የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉ የእርዳታ ሥራዎቹ ሊገቱ እንደሚችሉ አስጠነቀቀ

የምግብ እርዳታ እየተሰጣቸው ያሉ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ነዳጅና ምግብ መተላለፍ ባለመቻሉ የነፍስ አድን የምግብ እርዳታ አቅርቦት ሥራው ሊቆም መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስጠነቀቀ።

ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው ጦርነት ምክንያት ከታህሣሥ ጀምሮ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የእርዳታ ጭነት መኪኖች መቀለ ሊደርሱ እንዳልቻሉ ድርጅቱ ዛሬ ጥር 6/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

በተጨማሪም ምግብ፣ ነዳጅና የገንዘብ ድጋፍ ዕጥረት እንዳጋጠመው የገለጸው ድርጅቱ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ላለባቸው ህጻናት እና ሴቶችን ለመንከባከብ የሚውለው አልሚ ምግብ ተመናምኗል ብሏል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የመጨረሻ ክምችት የሆነው እህል፣ ጥራጥሬ እና ዘይት በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚሰራጭም ጨምሮ ገልጿል።

"በአሁኑ ወቅት የትኞቹን መመገብ እንዳለብን የትኞቹን ደግሞ እንዲራቡ ለመተው መምረጥ አለብን" በማለት የድርጅቱ የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ማይክል ደንፎርድ ገልጸዋል።

አክለውም "በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ለሰብዓዊ እርዳታ መተለላፊያ የሚሆኑ መንገዶች ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ዋስትና እንዲሰጡን እንፈልጋለን" በማለት አስረድተዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች በቀላሉ በሚፈለገው ፍጥነትና መጠን መድረስ እንዳልተቻለ የገለጹት ዳይሬክተሩ በትግራይ ባለው የምግብና የነዳጅ እጥረት ምክንያት ከሚያስፈልገው የእርዳታ መጠን መደረስ የተቻለው 20 በመቶ ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም በትግራይ ያለውን ሁኔታ ሲገልጹት "በሰብዓዊ ጥፋት አፋፍ ላይ ነን" ብለዋል።

በዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ መሰረት በሰሜን ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት ወደ 9.4 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

ይህም አሃዝ ከአራት ወራት በፊት ከነበረው የ2.7 ሚሊዮን ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ይህም እስካሁን ከታየው ከፍተኛው መሆኑንም የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገልጿል።

በተጨማሪም ውጊያው ከመፋፋሙም ጋር ተያይዞ የምግብ ስርጭቱም በጣም ዝቅተኛ መሆኑንም ጠቁሟል።

ድርጅቱ በትግራይ ለ2.1 ሚሊዮን፣ በአማራ ለ650 ሺህ እና በአፋር ለ534 ሺህ ሕዝብ የምግብ ዕርዳታ ለመስጠት አቅዷል።

ሆኖም ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ባጋጠመው የገንዘብ ድጋፍ ዕጥረት ምክንያት በመላው ኢትዮጵያ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የሚሰጠው የምግብ እና ሌሎች እርዳታዎች አቅርቦት በሚቀጥለው ወር እንደሚያልቅም አስጠንቅቋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ለማድረስ 337 ሚሊዮን ዶላር እና ባበለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በሶማሌ ክልል በከፋ ድርቅ ለተጎዱ ነዋሪዎች እርዳታ ለማድረስ 170 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ጠይቋል።

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ትራንስፖርትና የባንክ አገልግሎቶች አሁንም እንደተቋረጡ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ታኅሣሥ 21/2014 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት መሰረት እርዳታ የጫኑ መኪኖች ከታኅሣሥ ጀምሮ ወደ ትግራይ አልገቡም።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ ያለውን ከአምስት ሚሊዮን በላይ እርዳታ ፈላጊ ሕዝብ ለመድረስ ከታሰበ በየሳምንቱ 100 እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ክልሉ ሊገቡ ይገባል ቢልም፣ እንደ ኦቻ ሪፖርት ወደ ክልሉ መግባት የቻለው ከሚያስፈልገው አቅርቦት ውስጥ 12 በመቶ ብቻ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ እንዳይደርስ ምንም አይነት ክልከላ እንዳልጣለ ገልጾ፣ ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ ደግሞ ወደ ክልሉ የእርዳታ አቅርቦት እንዳይገባ በማድረግ ህወሓትን ከሷል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።