በሊባኖስ ጦርነት ሲፋፋም የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ምን እየሠራ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል እና የሊባኖሱ ሚሊሻ ሄዝቦላህ ለአራት አስርት ዓመታት ሲናቆሩ ቆይተዋል። አለመስማማታቸው ሁለት መሠረታዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው።
እስራኤል ጎረቤቷ ሊባኖስ የከተመው ታጣቂ ቡድን ለኅልውናዬ አስጊ ስለሆነ ላጠፋው ይገባል ትላለች። ሄዝቦላህ ደግሞ እስራኤል መጥፋት አለባት በሚል ጥቃቶችን ይሰነዝራል።
በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ያለው ግጭት ባለፉት 11 ወራት ተጠናክሯል። በተለይ በድንበር አካባቢ ግጭቶች መሰማታቸው የዕለተ ዕለት ዜና ሆኗል።
ከአውሮፓውያኑ 2006 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እስራኤል ሊባኖስን ወርራለች። ይህ ሁሉ ሲሆን የሊባኖስ ጦር ሠራዊት የት ነው ያለው? የሚለው ጥያቄ መነጋገሪያ ሆኗል።
የአገሪቱ ጦር ኃይል በሊባኖስ ላይ እየደረሰ ያለውን ውድመት ለመከላከል ያደረገውስ ነገር አለ? ሲሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሊባኖስን የሚከላከለው ሄዝቦላህ ወይስ ሠራዊቷ?
የሊባኖስ ጦር ሠራዊት በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል የሚካሄደውን ግጭት ከዳር ሆኖ መመልከትን ይመርጣል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎች አገራት ሄዝቦላህን የሽብር ቡድን ነው ሲሉ ፈርጀውታል።
በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ አንድን አገር በተለይ ከጠላት መጠበቅ ያለበት ጦር ሠራዊቷ ነው። እስራኤል ደግሞ የሊባኖስ ጠላት ናት።
ነገር ግን የሊባኖስ ጦር እስራኤልን የሚዋጋበት አቅም ያለው አይደለም። አፈ-ሙዞቹ እስራኤልን ለመውጋት የተሳሉ አይደሉም።
የእስራኤል ጦር እስከ አፍንጫው የታጠቀ፤ ዘመናዊ እና የምዕራባዊያን እርዳታ የማይለየው ነው። ምዕራባዊያኑ በገንዘብ እና በጦር መሣሪያ የእስራኤል ጦርን ይደግፋሉ።
አሜሪካ ለእስራኤል ኅልውና አስጊ ናቸው ለሚባሉ ቡድኖች የትኛውም አገር ከባድ እና ዘመናዊ የሚባሉ የጦር መሣሪያዎች እንዳይሰጥ ወይም እንዳይሸጥ ታስጠነቅቃለች ሲሉ ነባር የጦር መኮንኖች ይናገራሉ።
በአውሮፓውያኑ 2020 መሐል ቤይሩት ላይ የፈነዳው የማዳበሪያ መጋዘን የሚዘነጋ አይደለም። በወቅቱ ሊባኖስ በምጣኔ ሀብት ቀውስ እየታመሰች ነበር። ይህ ፍንዳታ ለሊባኖስ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባታል።
ሊባኖስ ምጣኔ ሀብቷ ደቀቀ ማለት ጦር ሠራዊቷ ወገቡን የሚያጠናክርበት ገንዘብ የለውም ማለት ነው። ሠራዊቱ ነዳጅን ጨምሮ አስፈላጊ የሚባሉ አቅርቦቶችን መግዣ የሚሆን ገንዘብ የለውም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ለጦሩ የምታደርገው እርዳታ
ሄዝቦላህ ከእስራኤል እኩል አሜሪካ ጠላቴ ናት ይላል። የሊባኖስ ጦር ዋና ረጂ ደግሞ አሜሪካ ናት። እንዲያውም በአንድ ወቅት የሊባኖስ ጦር ሠራዊትን ደመወዝ የምትከፍለው ዋሺንግተን ነበረች።
ነገር ግን የአሜሪካ እርዳታ ተሽከርካሪ ለመግዛት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች እንዲሁም ትናንሽ የጦር መሣሪያዎችን ለመሸመት የሚሆን ነው። በተነፃፃሪው ለእስራኤል የምታደርገው እርዳታ በቁና የሚሰፈር ነው።
ታዛቢዎች እንዲህ ይላሉ። የሊባኖስ ጦር ብቻ ሳይሆን የሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትም ጦራቸው ደካማ ነው።
“የሊባኖስም ሆነ የሌሎች የአረብ አገራት ጦር ኃይል እስራኤልን መቋቋም የሚችል አቅም የለውም” ይላሉ በሊባኖስ የተባበሩት መንግሥታት ጊዜያዊ ጦር አባል የነበሩት ጄኔራል ሙኒር ሺሃዴ።
“የእስራኤልን ጦርነት መዋጋት የሚቻለው በሽምቅ ውጊያ ብቻ ነው። ልክ ጋዛ ውስጥ እንዳየነው ያለ።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጡረታ የወጡት የሊባኖስ ጦር ጄኔራል የነበሩት ኻሊል ኤል ሄሉ ደግሞ “የሊባኖስ ጦር ኃላፊነት በአገር ውስጥ መረጋጋት ማስፈን ነው። ምክንያቱም አገር ቤት ያለው ነገር በጣም ውስብስብ ነው። ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ የሄዝቦላህ ደጋፊ ሊባኖሳውያን የሊባኖስ ተቃዋሚ ወደ ሆኑ ሥፍራዎች እንዲፈናቀሉ መደረጉ የእርስ በርስ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል” ይላሉ።
የረዥም ጊዜ የሄዝቦላህ መሪ የነበሩት ሐሳን ናስራላህ በእስራኤል መገደላቸውን ተከትሎ የሊባኖስ ጦር የእርስ በርስ ግጭት ሊነሳ ይችላል ብሎ ባመነባቸው ሥፍራዎች ተሰማርቷል።
ጦሩ ባለፈው እሑድ ባወጣው መግለጫ ዜጎች “ብሔራዊ አንድነትን እንዲጠብቁ” አሳስቦ በአገሪቱ ሰላም ለማስጠበቅ ሲባል እርምጃ ሊወስድ እንደሚችልም አስጠንቅቋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሊባኖስ ጦር እስራኤልን እየተዋጋ ነው?
ጥያቄው የሊባኖስ ጦር አሁን እያየነው ባለው ግጭት ውስጥ እጁ አለበት ወይ? ከሆነ መልሱ በፍፁም የሚል ነው።
ቢሆንም የሊባኖስ ጦር በደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል በቁጥር ልቆ ሰፍሮ ይገኛል። ጦሩ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ አንድ የሊባኖስ ወታደር በእስራኤል የድሮን ጥቃት መገደሉን አስታውቋል። ወታደሩ በሞተር ብስክሌት እየሄደ ሳለ ነው በእስራኤል ድሮን የተገደለው።
ምናልባት ወደፊት በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስ የሊባኖስ ጦር ወደ ደቡብ ተጉዞ ድንበር ላይ መሥፈሩ አይቀርም። የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርቡ ሲናገሩ ይህን ጠቆም አድርገዋል።
ነገር ግን የሊባኖስ ጦር ድንበር ለመጠበቅ ተጨማሪ ኃይል ያስፈልገዋል። ገንዘብም ይፈልጋል። ነገር ግን ጦሩ ለጊዜው በጀት የለውም።








