ሴት ተማሪዎችን “ተስፋ ያስቆረጠው” የታሊባን የዩኒቨርስቲ ትምህርት ምርጫ ገደብ

አፍጋኒስታውያን ሴት ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“ለዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና የሄድኩት በብዙ ተስፋ ነው። ሆኖም የዩኒቨርስቲ ትምህርት መምረጫ ቅፅን ሳየው የምፈልገውን ትምህርት ማግኘት አልቻልኩም” ስትል በእንባ ተሞልታ የ19 ዓመት ተማሪ ተናግራለች።

ፋጢማ በሚል የምንጠራት ይህቺ ተማሪ በምስራቅ አፍጋኒስታን በምትገኘው የሌግማን ግዛት ነዋሪ ናት።

ከህፃንነቷ ጀምሮ ህልሟ የነበረውን ትምህርት መማር ብትፈልግም በታሊባን አዲስ ስርዓት ምክንያት ህልሟ ጨልሟል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ በአስራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርት ቤት እንዳይማሩ የከለከለው ታሊባን ሴቶች በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች መመዝገብ በሚችሉባቸው የትምህርት ዘርፎች ላይ ሰፊ ገደቦችን ጥለዋል።

የደበዘዙ ተስፋዎች

“ጋዜጠኛ የመሆን ህልም ነበረኝ። በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት መስራት እፈልግ ነበር። ለሴቶች መብት መታገል እፈልጋለሁ" ስትል ፋጢማ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሴት ተማሪዎች በታሊባን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስለታገዱ የመጨረሻ አመት ትምህርቷን አላጠናቀቀችም።

ነገር ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጨረሻ ዓመት ተማሪ የነበሩ ሴት ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናዎችን መውሰድ እንደሚችሉ ውሳኔ ተላልፏል በታሊባን

የፋጢማ ደስታ ግን ብዙም አልቆየም።

ይህ ውሳኔ ሴቶች በሚመርጧቸው የትምህርት ዓይነቶች ላይ መጠነ ሰፊ ገደቦችን ይዞ መጥቷል።

ለምሌ 13 የትምህርት ክፍሎች (ዲፖርትመንት) ባሉት ናንጋርሃር ዩኒቨርስቲ ሴት ተማሪዎች ሰባት የትምህርት አይነቶችን ብቻ የመምረጥ መብት ብቻ ነው የተሰጣቸው።

ሴት ተማሪዎች ጋዜጠኝነት፣ ግብርና፣ የእንስሳት ህክምና፣ ምህንድስናና ወይም ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉ የትምህርት ዓይነቶች እንዲማሩ አይፈቀድላቸውም።

“የሁላችንም ተስፋ ተንኗል” ከተከለከሉ የትምህርት ዓይነቶችን ከመረጡ መካከል አንዷ የሆነችው ፋጢማ

የመግቢያ ፈተናውን በበላይነት የሚከታተሉ የዩኒቨርስቲ መምህራን ወንዶች ተማሪዎች የሚፈልጉትን ትምህርት እንዲመርጡ እንደሚፈቀድላቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

“የትምህርት መምረጫ ቅጹ ቀድሞ አልተሰጠንም እና ወደ አስር የሚጠጉ ሴት ተማሪዎች ቅጹን ስናይ እኛ የምንፈልገው የትምህርት ዓይነቶች ማግኘት ስላልቻልን ሁላችንም በእንባ ታጠብን” በማለት ፋጢማ ታስረዳለች።

ለፋጢማ እና ለጓደኞቿ የመጨረሻው ዓመት በከባድ ፈተናዎች የታጀበ ነበር። ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው በቤታቸው ለዩኒቨርስቲ መግቢያ መዘጋጀት ነበረባቸው። ፋጢማ በቡድን የሚደረጉ ጥናቶችን ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመሆን አዘጋጅታለች።

“በእኛ አካባቢ ትምህርት ቤት ገብተን ትምህርት ለመከታተል ዕድሉ የለም። ሁሉም ተዘግተዋል” ትላለች።

አፍጋኒስታውያን ሴት ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የመግቢያ ፈተናዎች

ባለስልጣናቱ በዚህ ዓመት 30 ሺህ ሴቶችን ጨምሮ 100 ሺህ ተማሪዎች የመግቢያ ፈተናዎች እንወሰዱ ይጠብቃሉ።

ወንዶች እና ሴቶች ፈተናዎቹን የወሰዱት በተለያዩ አዳራሾች ውስጥ ነው። የተፈታኞች ቁጥር ከፍተኛ በሆነባቸው አንዳንድ ግዛቶች የመግቢያ ፈተናዎች ከሁለት ወይም ሶስት ቀናት በላይ ተካሂደዋል።

ሴቶች በሁሉም ግዛቶች ውስጥ የህክምናና ነርሲንግ ትምህርት እንዲወስዱ ተፈቅዶላቸዋል እንዲሁም የመምህራን ስልጠና እና ኢስላማዊ ጥናቶችን መምረጥ ይችላሉ።

የሰብዓዊ መበት ተሟጋቾች እንደሚሉት ለሁሉም ተማሪዎች ትምህርት ቤት ካልተከፈተ በስተቀር በሚቀጥሉት አመታት ለዩኒቨርስቲ የሚያመለክቱ ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ያሽቆለቁላል።

አፍጋኒስታውያን ሴት ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

‘ዝቅተኛ ቁጥር'

የታሊባን ባለስልጣናት የተጣሉትን ገደቦች ቀለል አድርገው ነው የሚያዩት። የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የፈተና ክፍል መሪ የሆኑት አብዱልቃድር ካሙሽ፣ ሴት ተማሪዎች ከሶስትና ከአራት የትምህርት ዓይነቶች በስተቀር የሚወዱትን ትምህርት መምረጥ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

“ሴቶች በተለየ ክፍል ውስጥ ነው ትምህርት የሚሰጣቸው። በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ሴት ተማሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ ነው። ስለዚህ ሴቶች በተወሰኑ የትምህርት ዘርፎች እንዲያመለክቱ አንፈቅድም” ብለዋል።

ባለስልጣናቱ በዚህ ዓመት ትምህርት የሚሰጡ የዩኒቨርስቲ ቦታዎች ብዛት ገና ይፋ አላደረገም።

ታሊባን አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረ በኋላ የትምህርት ዘርፉ ክፉኛ ተጎድቷል እንዲሁም የአሜሪካ ወታደሮች አገሪቷን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ በርካታ ምሁራን ተፈናቅለዋል።

የሃገሪቱ ምጣኔ ኃብት ከቅርብ አስርት አመታት ወዲህ በአብዛኛው በእርዳታ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ታሊባን ሴት ተማሪዎችን ትምህርት ቤት መከልከሉን ተከትሎ የእርዳታ ኤጀንሲዎች በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ለትምህርት ዘርፉ የሚሰጡትን እርዳታ አንስተዋል።

በርካታ መምህራንም ለወራት ደመወዝ አልተከፈላቸውም።

‘አማራጭ የለኝም’

እገዳው በመላ ሀገሪቱ አንድ ወጥ እንዳልሆነ ቢቢሲ መረጃ ያገኘ ሲሆን ለምሳሌ በካቡል ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ጋዜጠኝነትን እንዲማሩ ተፈቅዶላቸዋል።

ነገር ግን ፋጢማ ታሊባን በግዛቷ ላይ የጣለውን እገዳ በመተላለፍ በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ማመልከት አትችልም ምክንያቱም ታሊባን ሴቶች ከግዛታቸው ውጭ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ማመልከት እንዳይችሉ ስለገደበ ነው።

"እኔ ማጥናት የምችለው ባቀረቡልኝ አማራጭ ብቻ ነው። ምንም አማራጭ የለኝም" ትላለች ፋጢማ፤ ነገር ግን በህልሟ ሙሉ በሙሉ ተስፋ አልቆረጠችም።

“መንግሥት በሚቀጥለው አመት ፖሊሲውን ከቀየረ እኔም ጋዜጠኝነትን እመርጣለሁ" ብላለች።