አጋሮቿ የተሽመደመዱባት ኢራን ከእስራኤል ጋር ወደለየለት ጦርነት ታመራ ይሆን?

የኢራን እስላማዊ አብዮት ዘብ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሆሴን ሳላሚ ወደ እስራኤል የሚወነጨፉ ወደ 200 የሚጠጉ የባላስቲክ ሚሳዔሎች እንዲምዘገዘጉ በስልክ ትዕዛዝ ለመስጠት በጦር ማዘዣ ክፍል ውስጥ ቆመው የሚታዩበት ምሥል በኢራን መገናኛ ብዙኃን ተሰራጭቷል።

የፎቶው ባለመብት, Iranian state television

የምስሉ መግለጫ, የኢራን እስላማዊ አብዮት ዘብ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሆሴን ሳላሚ ወደ እስራኤል የሚወነጨፉ ወደ 200 የሚጠጉ የባላስቲክ ሚሳዔሎች እንዲምዘገዘጉ በስልክ ትዕዛዝ ለመስጠት በጦር ማዘዣ ክፍል ውስጥ ቆመው የሚታዩበት ምሥል በኢራን መገናኛ ብዙኃን ተሰራጭቷል።

የኢራን እስላማዊ አብዮት ዘብ ጓድ (አይአርጂሲ) ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሆሴን ሳላሚ ወደ እስራኤል የሚወነጨፉ ወደ 200 የሚጠጉ የባላስቲክ ሚሳዔሎች እንዲምዘገዘጉ በስልክ ትዕዛዝ ለመስጠት በጦር ማዘዣ ክፍል ውስጥ ቆመው የሚታዩበት ምሥል በኢራን መገናኛ ብዙኃን ተሰራጭቷል።

በተጨማሪም ጄኔራሉ ከሌሎች የጦር አመራሮች ጋር ሆነው ከተነሱት ፎቶግራፍ ጀርባ ሌላ ትልቅ ባነር ግድግዳው ላይ ተሰቅሎ ይታያል።

የጥቃቱ ዓላማ በባነሩ ላይ የሚታዩ ሰዎችን ግድያ ለመበቀል ነው። የሐማሱ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሃኒያህ ቴህራን ውስጥ ባለፈው ሐምሌ ወር ሲገደሉ ኢራን እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋለች።

ባለፈው ሳምንት እስራኤል በቤይሩት ባደረገችው የአየር ጥቃት የተገደሉት የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህ እና አብዮታዊው ዘብ ቁድስ ብርጌድ የዘመቻ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አባስ ኒልፎሮሻን ናቸው በባነሩ ላይ የሚታዩት።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ እንደገለጸው ከሆነ እስራኤል ለመድረስ 12 ደቂቃ የፈጀባቸው ፋታህ የተሰኙ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎችን ጭምር በጥቃቱ ላይ ጥቅም ላይ ውለዋል። ሦስት የእስራኤል አየር ማረፊያዎችን እና የሞሳድ የስለላ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤትን ጨምሮ ዒላማቸውን በተሳካ ሁኔታ መምታታቸውንም አስታውቋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) ግን አብዛኞቹ ሚሳዔሎች “በእስራኤል እና በዩናይትድ ስቴትስ በሚመራው የመከላከያ ጥምረት” አንዲከሽፉ ተደርገዋል ብሏል። በመካከለኛው እና በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ “አነስተኛ ጥቃቶች” እንደነበሩ ግን አልሸሸገም።

ከጥቃቱ በኋላ ቴህራን በሚገኘው የፍልስጤም አደባባይ ላይ በዳዊት ኮከብ ቅርጽ ወደተሠሩ ሕንጻዎች ሚሳዔሎች ሲምዘገዘጉ እና “የፅዮናዊነት ፍጻሜ መጀመሪያ” የሚል ጽሑፍ የያዘ ትልቅ ባነር ተሰቀለ።

ከሐማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒያህ ግድያ በኋላ ኢራን ነገሮችን ለማርገብ የምትፈልግ ይመስል ነበር። የኢራን የቅርብ አጋር በሆነው ሄዝቦላህ ላይ እስራኤል ተከታታይ አሰቃቂ ድብደባ መፈጸሟ የአጸፋ ምላሽ ላልወሰደችው ቴህራን የውርደት ምንጭ ሆነ።

በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ አብዮታዊው ዘብ ሄዝቦላህ እንዲመሠረት ድጋፍ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ቡድኑ ሊባኖስ ውስጥ ከፍተኛ የጦር ኃይል ያለው እና ወሳኝ የፖለቲካ ተዋናይ እንዲሆን የኢራን መሳሪያዎች፣ ሥልጠና እና የገንዘብ ድጋፍ ወሳኝ ሚና ነበራቸው።

ከጥቂት ወራት በፊት የኢራን መሪዎች በጋዛ ከሐማስ ጋር ጦርነት ውስጥ የምትገኘው እስራኤል፤ ከሄዝቦላህ ጋር ወደ ግጭት ካመራች ትዳከማለች የሚል ሃሳብ ነበራቸው።

እስራኤል በአገራቸው የኒውክሌር እና የሚሳዔል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንዳትፈጸም የሄዝቦላህ ግዙፉ ሮኬቶች እና ሚሳኤሎች ትልቅ መከላከያ ሆኖ እንደሚያገለግላቸው ይተማመኑም ነበር።

እስራኤል ኢራንን ወደ ክልላዊ ጦርነት ከማስገባት ባለፈ ከአሜሪካ ጋር ልታጋጫት እየሞከረች ነው ሲሉ በሐምሌ ወር የተመረጡት ፕሬዝደንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ከሰዋል።

ረቡዕ ዕለት ኳታርን በጎበኙበት ወቅት “እኛም ደኅንነት እና ሠላም እንፈልጋለን። ቴህራን ውስጥ ሃኒያህን የገደለችው እስራኤል ነች” ማለታቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

“አውሮፓውያን እና አሜሪካኖች እርምጃ እስካልወሰድን ድረስ በአንድ ሳምንት ውስጥ በጋዛ ሰላም ይሰፍናል ይላሉ። ሰላም እንዲመጣ ብንጠብቀም ግን ግድያው እየጨመረ ነው” ብለዋል።

ከኢራን ጥቃት በኋላ ቴህራን በሚገኘው የፍልስጤም አደባባይ በዳዊት ኮከብ ቅርጽ ወደተሠሩ ሕንጻዎች ሚሳዔሎች ሲምዘገዘጉ እና “የፅዮናዊነት ፍጻሜ መጀመሪያ” የሚል ጽሑፍ የያዘ ትልቅ ባነር ተሰቅሏል

የፎቶው ባለመብት, Wana/Reuters

ወግ አጥባቂዎች

በኢራን የሚገኙ በርካታ ወግ አጥባቂዎች አገሪቱ በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ ባለማውሰዷ በጣም እየተጨነቁ ነበር።

በጠቅላይ መሪው በአያቶላ አሊ ኻሜኒ እና በአብዮታዊው ዘብ ቁጥጥር ሥር በሚገኘው መንግሥታዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የሚቀርቡ በርካታ ተንታኞች ለሃኒያህ ግድያ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ አለሞመከሩ የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ከማግዘፍ ባለፈ በሊባኖስ የሚገኙ የኢራንን ጥቅሞች እና አጋሮችን እንዲያጠቁ አበረታቷል ሲሉ ተከራክረዋል።

የኢራን ጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ባኬሪ ከማክሰኞው የሚሳዔል ጥቃት በኋላ “የመታገስ” ጊዜ ማብቃቱን ተናግረዋል።

“በእስራኤል የሚገኙ ወታደራዊ እና የስለላ ተቋማትን ሆን ብለን ዒላማ በማድረግ የኢኮኖሚ እና የኢንዱስትሪ አካባቢዎችን ከመምታት ተቆጥበናል። እስራኤል የአጸፋ ምላሽ የምትሰጥ ከሆነ ግን የእኛ ምላሽ የበለጠ ጠንካራ ይሆናል ” ብለዋል።

የሚሳኤል ጥቃቱ ከእስራኤል ጥቃት በኋላ የኢራን መሪዎች ዝም ማለታቸው አጋሮቻቸው በሆኑት በሄዝቦላህ እና በሐማስ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በተቀረው ዓለምም እንደ ደካማ እና ተጋላጭ እንዳያስቆጥራቸው ስጋት መኖሩን ያሳያል ተብሏል።

“የእጅ ዙር ጦርነት”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢራን እና እስራኤል ለብዙ አሥርተ ዓመታት የእጅ አዙር ጦርነትን መርጠዋል። “ጦርነትም ሠላምም የሌለበት” ፖሊሲን ተከትለዋል። ይህ አካሄድ ግን የሚያበቃ ይመስላል።

እስራኤል ጠንከር ያለ ምላሽ ለመስጠት ዝታለች።“ኢራን ትልቅ ስህተት ሠርታለች ለዚህም ዋጋ ትከፍላለች” ሲሉ ኔታንያሁ አስጠንቅቀዋል።

ከአሜሪካ በኩልም የድምጸት እና የስትራቴጂ ለውጥ ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው።

እስራኤል በሶሪያ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ጽህፈት ቤት ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት በርካታ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዦች መገደላቸውን ተከትሎ ቴህራን የአጸፋ ምላሽ ሰጥታለች።

በዚህም ወደ እስራኤል ከተተኮሱት 300 ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳዔሎች ውስጥ አብዛኞቹ በእስራኤል እና በአሜሪካ ጥምረት መክሸፋቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ባይደን ሁለቱም ወገኖች ግጭቶችን ከማባባስ እንዲታቀቡ ጠይቀዋል። እስራኤል የአሜሪካን ጥሪ ብትቀበልም በፈጸመችው የአጸፋ ጥቃት በማዕከላዊ ኢራን የአየር መከላከያ ምድብን በሚሳዔል መትታለች።

አሁን ግን የባይደን ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን የኢራን ጥቃት “ከባድ መዘዝ” እንደሚኖረው ገልጸው፤ ዩናይትድ ስቴትስ “ከእስራኤል ጋር እንደምትሠራ” አስጠንቅቀዋል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የእስራኤል ባለሥልጣናትን በመጥቀስ ረቡዕ ዕለት እንደዘገቡት ከሆነ እስራኤል በኢራን ላይ “በቀናት ውስጥ” አጸፋዊ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀች ትገኛለች። በዚህም የአገሪቱን አስፈላጊ የነዳጅ ማውጫዎችን ጨምሮ “ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን” ዒላማ ይደርጋሉ ብለዋል።

የኢራን የኒውክሌር ተቋማትም በእስራኤል ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሥልጣናቱ አስጠንቅቀዋል።

የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ተጨማሪ ጥቃት እስካልተፈጸመ ድረስ ለሃኒያህ፣ ለናስራላህ እና ለኒልፎሮሻን ግድያ በሚል የወሰዱት አጸፋ ምላሾች ማብቃታቸውን አስረግጠው ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ በበኩላቸው ቴህራን በሚገኘው የስዊዘርላንድ ኤምባሲ በኩል አሜሪካ “ጣልቃ እንዳትገባ” የሚያስጠነቅቅ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል።

“እስራኤልን የሚረዳ ወይም የአየር ክልሉን በመፍቀድ በኢራን ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የፈቀደ ሦስተኛ አገር እንደ ሕጋዊ ዒላማ ይቆጠራል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ አገራት ውስጥ አሏት። አብዛኞቹም በኢራቅ እና በሶሪያ ተሰማርተው ይገኛሉ። በሁለቱም አገራት የሚገኙት ወታደሮች በኢራን በሚደገፉ የሺዓ ሚሊሻዎችን ዒላማ ሊደረጉ ይችላሉ።

ኢራን የራሷን እርምጃ አጠናቃ የእስራኤልን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ስትሆን እየሞከረችው ያለው የቁማር አይነት ግምት ፍሬያማ እንደሚሆን ተስፋ ታደርጋለች።