በረሃብ ተዳክማ ልጇን መቅበር ያልቻለችው ሶማሊያዊት እናት

በባለፉት አራት አስርት ዓመት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ በተመታችው ሶማሊያ በርካታ ህፃናት በረሃብ እየረገፉ ነው።
ተጨማሪ እርዳታ ወደ አገሪቷ ካልደረሰ በቀናት ወይም በሳምንታት ውስጥ የከፋ ቀውስ ሊያጋጥም እንደሚችልም የአገሪቱ ባለሥልጣናት እያስጠነቀቁ ነው።
የ11 ዓመቱ ዳሂር እንባው ረሃብ ባጎሳቆለው ጉንጩ ላይ ይወርዳል።
“ከዚህ መትረፍ እፈልጋለሁ” አለ በለሆሳስ።
ከባይዶዋ ከተማ ወጣ ባለውና ከድንኳን በተሰራው ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ባለው አቧራማ ሜዳ ላይ ዳሂር እና እናቱ ተቀምጠዋል። እናቱ ፋጡማ ኡመር በደከመ ድምጿ እንዳያለቅስ ነገረችው።
“እንባህ ወንድምህን አይመልሰውም። ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል” አለችው።
የፋጡማ ሁለተኛ ልጇ የ10 ዓመቱ ሰላት ከሁለት ሳምንት በፊት በረሃብ ሕይወቱ አልፏል። ቤተሰቦቹ ከቀያቸው ለሦስት መንገድ ያህል ተጉዘው ባይዶዋ ከደረሱ በኋላም ነው ብዙም ሳይቆይ ሕይወቱ ያለፈው።
ህጻኑ ከአዲሱ ቤታቸው ጥቂት ሜትሮች ራቅ ብሎ ባለው ቋጥኝ ውስጥ የተቀበረ ሲሆን፣ መቃብሩ በቆሻሻ ተሸፍኖ ለመለየትም አስቸጋሪ ነው።
“ለልጄ ማዘን አልቻልኩም፤ እርሜን አላወጣሁም። ጊዜ የለም። ሌሎቹን በሕይወት ለማቆየት ሥራ እና ምግብ ማግኘት አለብኝ” በማለት ፋጡማ የዘጠኝ ወር ልጇን ቢሌን እያባበለች፣ እየሳለች ወዳለችው ወደ ስድስት ዓመት ሌላኛዋ ልጇ ማርያም እየተመለከተች ተናግራለች።
“ልጄን ለመቅበር ጥንካሬ አልነበረኝም”
አዲስ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው በጊዜያዊ ካምፕ ውስጥ ከሚገኙት ታዳጊ ህፃናት እና ነፍሰ ጡር እናቶች ውስጥ ወደ ሁለት ሦስተኛው የሚሆኑት በከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ይገኛሉ።
በተጨማሪም የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን አገሪቷ ረሃብ ለማወጅም መዘግየቷን ማሳያ ነው።
“ልጄ [የሦስት ዓመቷ ፋርሂር] ፊቴ ላይ ስትሞት ምንም ማድረግ አልቻልኩም” በማለት ቡሎ ሲር ከሚባል መንደር ተነስታ ለአስራ አምስት ቀናት ያህል ከዘጠኝ ልጆቿ ጋር በእግሯ በመጓዝ ባይዶዋ የደረሰችው ፋጡማ ለቢቢሲ ተናግራለች።
“ለ10 ቀናት ያህል አዝያት ነበር የተጓዝነው። ስትሞት መንገድ ዳር ትተናት መጣን። ለመቅበር ምንም አቅም አልነበረንም። የጅብ ድምፅም እየቀረበ መሆኑ እየተሰማን ነበር” ብላለች።

“ምንም ይዤ አልመጣሁም። ቤት ውስጥ ምንም ነገር የለኝም። ከብቶቹ ሞተዋል። ማሳው ደርቋል” ስትል የ50 ዓመቷ ዘቢባ መሐመድ ወደ መንደሯ እንደማትመለስ ተናግራለች።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተፈጠረው ተከታታይ ድርቅ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ለዘመናት የዘለቀውን የአርብቶ አደር የኑሮ ዘዬ ለማጥፋት አፋፍ ላይ ነው።
ልክ እንደ ሌሎች አዲስ መጤዎች ሀቢባ ለቤተሰቧ ሳይመሽና ቅዝቃዜውም ሳይመጣ ከቅርንጫፎች፣ ከዛፍ ዝንጣፊዎች፣ ከቆርቆሮ፣ ከካርቶን ድንኳን በመትከል ሥራ ተጠምዳ ነበር።
ማረፊያም ካገኘች በኋላ ነው ለአምስቱ ልጆቿ የምግብ እና የህክምና እርዳታ ፍለጋ የጀመረችው ።
በከተማው ዋና ሆስፒታል ውስጥ በሚገኘው የህሙማን ክፍል ዶክተር አብዱላሂ ዩሱፍ በየአልጋዎች መካከል እየተንቀሳቀሱ ትናንሽ እና የደከሙ ህፃናትን ይመረምራሉ።
አብዛኞቹ የተኙት ህሙማን ከሁለት ወር እስከ ሦስት ዓመት እድሜ ያላቸው ህጻናት ናቸው። በከፍተኛ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከመሰቃየታቸው በተጨማሪ በሳንባ ምች የተጠቁ እንዲሁም በኩፍኝ የተያዙም ይገኙበታል።
ጥቂቶቹ ለማልቀስ ጥንካሬ ቢኖራቸውም አብዛኞቹ ዝለዋል። ህፃናቱ በከፋ ረሃብ ምክንያት ሰውነታቸው ተሰነጣጥቋል።
“ብዙዎቹ የሚሞቱት ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት ነው” ይላሉ ዶ/ር አብዱላሂ።
“አስፈሪ ነው፤ ሰዎች እየሞቱ ነው”
ምንም እንኳን የሶማሊያ ባለሥልጣናት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በደቡብ ምዕራብ ግዛቶች ሊደርስ ስለሚችለው ረሃብ ለወራት ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም፣ ዶ/ር አብዱላሂ ሆስፒታላቸው ቀድሞውንም ቢሆን ለህጻናት የተመጣጠነ ምግብ ማሟያዎችን ጨምሮ መሠረታዊ የህክምና ቁሶች እጥረት ነበረበት ብለዋል።
“አንዳንድ ጊዜ የአቅርቦት እጥረት አለብን። አሁን ሁኔታው በጣም የሚያስደነግጥ ነው፣ ምክንያቱም ሰዎች እየሞቱ ነው። እኛም ልንረዳቸው አልቻልንም። የአካባቢው አስተዳደር ይህንን በአግባቡ እየተከታተለ አይደለም። ለድርቁ ወይም ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች አላሰቡም” ይላሉ ዶክተሩ በብስጭት።
አንድ የመንግሥት ሚኒስትር ጉድለቶች እንደነበሩ አምነዋል።
“መከናወን ያለባቸው ተግባራት መፍጠን አለባቸው እናም የበለጠ ውጤታማ መሆን አለብን” ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ግዛት የሰብአዊ ጉዳይ ሚኒስትር ናስር አሩሽ በባይዶዋ ዙሪያ ካሉት ካምፖች በአንዱ ባደረጉት አጭር ጉብኝት ወቅት ተናግረዋል።
ሆኖም ዋነኛው ነገር የበለጠ ድጋፍ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሲገኝ ነው ብለዋል።
“የሚያስፈልጉንን እርዳታ ካላገኘን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሞታሉ። አሁን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ከሦስት ወራት በፊት መሰራት ነበረባቸው። በጣም ዘግይተናል። በፍጥነት እርዳታ እስካልተገኘ ድረስ የከፋ ጥፋት ይደርሳል” ብለዋል።
ረሃብን በመደበኛነት የማወጅ ሂደት ከመረጃዎች እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ውስብስብ ነው።
በሞቃዲሾ የብሪታንያ አምባሳደር ኬት ፎስተር እንደሚሉት ረሃብ የማወጅ ሂደት “ቴክኒካል” ነው ይላሉ። በአውሮፓውያኑ 2011 በተከሰተው ድርቅ ወቅት ከ260 ሺህ ሰዎች ውስጥ ግማሾቹ የሞቱት ረሃብ ከመታወጁ በፊት ነው ሲሉ ያስታውሳሉ።

“ሴቶች ይሸሻሉ፤ ወንዶች ወደ ኋላ ይቀራሉ”
ምንም እንኳን አሃዙ ቢለያይም ባለፉት ጥቂት ወራት የባይዶዋ ሕዝብ በግምት በአራት እጥፍ አድጎ ወደ 800 ሺህ ደርሷል።
ማንኛውም ይህንን ስፍራ የጎበኘ ሰው ማስተዋል የሚችለው ነገር ቢኖር አዲስ መጤዎቹ ሁሉም በሚባልበት ሁኔታ ሴቶች ናቸው።
ሶማሊያ ለዘመናት በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ ናት። ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ማዕከላዊ መንግሥት መፈራረስን ተከትሎ ጦርነቱ መልኩን እየቀየረ በመካሄድ ላይ ነው። ይህም በርካታ ቤተሰቦችን በመበተን ወንዶች ለተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ተሰልፈው ተዋጊ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ባይዶዋ እንደደረሱት አብዛኞቹ ሃዲጃ አቡከርም ከታጣቂው እስላማዊ ቡድን አል ሻባብ ከሚቆጣጠረው ግዛት አምልጣ ነው የመጣችው።
“አሁንም ቤተሰቦቼ ስልክ ይደውሉልኛል። በመንግሥት እና በአል ሻባብ መካከል ጦርነቱ ቀጥሏል። ዘመዶቼ ሸሽተው ጫካ ውስጥ ተደብቀዋል” ስትል በባይዶዋ ሆስፒታል የታመመ ልጇን ያቀፈችው እናት ትናገራለች።
በካምፑ ውስጥ ያሉ ሌሎች ሴቶች ባለቤቶቻቸው እና ትልልቅ ልጆቻቸው በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ያሉ አካባቢዎችን ለቀው እንዳይወጡ መከልከላቸውን እና በቡድኑ ለዓመታት ሲዘረፉ ስለነበሩበት ሁኔታ ተናግረዋል።
ባይዶዋ በአል ሻበብ የተከበበች ናት ለማለት አይቻልም። ነገር ግን አስተማማኝ መሸሸጊያ ቦታ ናት። ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች እና የውጭ ጋዜጠኞች በስፍራው ለመንቀሳቀስ ከፍተኛ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል።
“የተከበቡ ሕዝቦች አሉ። አንዳንድ ጊዜ የተስፋ ቢስነት ስሜት አለው” በማለት በማዕከላዊ እና በደቡብ ሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ ኃላፊ የሆኑት ቻርለስ ንዙኪ ተናግረዋል።

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ጊዜ በተከሰተው ድርቅ የተጎዳው ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሚገኘው በአል ሸባብ ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች ነው።
በአሸባሪነት ለተፈረጁ ቡድኖች ማንኛውንም እርዳታ የሚከለክለው ጥብቅ የአሜሪካ መንግሥት ሕግ ችግር ላይ ያሉ ማኅበረሰቦችን ለመድረስ የሚደረገውን ጥረት ውስብስብ አድርጎታል።
ነገር ግን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የሶማሊያ ባለሥልጣናት ከአገር ውስጥ አጋሮች ጋር በመሆን በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ እርዳታ ለማድረስ በአየር ለመጣል እያሰቡ እንደሆነ ተነግሯል።
ያም ሆኖ አንድ የእርዳታ ሠራተኛ ምንም አይነት ምግብም ሆነ ገንዘብ ለአል ሻባብ እንደማይደርስ ዋስትና መስጠት ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን ተናግረዋል።
“አስቸጋሪ ነው። አል ሻባብ የገንዘብ ልገሳዎችን ሳይቀር ግብር ይቆርጣል” ይላሉ።
በባለፉት ዓመታት አል ሻባብ በሁከት እና በማስፈራራት ብቻ ሳይሆን በባለሥልጣናት መጠነ ሰፊ ሙስና በምትቸገረው ሶማሊያ ፍትህን በማስፈን ስመ ጥር ሆኗል።
ለባይዶዋ ቅርብ በሆኑ ቢያንስ አራት መንደሮች ውስጥ፣ አል ሸባብ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን ያስተዳድራል።
እነዚህ ፍርድ ቤቶችም በሞቃዲሾ እና በሌሎች ከተሞች ውስጥ ነዋሪዎች ያላቸውን የንግድ እና የመሬት አለመግባባቶችን ይዳኛሉ።
በሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ በአል ሸባብ ላይ የተቀሰቀሰው ድንገተኛ ሕዝባዊ አመጽን ተከትሎ በማዕከላዊ መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ የሚደረግላቸው የአካባቢው ማኅበረሰቦች እና የጎሳ ሚሊሻዎች ቡድኑን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በደርዘን ከሚቆጠሩ ከተሞች እና መንደሮችን እንዲያፈገፍግ አድርጎታል።
እነዚህ ወታደራዊ ስኬቶች በአገሪቱ ውስጥ ያለው ተስፋ እንዲያንሰራሩ ምክንያት ሆኗል። ነገር ግን ይህ ረሃብን ለመዋጋት ይረዳል ወይስ የሶማሊያ መንግሥት እንዲዘናጋ በር ይከፍት ይሆን የሚለው ግልፅ አይደለም።
“የተቸገረውን ሕዝብ ለመርዳት ሊጠቅም ወይም ላይጠቅም ይችላል። በርካታ ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሊሆን ይችለል ብዬ አስባለሁ። ወይም ደግሞ መንግሥት ብዙ አካባቢዎችን ነጻ ሊያወጣ እና ሰዎች የበለጠ እርዳታ እንዲደርሳቸው ሊያደርግ ይችላል። በሁሉም አቅጣጫ እየተመለከትነው ነው” ሲሉ የአካባቢው ሚኒስትር ናስር አሩሽ ተናግረዋል።












