በናይጄሪያ የሸሪዓ ፖሊስ የስፖርት ውርርድ ቤቶችን በዘመቻ ዘጋ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሰሜናዊ ናይጄሪያ ካኖ አውራጃ፣ ካኑ ከተማ፣ የሸሪዓ ፖሊስ አቋማሪ የስፖርት ውርርድ ቤቶች ላይ ዘመቻ አካሄደ።
የሸሪዓ ፖሊስ ምክትል ኃላፊ ሙጃሂድ አሚኑዲን “በእስልምና ቁማር ክልክል ነው፤ ስለዚህ ቤቶቹ ዘግተናቸዋል” ብለዋል።
ይህ የሸሪዓ ፖሊስ ዘመቻ የተካሄደው ከሕብረተሰቡ እና ከነዋሪዎች ከፍተኛ ቅሬታ ለፖሊስ መቅረቡን ተከትሎ ነው።
በዚህ የመጀመሪያው ዙር ዘመቻ 30 የሚሆኑ የውርርድ ሱቆች ተዘግተዋል።
የሱቆቹ ባለቤቶች እና አቋማሪዎች ግን እስር አልገጠማቸውም። ሁለተኛ እንዳይለመዳቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ወደ ቤት ተሸኝተዋል።
“ሒስባህ” የሚል ስም ያለው የሰሜናዊ ናይጄሪያ የሸሪዓ ፖሊስ ከዚህ በኋላ እንዲህ ዓይነት ድርጊት እንደማይታገስ ዝቷል።
የካና አውራጃ ዋና ከተማ ካኖ ትባላለች። አብዛኛው ሕዝብ ሙስሊም ነው። በከተማዋ በዋናነት ሸሪዓ ሕግ ተግባራዊ ቢደረግም ዓለማዊ ሕግም ጎን ለጎን አብሮ ይሠራበታል።
በካኖ የቁማር ቤቶች እና ጭፈራ ቤቶች ክርስቲያኖች በሚበዙባቸው ሰፈሮች አገልግሎት መስጠት ይችላሉ።
ሆኖም ግን ሙስሊሞች ወደዚያ መሄድን ያዘወትራሉ ተብሎ ሲገመት በክርስቲያን ሰፈሮች የሚገኙ ቤቶች ላይም እርምጃ ሊወሰድባቸው ይችላል።
አሁን የውርርድ ቤቶች ዘመቻው ያተኮረው ግን ሙስሊሞች በሚኖሩበት ካኖ አካባቢ ብቻ ነው።
በናይጄሪያ የስፖርት ውርርድ ቤቶች በየአካባቢው በስፋት የሚገኙ ሲሆን፣ ግድግዳ ላይ ቴሌቪዥን በመስቀል ለተመልካች የፈረስ ግልቢያ እና የእግር ኳስ ውድድር እያሳዩ ደንበኞቻቸውን ያቋምራሉ።
የሸሪዓ ፖሊስ እንደሚለው ብዙዎቹ አቋማሪዎች ተግባራቸውን የሚፈጽሙት በድብቅ ነው። ከሥራ ፈቃዳቸው ውጪ በድብቅ ይህን ተግባር ያከናውናሉ ሲል ይከሳል።
“ብዙዎቹ ፍቃድ የተሰጣቸው ቪዲዮ ጌም ለማጫወት ቢሆንም በድብቅ ሲያቋቆምሩ ደርሰንባቸዋል” ብለዋል ምክትል ኃላፊው ሙጃሂድ።
የስፖርት ውርርድ ቤቶች በናይጄሪያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊ ተወዳጅነት ያተረፉ ሆነዋል።
ናይጄሪያ በሰሜናዊው ክፍል በብዛት ሙስሊሞች ሲኖሩ፣ የደቡብ ናይጄሪያ ሕዝቦች ደግሞ በብዛት ክርስቲያኖች ናቸው።
አሁን በናይጄሪያ ባለው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በርካታ ሰዎች ያላቸውን ትንሽ አንጡራ ሃብትም ቢሆን ያልፍልን ይሆናል ብለው በቁማር ለማጥፋት አይሳሱም ይላሉ ከዚያ አካባቢ የሚወጡ ዘገባዎች።
ይህን ተከትሎ በተለይ ወጣቶችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየመሩ ያሉ አቋማሪ ቤቶች እንዲዘጉ ከወላጆች ከፍተኛ ግፊት ሲደረግ ቆይቷል።
በቁማር ሱስ የተነሳ ተማሪዎች ትምህርት ቤት እያቋረጡ እንደሆነም ይነገራል።
የሸሪዓ ፖሊስ ምክትል ኃላፊ “በናይጄሪያ የተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ በእኛ ሃጥያት የመጣ ነው፤ በሌላ አነጋገር ፈጣሪ ቁማርን የመሰለ ሃጥያት እንዳንፈጽም እየነገረን ነው” ብለዋል።
በካኖ ሸሪዓ ሕግ ተግባራዊ መደረግ የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2000 ነበር። ይህን ተከትሎም ዝሙት፣ ስካር እና ቁማር መፈጸም ከፍተኛ ወንጀል ተደርጓል።












