ካለዕድሜዋ ከተዳረችበት ጋብቻ ለመውጣት ለዓመታት የታገለችው ታዳጊ እና የታሊባን አፈና

ቢቢ
የምስሉ መግለጫ, ቢቢ

አንዲት ታዳጊ ሰነዶች ይዛ በሁለት ጎዳናዎች መካከል ቆማለች።

ቢቢ ናዝዳና ትባላለች። የያዘቻቸው ሰነዶች ከምንም በላይ ይጠቅሟታል።

ለሁለት ዓመታት በፍርድ ቤት ከታገለች በኋላ ፍቺ እንድትፈጽም ፈቃድ የተሰጠባቸው ሰነዶች ናቸው።

ዕድሜዋ ሳይደርስ ነው የተዳረችው። ሰነዶቹ ከዚህ ሕይወት ነጻ ያወጧታል።

እነዚህን ሰነዶች ታሊባን ተቀባይነት የላቸውም ብሏል።

ታሊባን የሸሪዓን አተረጓጎም ተጠቅሞ አፍጋኒስታን ውስጥ የሴቶችን ነጻነት ይቀማል።

ፍርድ ቤት የፍቺ ፈቃድ ሰጥቷቸው ታሊባን ፈቃዱ ተቀባይነት የለውም ያላቸው ሴቶች በአሥር ሺዎች ይቆጠራሉ። አንደኛዋ ደግሞ ቢቢ ናት።

ታሊባን ከሦስት ዓመታት በፊት አፍጋኒስታንን መልሶ መቆጣጠሩ ይታወሳል።

የሰባት ዓመት ልጅ ሳለች እንድታገባው የታጨችለት ሰው በ10 ቀናት ውስጥ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አስቀልብሷል።

ውሳኔውን በፍርድ ቤት ለማግኘት ለዓመታት ነበር የታገለችው።

ቢቢ 15 ዓመት ሲሞላት ሄክማቱላህ የተባለው ሰው ሊወስዳት ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ሄደ።

አባቷ ሊድሩለት ከተስማሙ ስምትን ዓመታት ተቆጥረዋል።

ጠላቶች ወዳጆች እንዲሆኑ ሲባል በሚፈጸም የጋብቻ ስምምነት ነበር ቢቢ ያገባችው።

ጉዳይዋን ወደ ፍርድ ቤት ወሰደችው። በወቅቱ ፍርድ ቤቱ ይተዳደር የነበረው አሜሪካ በምትደግፈው የአፍጋኒስታን መንግሥት ነበር።

በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል ያለውን አርሶ አደር መፍታት እንደምትፈልግ ለፍርድ ቤት አስታወቀች።

ከሁለት ዓመት በኋላ ፍቺ ተፈቀደላች።

“ፍርድ ቤቱ እንኳን ደስ አለሽ አለኝ። አሁን ፍቺ ፈጽመሽ ያሻሽን ሰው ማግባት ትችያለሽ ተባልኩ” ትላለች።

ቢቢ እና ወንድሟ
የምስሉ መግለጫ, ቢቢ እና ወንድሟ

ግለሰቡ ይግባኝ ካለ በኋላ ግን ፍቺውን መፈጸም አትችይም ተባለች። ከግለሰቡ ምላሽ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

“ሸሪዓ ስለማይፈቅድ ፍርድ ቤት እንዳልመለስ በታሊባን ተነገረኝ። እኔን መወከል የሚችለው ወንድሜ እንደሆነ ገለጹልኝ” ትላለች።

ወንድሟ ሻምስ 28 ዓመቱ ነው።

“ትዕዛዙን የማናከብር ከሆነ እህቴን በግድ ለሰውየው እንደሚሰጧት ነገሩን” ይላል።

ግለሰቡ በቅርቡ ታሊባንን የተቀላቀለ ሲሆን፣ የቢቢን የፍርድ ቤት ውሳኔ አስቀልብሷል። ሻምስ ለፍርድ ቤት ጉዳዮን ለማስረዳት ሞክሮ ነበር።

የእህቱ ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ቢናገርም ሰሚ አላገኘም።

የፍርድ ቤት ሰነዶች
የምስሉ መግለጫ, የፍርድ ቤት ሰነዶች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እህት እና ወንድም አማራጭ ሲያጡ ተሰደዱ።

ታሊባን ዳግመኛ ሥልጣን ሲይዝ ሙስናን ለማስወገድ እና በሸሪዓ መሠረት “ፍትሕ ለማስፈን” ቃል ገብቷል።

355 ሺህ የፍርድ ጉዳዮችን እስካሁን እንደተመለከተ ታሊባን ገልጿል።

አብዛኞቹ የወንጀል ጉዳዮች ናቸው። 40 በመቶ ከመሬት ጋር የተያያዙ እና 30 በመቶ ፍቺን ጨምሮ ሌሎችም የቤተሰብ ጉዳዮች ናቸው።

ቢቢሲ የካቡል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰነዶችን ካገኘ በኋላ ነው የቢቢ የፍቺ ጉዳይ ይፋ የወጣው።

የአፍጋኒስታን ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊ አብዱልዋሂድ ሀቃኒ ፍርድ ቤት ለቢቢ የወሰነው መቀልበሱን አረጋግጧል።

“የቀድሞው ሙሰኛ አስተዳደር ትዳሩን ለማፍረሰ ያሳለፈው ውሳኔ የሸሪዓ የትዳር ሕግን ይጻረራል” ብሏል።

ታሊባን የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ቃል ቢገባም ውሳኔ የተሰጠባቸውን ጉዳዮች ዳግመኛ እየተመለከተ እየቀለበሰ ነው።

በስልታዊ መንገድ ሁሉንም ዳኞች አስወጥቶ የታሊባንን አስተዳደር የሚደግፉ ዳኞችን ተክቷል።

ሴቶች በፍትሕ ሥርዓቱ ለመሳተፍ “ብቁ አይደሉም” ይላል ታሊባን።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አብዱልራሂም ራሺድ “የሸሪዓ ሕግና የፍትሕ ሥርዓቱ ልሂቃንን ይፈልጋል። ሴቶች በዚህ ለመሳተፍ ብቁ አይደሉም” ብሏል።

ከፍትሕ ሥርዓቱ የተገለሉት ሴቶች የተፈጠረውን ክፍተት ይገልጻሉ።

የቀድሞዋ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ፋዋዚያ አሚኒ ታሊባን ወደ ሥልጣን ሲመለስ ከአገር ወጥታለች።

በአገሪቱ ፍርድ ቤቶች ሴቶች ከሌሉ የሴቶችን መብት ለማስከበር ከባድ እንደሆነ ታስረዳለች።

“ቁልፍ ሚና ነበረን። በ2009 ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን የሚገታ ሕግ አጽድቀናል። ከስኬቶቻችን አንዱ ነው። ለሴቶች መጠለያ ለማዘጋጀት፣ ሕገ ወጥ የሰው ዝውውርን ለመግታት እና ወላጅ አልባ ልጆችን ለመንከባከብ ሠርተናል” ትላለች።

የቢቢ የፍቺ ውሳኔ መቀልበሱን ትቃወማለች።

“አንድ ሴት ባሏን ከፈታች እና የፍርድ ቤት ሰነድ ካላት ጉዳዩ አክትሟል። መንግሥት ሲቀየር የፍርድ ቤት ውሳኔ አይቀየርም” ስትልም ታክላለች።

“የሲቪል ሕጋችን ከግምሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሆኖታል። ታሊባን ሳይፈጠር በፊት ሕጉ ነበር። ፍቺን የሚመለከት ሲቪል ሕግ እና የወንጀል መቅጫ ሕግ ከቁርዓን ነው የተወረሱት” ትላለች የሕግ ባለሙያዋ።

ታሊባን ግን የቀድሞው አስተዳር በበቂ ሁኔታ እስልምናን የተከተለ አልነበረም ይላል።

ታሊባን ሀናፊ ፊቅ በተባለው የሃይማኖት ሕግ እንደሚመራ ይገልጻል።

ይህም በ8ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረ ሲሆን “ዘመኑን እንዲዋጅ” መደረጉን የጠቅላይ ፍርድ ቤት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አብዱልራሂም ራሺድ ይናገራል።

“የቀድሞው አስተዳደር በፍትሃ ብሔር ሲቪል እና በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ የተመሠረተ ነው። የአሁኑ ግን መሠረቱ ሸሪዓ ነው” ይላል።

የቀድሞዋ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ፋዋዚያ አሚኒ ግን “ለታሊባን ጥያቄ አለኝ። ትዳር የያዙት በእነዚህ ሕጎች ነው ወይስ ልጆቻቸው በሚጽፉት ሕግ?” ስትል ትሞግታለች።

ቢቢ አሁን 20 ዓመት ሞልቷታል።

የፍቺ ወረቀቷን ይዛ የሚተባበራት ሰው ትፈልጋለች።

“የመንግሥታቱን ድርጅት ጨምሮ ብዙ በር አንኳኩቻለሁ። ድምጼን ግን ማንም አልሰማም። የት አለ ድጋፉ? እንደ ሴት ነጻነት አይገባኝም?” በማለት ምላሽ ያላገኘውን ጥያቄዋን ደግማ ትጠይቃለች።