ስለ እስራኤል- ሄዝቦላህ ግጭት እስከአሁን የምናውቃቸው

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሁለቱ ተዋጊዎች ወደ ሙሉ ጦርነት እየገቡ ይመስላል። ቀጠናዊ ግጭት ሆኖ ሊቀጥል ይችላል ወይ የሚለው አሁንም እያነጋገረ ነው።
እስራኤል ላለፉት ዘጠኝ ቀናት ደቡባዊ ሊባኖስ ላይ ቦምብ ስታዘንብ ነበር።
አሁን ደግሞ ‘ውስን፣ ዒላማውን እና ዓላማውን የለየ የእግረኛ ጦር ዘመቻ’ አካሄዳለው ብላለች።
ባለፈው ዓርብ መሪው የተገደለበት ሄዝቦላህ አጣብቂኝ ውስጥ ይገኛል። ይሁንና አሁንም ሄዝቦላህ ተዳከመ እንጂ ጨርሶ አልተደመሰሰም።
አሁንም ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ያስወነጭፋል። በርካታ ኮማንደሮቹ ተለቅመው የተገደሉበት ድርጅት አልሞት ባይ ተጋዳይ የሆነ ይመስላል።
የእግረኛ ጦር ዘመቻ
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ወደ ሊባኖስ እግረኛ ሠራዊት ዘመቻ መክፈቱን ይፋ አድርጓል። ይህ ሲጠበቅ የነበረ ነው።
ይሁንና ዘመቻው መላው ሊባኖስን የሚያካልል አይሆንም። ድንበር አካባቢ የሚገኙ በይበልጥ በሄዝቦላህ ቁጥጥር ሥር የነበሩ አካባቢዎችን የማጽዳት ሥራ ይሠራል ነው ያለው።
መከላከያ ዘመቻው መጀመሩን ከመግለጹ አስቀድሞ በርካታ ታንከኛ ሠራዊት በድንበር ተሰልፎ ሲጠባበቅ ታይቷል።
የዘመቻው ዓላማ በድንበር አካባቢ ከጦርነት ቀጠና ውጪ የሆነ አካባቢን መፍጠር ነው። ከዚያ በኋላ በሰሜን እስራኤል የተፈናቀሉ 60 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎችን ወደ ቀያቸው መመለስ ነው።
እነዚህ ዜጎች ለአንድ ዓመት ያህል ወደ ሌላ ሥፍራ እንዲሄዱ ተደርጎ ነው የቆዩት።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የተወሰኑ የእስራኤል ኮማንዶዎች ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ ገብተው እንዳንድ “የማጽዳት ሥራዎችን” አከናውነዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሐሳን ናስራላህ መገደል፡ የእስራኤል ትልቅ ድል
እስራኤል መጀመርያ ፔጀር በተሰኘ የመስክ ራዲዮ መገናኛ፣ ቀጥሎ ደግሞ በዎኪቶኪ የተጠና ጥቃት በሄዝቦላህ አባላት ላይ አደረገች። ይህን ተከትሎ ነው የአየር ዘመቻው የቀጠለው።
በእነዚህ አጭር ቀና ውስጥ ብቻ በወሰደችው እርምጃ ሄዝቦላህ በከፍተኛ ሁኔታ ተሽመድምዷል።
የቢቢሲ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ አርታዒ ጄቴሚ ቦዊን “ለሄዝቦላህ ትልቁ ኪሳራ የመሪው ሐሳን ናስራላህ መገደል ነው” ይላል።
ከ30 ዓመታት በላይ ናስራላህ የሄዝቦላህ የልብ ምት ሆኖ ነው የኖረው። በኢራን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ይህ ድርጅት እሰራኤል ለ22 ዓመታት ይዛው የነበረን የሊባኖስ ግዛት እንድትለቅ አስገድዷታል። ይህም በአውሮፓውያኑ 2000 የሆነ ነው።
ከዚያ ወዲህ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2006 ከእስራኤል ጋር ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ ገብቶ ነበር።
ሄዝቦላህ የእስራኤልን ግዙፍ ሠራዊት ማቆም የቻለ ኃይል ተደርጎ ነበር የሚታሰበው።
ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈው ዓርብ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባደረጉት ኃይል የተቀላቀለበት ስሜታዊ ንግግር አገራቸው እስራኤል ጠላቶቿን ታንበረክካለች ብለው ዝተው ነበር።
ከዚያው ከኒው ዮርክ በሰጡት ትዕዛዝም የሐሳን ናስራላህ መገደል ይፋ ሆነ።
የሊባኖሳዊያን መከራ
የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር እንዳለው ከሆነ በእነዚህ አጭር ቀናት ብቻ አንድ ሺህ ሰዎች ተገድለዋል።
ከሟቾቹ መካከል 87 የሚሆኑት ሕጻናት ሲሆኑ፣ 56 የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ነጂብ ሚካቲ እንደሚሰጉት ከሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
እስራኤል ዒላማ የማደርገው የሄዝቦላህን ወታደራዊ ጥቅሞች ነው ትላለች።
የሆስፒታል እማኞች እንደሚሉት ግን ሟቾች በብዛት ንጹሐን ናቸው።
ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ከሽፈዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሐሳን ናስራላህ መገደል አስደስቷቸዋል። ይሁንና እስራኤል በአካባቢው ያለውን ውጥረት ወደላቀ ደረጃ መውሰዷ የባይደን አመራር ጦርነቱን ለማቆም ሲያደርገው የነበረውን ጥረት ትርጉም አልባ አድርጎታል።
ጆ ባይደን በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካንን ጦር እያጠናከርኩ ነው ብለዋል። ፔንታገን ደግሞ ኢራን በአሜሪካ ወታደራዊ ዕዞች ላይ ምንም ዓይነት ትንኮሳ ከማድረግ እንድትቆጠብ አሳስቧል።
አሜሪካ ኔታንያሁ የሰላም ስምምነት እንዲፈርሙ ጫና ስታደርግ ብትቆይም እስራኤል ግን እጅ የምትሰጥ አልሆነችም። ከዋሺንግተን የሚመጡ የሰላም ጥሪዎችም ከዚህ ወዲህ ብዙም ትርጉም የሚሰጡ አይመስሉም።
ኢራንና ሄዝቦላህ ቀጣይ እርምጃ
የሄዝቦላህ ምክትል መሪ ናኢም ቃሳም ሰኞ ዕለት ንግግር አድርገዋል። ድርጅታቸው አሁን በእስራኤል ላይ እያደረገ ያለው የሮኬት፣የድሮንና የሚሳኤል ጥቃት “ከአቅማችን በጣም ትንሹ ነው’’ ብለዋል።
እስራኤል የእግረኛና ታንከኛ ጦሯን ስታስገባ ድሉ የኛ ይሆናል ሲሉም ፎክረዋል።
ሄዝቦላህ አሁንም በሺህ የሚቆጠሩ ተዋጊዎች አሉት። ብዙዎቹ በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የተዋጉና ልምድ ያላቸው ናቸው።
በጦር መሣሪያ ደረጃ አሁንም ሄዝቦላህ የርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎች አሉት። ቴሌ አቪቭ መድረስም ይችላሉ።
የቢቢሲ የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ ፍራንክ ጋርድነር ሔዝቦላህ እነዚህ መሣሪያዎች ሳይወድሙበት በፊት ጥቅም ላይ ሊያውላቸው ይችላል። ነገር ግን ይህን ካደረገ ከእስራኤል አጸፋው የከፋ ይሆንበታል።
የነስረላህ መገደል ኢራን በቀጠናው የፈጠረችው ‘’ተከላካይ ቀለበት’ (Axis of Resistance) እንዲሰበርባት ምክንያት ሆኗል።
ይህ ቀለበት ሶሪያን፣ ሄዝቦላህን እና የየመን ሁቲን የሚጨምር ነበር።












