ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተሰረዘው ወልቂጤ ከተማ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

የፕሪሚዬር ሊጉ አክሲዮን ማሕበር እና የወልቂጤ አርማ

የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ከሊጉ መሰረዙን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስተዳዳሪ አስታውቋል።

ክለቡ ለ2017 የውድድር ዘመን የክለብ ላይሰንሲንግ (ፈቃድ) ምዝገባ እና ሌሎች የተቀመጡ መስፈርቶችን ባለማሟላቱ ከሊጉ መሰረዙ ተሰምቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማሕበር ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው ማብራሪያ አንድ ክለብ ለ2017 የውድድር ዘመን የክለብ 'ላይሰንሲንግ' ምዝገባውን ካከናወነ በኋላ የተቀመጡ መስፈርቶችን ስለማሟላቱ ምርመራ እንደሚደረግ ጠቅሷል፡፡

ያልተሟሉ መስፈርቶችን በመጥቀስ በተሰጠው ቀነ ገደብ እንዲያሟላ፣ የተላለፈውን ውሳኔ እስኪፈፅም ድረስም ከዝውውር እንቅስቃሴ ታግዶ ማስጠንቀቂያ ወይንም የገንዘብ ቅጣት እንደሚተላለፍበት አውስቷል፡፡

ወልቂጤ ከተማ ክለብ እስከ ቀነ ገደቡ ማብቂያ ለአገር ውስጥና የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ያልተከፈለ ውዝፍ ደሞዝ ከፍሎ ማጠናቀቁን የሚያሳይ ሰነድ ካለማቅረቡም በላይ የተጫዋቾች ዝውውር ሳያከናውን የውድድር ዓመቱ ተጀምሯል ይላል የአክሲዮን ማሕበሩ መግለጫ፡፡

መስከረም 8 የነበረው ቀነ ገደብ ካለፈ በኋላም በቅጣት ይህን መስፈርት ማሟላት ባለመቻሉ ከክለብ ላይሰንሲንግ በተጨማሪ በፊፋ የተጣለበት የዝውውር እገዳ ባለመነሳቱ ክለቡ ለሁለተኛው ሳምንት የፕሪሚየር ጨዋታም ተጫዋቾችን ማስመዝገብ ሳይችል ቀርቷል።

ወልቂጤ ከተማ በመጀመሪያው ጨዋታ ከመቻል ጋር የነበረውን መርሃ ግብር አላከናወነም።

በሁለተኛውም ሳንምት ጨዋታም ወልቂጤ ከተማ በወጣለት መርሐ ግብር መሠረት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታውን አለማድረጉን ሊጉ አስታውቋል።

በዚህም ምክንያት በእነዚህ ጨዋታዎች በፎርፌ እንዲሸነፍ መደረጉ ተገልጿል።

ወልቂጤ ከተማ በውድድር ዓመቱ ሁለት ጨዋታዎችን ፎርፌ በመስጠቱ ምክንያት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሰረዙን ነው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ ለቢቢሲ የተናገሩት።

የትኛውም ክለብ በአንድ ውድድር ዓመት ሁለት ጨዋታዎችን (በተከታታይም ሆነ በተለያዩ ጊዜያት) ሳይጫወት ለተጋጣሚው ፎርፌ ከሰጠ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ደንብ መሠረት ይሰረዛል ይላሉ።

ክለቡ በፌደሬሽኑም ሆነ በሊጉ እንደክለብ ቢመዘገብም ለመጫወት የሚያስፈልገውን መስፈርት አሟልቶ ሜዳ ላይ ባለመገኘቱ መሰረዙን አስታውቀዋል።

ክለቡ ከሊጉ መሠረዙን ተከትሎ በዘንድሮው ውድድር ዓመት የሊጉ መክፈቻ እና ሁለተኛ ጨዋታዎች ለመቻል እና ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተሰጠው የፎርፌ ውጤትም እንደሚሰረዝ ታውቋል።

የሊጉ ጨዋታዎችም በቀሪዎቹ 18 ቡድኖች እንደሚቀጥሉ አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል።

የክለቡን እጣ ፈንታ በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ደግሞ “የወልቂጤ እታ ፈንታ በክለቡ አመራሮች የሚወሰን ይሆናል” ካሉ በኋላ “ሁለት ፎርፌ ሲሆን ተሰርዞ ወደ ታችኛው ሊግ ይወርዳል። ያኔ ደግሞ በሚወርድበት ሊግ የሚጠበቁበትን መስፈርቶች አሟልቶ በታችኛው ሊግ ላይ ይሳተፋል” ብለዋል።

አንድ ክለብ ከወጣለት መርሐ ግብር ከ75 በመቶ በታች ከተጫወተ እንደተሳታፊ ቡድን እንደማይቆጠርም ኃላፊው ገልጸዋል።

ወልቂጤ ላይ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ከሊጉ የሚወርዱ ቡድኖች ቁጥር እንደሚቀንስ የጠቀሱት አቶ ሙሉጌታ፤ ቀጣይ ውሳኔዎች ወደፊት ይፋ እንደሚደረጉ አክለዋል።