ትንታኔ፡ ከኢራን የሚሳዔል ጥቃት በኋላ የእስራኤል ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?

ኢራን ወደ እስራኤል የተኮሰቻቸው ሚሳኤሎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    • ፀሐፊ, ጄሬሚ ቦዌን
    • የሥራ ድርሻ, የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አርታዒ

ኢራን ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር እስራኤል ላይ ጥቃት ስትፈጽም ቀድማ ማስጠንቀቅያ ሰጥታ ስለነበር የእስራኤል እና የአሜሪካ መከላከያ ኃይሎች የተተኮሱትን ሚሳኤሎች ማምከን ችለው ነበር።

አሁን ግን የሆነው ከዚያ የተለየ ነው፤ ኢራን በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ የፈለገች ሲሆን፣ ጥቃቱንም ሙሉ በሙሉ ቁጣ በተቀላቀለበት መልኩ ነበር የፈጸመችው።

የኢራን እስላማዊ አብዮት ዘብ ጥቃቱን የፈጸመው በሐማስ እና በሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራሮች መገደል የበቀል ስሜት ተነሳስቶ መሆኑን ጠቅሶ እስራኤል የመልስ ምት እሰጣለሁ ካለች ዳግም ጥቃት እንደሚጠብቃት ዝቷል።

ከዚህ ቀደም ኢራን ወደ እስራኤል ሚሳዔል ስታስወነጭፍ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለቤንያሚን ኔታኒያሁ “በቃ” በማለት ምላሽ መስጠት አይገባም በማለት ውጥረቱን እንዲያረግቡ ምክር የሰጡ ሲሆን፣ እስራኤልም ምክሩን የተቀበለች ይመስል ነበር።

አሁን ግን በእስራኤል ያለው የመጠቃት መንፈስ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ ነው።

የእስራኤል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ማክሰኞ [ትናንት] ማታ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጠንከር ያለ መልዕክት አስፍረዋል።

“የመካከለኛው ምሥራቅን ገጽታን ለመቀየር በ50 ዓመታት ውስጥ የተገኘ ድንቅ ዕድል ነው” በማለት እስራኤል የኢራንን ኑክሌር ተቋማት፣ “አሸባሪውን መንግሥት ክፉኛ ለማሽመድመድ” ማጥቃት አለባት ሲሉ ተናግረዋል።

ምንም እንኳ ቤኔት በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ባይሆኑም ወደፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሎ ስለሚታመን አይበገሬ አቋም እንዳላቸው ለማሳት የፈለጉ ይመስላል።

ከዚያም ባሻገር በአሁኑ ወቅት በእስራኤል ኢራንን በሚመለከት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን መንፈስም ያሳያል።

በአሁኑ ወቅት እስራኤል በኢራን የኑክሌር ተቋማት፣ ፔትሮኬሚካል እንዲሁም የኢራን ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ጥቃቶችን ልትፈጽም እንደምትችል ይጠረጠራል።

ኢራን በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰውን ሄዝቦላህ በመደገፍ ከፊት የተሰለፈች ናት። በዚህም የተነሳ አማጺ ድርጅቱ ከባድ እና ውስብስብ የጦር መሳሪያዎችን ለመታጠቅ በቅቷል።

እስራኤል ኢራን እና የኑክሌር ተቋማቷ ላይ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ እነዚያን መሳሪያዎች ሊጠቀም ይችላል ተብሎ ይሰጋል።

ነገር ግን ባለፉት ሁለት ሳምንታት እንደታየው እስራኤል የሄዝቦላህን አሽመድምዳዋለች።

እንደ አሜሪካ እና እስራኤል ባለሥልጣናት ከሆነ የሄዝቦላህን ከግማሽ በላይ የሚሆን ጦር መሳሪያ በአየር ጥቃት አውድማለች፣ ወደ ሊባኖስም ሰርጋ ገብታለች።

እስራኤል ከፍተኛ ጉዳት እያጋጠማትም እንኳ ቢሆን ኢራንን ዝም ትላለች ብሎ ማንም አይጠብቅም።

ስለዚህ እስራኤል ጥቃቱን ለመፈጸም በማንኛውም ሰዓት ልትነሳ ትችላለች።

ጆ ባይደንም ለኢራን እስራኤልን ነካችሁ ማለት አሜሪካንን እንደነካችሁ ቁጠሩት ሲሉ የአጋርነት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለዚህም ነው በቀጠናው የሚኖሩ ዜጎች ጦርነቱ፣ አለመረጋጋቱ እንዲሁም ያንን ተከትሎ የሚመጣው ቀውስ ሁሉ ሊራዘም እና ሊስፋፋ ይችላል ሲሉ የሚሰጉት።

ከዚያም ነገሮች ከተወሳሰቡ በኋላ በዲፕሎማሲ ለመፍታት ያለው ዕእድል የሰለለ ይሆናል ሲሉ ስጋታቸውን ያጠናክራሉ።