የዓለም መሪዎች ቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ ያስጨነቃቸው ለምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት በኒው ዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከመድረክ ጀርባ ዲፕሎማቶች ያንሾኳሽካሉ።
አንድ ጉዳይ እንዳስጨነቃቸው መረዳት ይቻላል።
መጪው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ማን ይሆናል የሚለው ነው እንቅልፍ የነሳቸው።
ብዙ አገራት የውስጥም የውጭም ፖለቲካቸው ይነስም ይብዛ በአሜሪካ መጪው መሪ ላይ ይወሰናል።
ቻይና መጪው የአሜሪካ መሪ ማን ነው የሚለው እጅግ ያሳስባታል።የንግድ ታሪፍ፣ ቀጠናዊ ፍጥጫዎች፣ ታይዋን ስስ ብልቶቿ ናቸው።
ሩሲያ ትራምፕ እንዲመረጡላት የሚቻላትን ሁሉ እያደረገች ነው።እስከ ዛሬም ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም። በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን ፈሰስ አድርጋለች፤ የመራጩን አስተሳሰብ ለመቀየር።
ሩሲያ፣ አሜሪካውያን ለትራምፕ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ለማድረግ በራሷ ሚዲያ፣ በተጽእኖ ፈጣሪ አሜሪካውያን፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረኮች ሁሉ የተቻላትን ታደርጋለች።
ኢራን በበኩሏ የሩሲያ ወዳጅ ትሁን እንጂ ምርጫዋ ካማላ ሃሪስ ናቸው።
ኢራን፣ የትራምፕ መምጣት መጥፊያዋ ሊሆን እንደሚችል ስለምታምን ካማላ ሃሪስ እንዲመረጡ ሁሉን አቀፍ ጥረትን ታደርጋለች።
ትራምፕ እንዲያውም ኢራን ልታስገድላቸው እንደምትፈልግ ጠቆም አድርገው ያውቃሉ። ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለ ፓኪስታናዊም አለ።
ከእነዚህ የዓለም ቁልፍ አገራት ሌላ ሁሉም አገር ጥቅሙን ለማስጠበቅ በአቅሙ ይታትራል፤በቡድንም በግልም።
የአውሮፓ ኅብረት ትልቁ ነው። የትራምፕ መመረጥ ለአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ትልቅ መርዶ ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ ትራምፕ ለዩክሬን የሚደረገውን የቢሊዮን ዶላሮች እርዳታ አይደግፉም። ዋይት ሐውስን በረገጥኩ በነገታው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነትን አስቆማለሁ እያሉ ቃል ለመግባት አልፈሩም።
ዶናልድ ትራምፕ ሰሞኑን ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ጋር በኒው ዮርክ ተገናኝተው ነበር። “የዚህ ሰው አገር (ወደ ዘለንስኪ እየጠቆሙ) ብዙ መከራ ውስጥ እያለፈች ነው፤አንድ ነገር ማድረግ አለብን፣ ፑቲን ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን’’ ሲሉ ወደፊት ድርድር ሊኖር እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መልስ ዓለም እንዲህ በጦርነት ጭንቅ ውስጥ ወድቃ አታውቅም። ሊባኖስ ወደ ሙሉ ጦርነት ልትገባ ዳር ዳር እያለች ነው።
ፍልስጤም በከፊል ወደ ፍርስራሽነት ተቀይራለች። መካከለኛው ምሥራቅ ወደ ለየለት የማያባራ ጦርነት ሊገባ ይችላል የሚለው ፍርሃት ዛሬም ዓለምን እያቃዠ ነው።
በአፍሪካ እና በእስያ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል። ኑሮ ከብዷል። ስደት በርክቷል።
ይህ ሁሉ ተደማምሮ የዓለም መንግሥታት መፍትሄን ይሻሉ። የአሜሪካ መጪው ፕሬዝዳንት ማን ነው የሚለው ግን ብዙ ነገሮችን ይወስናል።ወይም ይወስናል ብለው ያምናሉ ብዙዎቹ ዲፕሎማቶች።
ዶናልድ ትራምፕ ለብዙዎቹ የዓለም አገራት ብዙም ደንታ ያላቸው አይመስልም። ፖሊሲያቸው ምንጊዜም አሜሪካንን ማስቀደም ነው።
እርግጥ ነው ይህ የሁሉም ፕሬዝዳንቶች ተግባር ነው፤ሊሆንም ይገባል። ነገር ግን ቸል የሚሏቸው አገራት በርካታ ናቸው።
አንድ ጎምቱ ዲፕሎማት ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ አሁን የምርጫ ወቅት ስለሆነ የትኛውም ዕጩ በእስራኤል ጋዛ ጦርነት ጉዳይ ብዙ ርቀት መሄድን አይፈልግም።
ነገሮች የሚለይላቸው መጪው ፕሬዝዳንት ማን እንደሆነ ሲታወቅ ብቻ ነው።
እኚህ ዲፕሎማት እንደሚያምኑት ቀጣዩ የዋይት ሐውስ ሰው በሚታወቅ ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚመጣው ሰላምም ሆነ ሌላ ጉዳይ እየጠራ . . . እየለየለት ይመጣል።
የቢቢሲ ዘጋቢ በኒው ዮርኩ ስብሰባ ላይ ያገኛቸው በርካታ ዲፕሎማቶች መታከት ይታይባቸው ነበር። ማንም ይምጣ ማን ከአሜሪካ ጋር ለመሥራት እንቸገራለን የሚሉ ብዙ ነበሩ።
እነዚህ ዲፕሎማቶች ከጉዳዩ ስሱነት የተነሳ ስማቸው እንዲገለጽ አይሹም።
“በካማላ እና በትራምፕ መካከል ብዙ ልዩነት አይታየኝም፤ ዓለምን ተመልከት - በሙሉ ቀውስ ውስጥ ነው።” ይላሉ አንድ የደቡብ እስያ አገር ዲፕሎማት።
እያሉ ያሉት ማንም ይምጣ ማን ቀውሱ ይቀጥላል ነው።
ሌሎች ዲፕሎማቶችም ይህን ስሜት ማንጸባረቃቸውን ቀጥለዋል።
አሜሪካ ለተቀረው ዓለም ያላት ቸልተኝነትን ያነሳሉ። ከቀውስ አትራፊነቷንም ያወሱ አሉ።
ስለዚህ በዋይት ሐውስ ማን መጣ ማን ሄደ ለተቀረው ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ምኑም አይደለም ብለው ያምናሉ።
አንድ ሌላ የአረብ ዲፕሎማት ደግሞ እንዲህ ይላሉ፤ “ከካማላ ይልቅ ትራምፕ እንዲህ ናቸው - ይህን ያደርጋሉ ብሎ ለመበየን የሚያስቸግሩ ሰው ናቸው። ያም ቢሆን ግን ዓለም አቀፍ ትብብሮች እየፈራረሱ መጥተዋል። ስለዚህ ማን መጣ ማን ሄደ ብዙም ለውጥ ላይኖረው ይችላል።”
ሌላ ዲፕሎማት ደግሞ እንደ ቀድሞው በአሜሪካ ምርጫ መጨነቅ አሁን የለም ይላሉ። ምክንያቱን ሲጠየቁ ደግሞ አጭር መልስ ይሰጣሉ። “አሁን እያንዳንዱ ቀን በቂ ጭንቀት ያለበት ዘመን ነው። እስከ አሜሪካ ምርጫ ድረስ የሚያቆይ ጭንቀት የለም” ይላሉ።
ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የሚያደርጉትን አይተናል የሚሉት ዲፕሎማቱ በቀጣይ ካሸነፉ ግን ሙሉ ትኩረታቸው በአገር ውስጥ ጉዳይ ላይ ይሆናል ይላሉ።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶም በዚሁ ጉዳይ አስተያየታቸውን ለቢቢሲ ሰጥተው ነበር።
ብዙም የተለየ ነገር እንደማይመጣ ነው የሚያስቡት። “ኬንያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ጥብቅ ነው። ማን መጣ ማን ሄደ የሚለው አይቀይረውም። ትራምፕ ዋይት ሐውስ ሳሉ ጥሩ ግንኙነት ነበረን። ከባይደንም ጋር እንደዚሁ። ግንኙነቱ ከአለት የጠነከረ ነው። በጋራ እሴት እና ጥቅም ላይ የተመሠረተ በመሆኑ አይናወጽም” ይላሉ።
በአውሮፓውያን ዘንድ ግን እንዲያ አይደለም የሚታሰበው። ማን ያሸንፋል የሚለው የሚያሳስባቸው በቀጥታ ነው።
በተለይ የትራምፕ ማሸነፍ ብዙ ነገሮችን ያበላሽባቸዋል። በአገር ውስጥ ቀኝ አክራሪዎችን የልብ ልብ ይሰጣል። ዓለም አቀፍ ግንኙነታቸውንም ያቆረፍደዋል።
አንድ ለረጅም ጊዜ በዲፕሎማትነት የሠሩ ጎምቱ አውሮፓዊ ዲፕሎማት “ካማላ ሃሪስ ብታሸንፍ ብዙዎቻችን የሰላም እንቅልፍ እንተኛለን” ሲሉ ነገሩን አጠቃለውታል።















