ታሊባን ‘ስኮላርሺፕ’ ያገኙ ሴት ተማሪዎች ከአገር እንዳይወጡ ከለከለ

ሁለት አፍጋን ሴት ተማሪዎች ከጀርባ

የፎቶው ባለመብት, epa

አፍጋኒስታንን እያስተዳደረ የሚገኘው ታሊባን የውጭ አገር የትምህር ዕድል ያገኙ ሴት ተማሪዎች ከአገር እንዳይወጡ ከለከለ።

ቡድኑ ከዚህ ቀደም ሴት ተማሪዎች በአገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው መማር አይችሉም ብሎ መከልከሉ ይታወሳል።

አንዲት የ20 ዓመት ተማሪ “ታሊባን ዩኒቨርሲቲዎችን ለሴት ተማሪዎች ዝግ ካደረገ በኋላ የነበረኝ ተስፋ በስኮላርሺፕ ከአገር ውጭ መማር ብቻ ነበር” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ለደኅንነቷ ሲባል ስሟ የተቀየረው እና ናታካይ የተባለችው ተማሪ በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የንግድ ከተማ ዱባይ በሚገኘው በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዱባይ የከፍተኛ ትምህር ዕድል አግኝታ ወደዚያው ለማምራት ብትዘጋጅም ከአገር እንዳትወጣ መከልከሏን ገልጻለች።

ይህ በአረብ ኤሜሬቶች ቢሊየነር ሼክ ካህላፍ አሕመድ አል ሃብቱር የተመሠረተው የትምህርት ዕድል ለአፍጋን ተማሪዎች የተቋቋመ ሲሆን፣ እስካሁን ከ100 ያላነሱ የአፍጋን ሴቶች የስኮላርሺፑ አሸናፊ ሆነዋል።

ናታካይ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ቤተሰብ እና ጓደኞቿን ተሰናብታ ወደ አየር ማረፊያ ከተጓዘች በኋላ፣ በአየር ማረፊያው ባሉ የታሊባን ኃላፊዎች ምክንያት ሕልሟ ሁሉ መና እንደቀረ ተናገራለች።

“የታሊባን ባለሥልጣናት የአየር ቲኬታችንን እና የተማሪ ቪዛችንን ሲመለከቱ፣ ‘ሴቶች በተማሪ ቪዛ ከአር መውጣት አይችሉም’ ብለው መለሱን” ስትል በሐዘን የገጠማትን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ናታካይ ከአየር ማረፊያ እንዲመለሱ ከተደረጉ 60 ወጣት ሴቶች መካከል አንዷ ነች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ታሊባን ብቻቸውን የሆኑ ሴቶች ወደየትም እንዳይጓዙ የከለከለ ሲሆን፣ ከአገር መውጣት የሚችሉት ከባሎቻቸው ወይም እንደ ወንድም፣ አጎት ወይም አባት ያሉ ሰዎች ጋር ብቻ ሲጓዙ ነው የሚል ገደብ ጥሏል።

ይሁን እንጂ የትምህር ዕድል ያገኙት ሴቶች በወንድ ዘመዶቻቸው ታጅበው ከአገር ለመውጣት ያደረጉት ሙከራም አልተሳካም።

ናታካይ ለቢበሲ ስትናገር ከወንድ የቤተሰብ አባል ጋር የነበሩ ሴቶች አውሮፕላን ከተሳፈሩ በኋላ ተመርጠው እንዲወርዱ መደረጋቸውንም ገልጻለች።

አንድ እህቱ የትምህር ዕድል አግኝታ ወደ ዱባይ ለመጓዝ ያደረገችው ጥረት የከሸፈባት ተማሪ ወንድም ለቢቢሲ ሲናገር፤ “ስኮላርሺፑ ለእህቴ አዲስ ተስፋን ሰጥቶ ነበር። በተስፋ ተሞልታ ወጥታ በእምባ ተሞልታ ተመለሰች። መብቷ በሙሉ ተነጥቃለች” በማለት ተናግሯል።

ለሴት ተማሪዎቹ የስኮላርሺፕ ዕድሉን የሰጠው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዱባይ የትምህር ዕድሉን ካሸነፉት መካከል ከአገር እንዳይወጡ የተደረጉ ስለመኖራቸው አስታውቋል።

ይህ የታሊባን እርምጃ ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ነቀፌታን በእስላማዊ ቡድኑ ላይ አስከትሏል።

ታሊባን ሴቶች የትምህር ዕድል እንዳያገኙ መከልከላቸው ከፍተኛ የሆነ የጭካኔ ደረጃ ነው ሲሉ የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ሂዩማን ራይትስ ዋች ባልደረባ ሂዘር ባር ተናግረዋል።

ይህ የታሊባን ፖሊሲ የሴት ተማሪዎች የመማር ዕድልን አጨናግፎ እስረኛ አድርጎ የሚይዝ ነው ብለዋል ሂዘር ባር።

የታሊባን ቃል አቀባይ በሥራ ጉዞ ላይ እንደሚገኑ ገልጸው ስለጉዳዩ ምንም መረጃ የለኝም በማለት ለቢቢሲ መልስ ሰጥተዋል።

ናታካይ ግን በዚህ መካከል በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ትገኛለች።

ታሊባን እአአ 2021 ላይ አገሪቱን ሲቆጣጠር ናታካይ የሁለተኛ ድረጃ ትምህርቷን አጠናቃ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ነበረች።

ናታካይ ለሴቶች ምንም አይነት ክብር የሌለው ታሊባን ተስፋዬን አጨልሞታል ትላለች።

“ሴት መሆን ወንጀል በሆነበት አገር ስለምኖር ይህን ዕድል አጥቻለሁ። በጣም አዝኛለሁ። ምን ማድረግ እንዳለብኝም ሆነ በቀጣይ ምን እንደሚገጥመኝ አላውቅም” ብላለች።