እስራኤል እና ሄዝቦላህ ሊባኖስ ውስጥ ፊት ለፊት ውጊያ መግጠማቸውን አሳወቁ

የእስራኤል አየር ኃይል በሊባኖስ ጥቃት ካደረሰ በኋላ

የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ ከሄዝቦላህ ታጣቂዎች ጋር “በቅርብ ርቀት እየተዋጋ” መሆኑን አስታወቀ።

ሄዝቦላህ በበኩሉ ወደ ሊባኖስ ድንበት “ሰርገው ከገቡ” የእስራኤል ወታደሮች ጋር ውጊያ መግጠሙን አረጋግጧል።

የሊባኖስ ጦር እስራኤል የሁለቱን አገራት ድንበር አልፋ መግባቷን ገልጿል።

ጦሩ በመግለጫው ላይ እስራኤል ብሉ ላየን ተብሎ የሚታወቀውን እና የተባበሩት መንግሥታት ቅኝት ሚያደርግበትን የጎላን ተራሮችን ከሊባኖስ የሚለየውን አካባቢ አልፋ በደቡባዊ ሊባኖስ 400 ሜትሮችን ዘልቃ መግባቷን ተናግሯል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በመግለጫው በደቡባዊ ሊባኖስ “በበርካታ አካባቢዎች” ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጿል።

የእስራኤል የምድር ጦር ከአየር ኃይሉ ጋር በጥምረት በመሆን “ሽብርተኞችን እንዲሁም የሽብርተኞች መሠረተ ልማቶችን” አውድመዋል ብሏል።

አክሎም “ከ150 በላይ መሠረተ ልማቶች” በአየር ጥቃቱ መውደማቸውን ገልጿል።

ሄዝቦላህ በበኩሉ ወደ ሊባኖስ ከተማ ማሮን አል ራስ ሰርገው ከገቡ የእስራኤል ወታደሮች ጋር ውጊያ መግጠሙን ተናግሯል።

ከተማዋ ከእስራኤል እና ከሊባኖስ ድንበር 2 ኪሎ ሜትር ብቻ የምትርቅ ናት።

እንደ ሄዝቦላህ መግለጫ ከሆነ የእስራኤል ወታደሮች በምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በኩል የገቡ ሲሆን፣ የሚደረገው ውጊያ ቀጥሏል።

ሄዝቦላህ ከዚህ ቀደም ወደ ሊባኖስ ሊገባ ያለውን የእስራኤል እግረኛ ጦር እንዲመለስ ማድረጉን ጠቅሶ ነበር።

የሊባኖስ ብሔራዊ የዜና ወኪል ኤንኤንኤ በበኩሉ አገሪቱ ከእስራኤል ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ በምትገኝ ደበል የተሰኘች መንደር ላይ ዛሬ ረቡዕ ጠዋት በተፈጸመ የአየር ጥቃት ሦስት ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል።

አክሎም አንድ ሰው እንዲሁ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በምዕራብ ቤካ ሸለቆ አካባቢ በተፈፀመ የአየር ጥቃት ሞቷል።

የሊባኖስ መከላከያ በበኩሉ ከትናንት ማክሰኞ ምሽት ጀምሮ በደቡባዊ ቤይሩት የአራት ሰዎችን አስከሬን ሲያነሳ 40 ሰዎች ደግሞ ተጎድተው ሕክምና አንዲገኙ ማድረጉን ገለጿል።

ጦሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈረው መግለጫ ላይ የእስራኤል ጦር የሊባኖስን ድንበር አልፎ 400 ሜትር ያህል ከዘለቀ በኋላ “ከጥቂት ቆይታ በኋላ ተመልሶ ወጥቷል” ብሏል።