ወቅት ተመሳሳይ ልምድ ያላቸው የአይቲ ባለሙያዎችን ማግኘቱን ገልጿል።

እርሱም ተመሳሳይ ገጠመኞች እንዳሏቸው አረጋግጧል።

እያደገ የመጣ ችግር

ቢቢሲ በሳይበር ደኅንነት እና በሶፍትዌር ዴቬሎፕመንት ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ በርካታ የቅጥር ኃላፊዎችን አነጋግሯል፤ እነሱም በቅጥር ሂደታቸው የሰሜን ኮሪያ የአይቲ ሠራተኞች ናቸው ብለው የጠረጠሯቸውን ብዙ አመልካቶች መለየታቸውን ተናግረዋል።

በአሜሪካ ውስጥ የአሊ ሴኪዩሪቲ መሥራች የሆኑት ሮብ ሄንሊ በቅርብ ጊዜ በድርጅታቸው ውስጥ ለተከታታይ የርቀት ክፍት የሥራ ቦታዎች ቅጥር እያከናወኑ ነበር።

እናም በሂደቱ እስከ 30 የሚደርሱ የሰሜን ኮሪያ የአይቲ ሠራተኞችን ቃለ መጠይቅ ማድረጋቸውን ያምናሉ።

"መጀመሪያ ላይ በተወሰነ ደረጃ እንደ ጨዋታ፣ ልክ ማን እውነተኛ እና ማን ሐሰተኛ እንደሆነ ለማወቅ መሞከር ነበር፣ ነገር ግን በጣም በፍጥነት የሚያናድድ ሆነ" ብለዋል።

በስተመጨረሻም አመልካቾቹን በቪዲዮ እንዲያናግሯቸው በመጠየቅ ባሉበት አገር ቀን መሆኑን ለማየት ሞከሩ።

"እኛ ለእነዚህ የሥራ መደቦች አመልካቾችን እየተቀበልን የነበረው ከአሜሪካ ብቻ ነው። ነገር ግን ሁሉም ነገር እንደጠበቅሁት አይደለም። ተስፋ የሚሰጥ ነገር አይቼ አላውቅም።"

በመጋቢት ወር ላይ ፖላንድ ውስጥ የሚገኘው የቪዶክ ሴኩሪቲ ላብ ተባባሪ መሥራች የሆነው ዳዊድ ሞክዛድሎ አመልካቾች ፊታቸውን ለመደበቅ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሲጠቀሙ የታዩበትን የሥራ ቃለ መጠይቅ ቪዲዮ አጋርቷል።

ከባለሙያዎች ጋር ከተነጋገረ በኋላ አመልካቹ የሰሜን ኮሪያ የአይቲ ሠራተኛ ሊሆን እንደሚችል ተጠራጥረዋል።

በዚህ ታሪክ ውስጥ ሰሜን ኮሪያውያንን በሚመለከት ለቀረቡት መረጃዎች ምላሽ ለማግኘት በለንደን የሚገኘውን የሰሜን ኮሪያን ኤምባሲ ብናነጋግርም ምላሽ አላገኘንም።

ከቪዲዮ ቃለ መጠይቅ ላይ የተወሰደ የስክሪን ሾት ምስል። ዳዊድ ሞክዛድሎ፣ የቪዶክ ሴኩሪቲ ላብ ተባባሪ መስራች አመልካችን ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ
የምስሉ መግለጫ, ጌት ሪል ሴኩሪቲ፣ ዲጂታል ፎረንሲክስ ኩባንያ፣ አመልካቹ (በስተግራ) የፊት መለወጫ ወይም የኤአይ ፊልተር እየተጠቀመ ሊሆን እንደሚችል ለቢቢሲ ተናግሯል

ለማምለጫ ያለ ብቸኛው መንገድ

ሰሜን ኮሪያ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሠራተኞችን ለአስርት ዓመታት ወደ ውጭ አገር ስትልክ ቆይታለች።

በአብዛኛው በቻይና እና በሩሲያ ውስጥ በአብዛኛው በፋብሪካ እና በሬስቶራንት ውስጥ እስከ 100,000 የሚደርሱ ሰሜን ኮሪያውያን ተቀጥረው ይሠራሉ።

ጂን ሱ በቻይና ውስጥ በርካታ ዓመታት ከኖረ በኋላ የማያላውስ የሥራ ሁኔታው ላይ "የመታሰር ስሜት" እያዳበረ መምጣቱን ይናገራል።

"እንድንወጣ አልተፈቀደልንም እና ሁልጊዜ ቤት ውስጥ መቆየት ነበረብን" አክሎም፣ "የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም፤ የምትፈልገውን ማድረግ አትችልም።"

ነገር ግን የሰሜን ኮሪያ የአይቲ ሠራተኞች ከአገር ውጪ በሚሆኑበት ጊዜ የምዕራባውያንን ሚዲያ የማግኘት የበለጠ ነፃነት እንዳላቸው ጂን ሱ ተናግሯል።

"የገሃዱ ዓለምን ታያለህ። ውጭ አገር ስንሆን በሰሜን ኮሪያ ውስጥ የሆነ ችግር እንዳለ እንገነዘባለን።"

ነገር ግን ይህ ቢሆንም፣ ጂን ሱ እንዳደረገው ለመጥፋት የሚያስቡት ጥቂት የሰሜን ኮሪያ የአይቲ ሠራተኞች ናቸው።

"ገንዘባቸውን ወስደው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው ስለ መኮብለል የሚያስቡት።"

ምንም እንኳን ከሚያገኙት ደመወዝ የሚሰጣቸው ትንሽ ቢሆንም፣ በሰሜን ኮሪያ ብዙ ዋጋ አለው። መኮብለልም በጣም አደገኛ እና ከባድ ነው።

በቻይና ውስጥ ክትትል ይደረጋል ማለት ብዙዎቹ ተይዘዋል ማለት ነው።

እነዚያ ጥቂቶች መኮብለል የቻሉ ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን ዳግመኛ ማየት አይችሉም፣ እና ዘመዶቻቸው በመኮብለላቸው ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል።

ጂን ሱ አሁንም በአይቲ ውስጥ እየሠራ ቢሆንም ከአገሩ ኮብልሏል። ለገዥው መንግሥት በሚሠራበት ወቅት ያካበተው ክኅሎት ወደ አዲስ ሕይወቱ እንዲገባ እንደረዳው ይናገራል።

ምክንያቱም ብዙ ሥራዎችን በሐሰት መታወቂያ እየሠራ አይደለም።

የሚያገኘው ለሰሜን ኮሪያ መንግሥት እየሠራ ከነበረበት ጊዜ ያነሰ ነው። ነገር ግን የሚያገኘውን ገንዘብ መቆጠብ ስለሚችል በአጠቃላይ በኪሱ ውስጥ ብዙ ገንዘብ አለው።

"ሕገ ወጥ ሥራዎችን በመሥራት ገንዘብ ማግኘት ለምጄ ነበር። አሁን ግን ጠንክሬ በመሥራት የሚገባኝን ገንዘብ አገኛለሁ።"