በረሃ ላይ ብቻውን ምግብ እያበሰለ ፎቶው የታየው ኢትዮጵያዊ ታዳጊ እርዳታ ተሰባሰበለት

የፎቶው ባለመብት, Boru Konso
በረሃ ላይ ብቻውን ምግብ እያበሰለ የነበረውን ታዳጊ ፎቶ ያነሳው ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ ከፎቶው ጀርባ ስላለው ታሪክ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ፎቶውን በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ብዙዎች ያጋሩት ሲሆን ለልጁ ገንዘብና የተለያዩ እርዳታዎችም ተሰባስበውለታል።
ፎቶውን ያነሳው ጋዜጠኛ ቦሩ ኮንሶ ይባላል።
በፎቶው ላይ ታዳጊው ብቻውን በረሃ ላይ ምግብ እያበሰለ የሚታይ ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያም ለተመለከቱትም ከፍተኛ ኃዘኔታን አሳድሯል።
ፎቶውን ያነሳው ጋዜጠኛ በሞተር ሳይክል ሚዮ በተባለች ገጠራማ ሰፈር ሪፖርት ለመስራት እየሄደ በነበረበት ወቅት ነው ልጁን ያገኘው። በጣም መሽቶም ነበር።
"ትንሽ ልጅ ነው ምናልባትም ዕድሜው ከ10 ዓመት በታች። ብቻውን እሳት አንድዶ ምግብ እያበሰለ ነበር። ብቻውን በረሃ ውስጥ እያበሰለ ሳየው ደነገጥኩ። በ10 ኪሎሜትር ርቀት ካልሆነ በአካባቢው ምንም አይነት ቤት የለም። ሞተር ሳይክሌን አቁሜም ፎቶ አነሳሁት" ይላል ቦሩ።
ልጁ ለጋዜጠኛው የገለጸለት ቤተሶቦቹ በሌላ ወረዳ ውስጥ እንደሚኖሩና ውሃና ግጦሽ ፍለጋም ከብቶቹን ይዞ ከቦታ ቦታ እንደሚንቀሳቀስ ነው።
ቦሩ የልጁን ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ማጋራቱን ተከትሎ በርካቶችም ታዳጊውን መርዳት እንደሚፈልጉም ነገሩት።
ህፃኑን ከጎበኙት መካከል ነጋዴዋ ሙና ባካሬ የምትባል ግለሰብ አንደኛዋ ስትሆን ለልጁ ፣ለቤተሰቦቹ እና ለጎረቤቶች የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጋለች።
"የዚህን ትንሸ ልጅ ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ማየቴ ልቤን ነክቶታል። መተኛት አልቻልኩም ነበር። ልጄ እንደሆነ ተሰማኝ፣ ስለዚህ እሱን መፈለግ ጀመርኩ" ብላለች ሙና።
ሙና የልጁን የትምህርት ወጪ እንደምትሸፍን የተናገረች ሲሆን ኮሌጅ እስኪጨርስ ድረስ ለመክፈል ቃል ገብታለች።
በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና እና ሕዝቦች እንዲሁም በሶማሌ ክልሎች በአራት አስርት ዓመታት ያልታየ የከፋ ድርቅ መከሰቱ ተገልጿል።
በአራቱ ክልሎች ባጋጠመው ሦስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች መጨናገፍ የተነሳም በተከሰተ ድርቅ በርካታ እንስሳት ሞተዋል፣ ሰብሎች ወድመዋል፣ የውሃና የምግብ እጥረት በርካቶችንም እያፈናቀለ መሆኑን የተለያዩ የረድኤት ተቋማት እየተናገሩ ነው።
በደቡብ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በእንስሳት መኖ እና ውሃ እጥረት ቢያንስ 267 ሺህ ከብቶች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኦቻ ታኅሣሥ ወር ላይ ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
በድርቁ ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው እና የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር ባለመኖሩ በሶማሌ 99 ሺህ ተማሪዎች እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ 56 ሺህ ተማሪዎች በአጠቃላይ 155 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውም ተጠቁሟል።












