በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች በ40 ዓመት ውስጥ ከታዩት የከፋ ድርቅ ማጋጠሙ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Eric Lafforgue/Art in All of Us
በኢትዮጵያ የሶማሌ እና የኦሮሚያ ክልልሎች በ40 ዓመታት ውስጥ የከፋ ነው የተባለ ድርቅ እንዳጋጠማቸው የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት-ዩኤስኤይድ አስታወቀ።
የክልሎቹ ነዋሪዎች ከብቶቻቸው ምግብና ውሃ በማጣታቸው እየረገፉ መሆናቸውንና ድርቁ የማኅበረሰቡ የኑሮ መሠረት የሆኑትን እንስሳቱን እየነጠቀው መሆኑም ተገልጿል።
የዓለም አቀፉ ነፍስ አድን ኮሚቴም በደቡበ ምሥራቅ ኢትዮጵያና በሶማሊያ በአርባ ዓመት ውስጥ ከታዩት የከፋ ድርቅ እንዳጋጠማቸውና በእነዚህ አካካቢዎች ለሰብዓዊ ቀውስ መባባስ ምክንያት መሆኑንም በቅርብ ጊዜ ባደረገው ግምገማ መመልከቱንም በሪፖርቱ አስታውቋል።
በሶማሌና በኦሮሚያ ክልልሎች ለሦስተኛ ጊዜ የሚጠበቀው ዝናብ ባለመገኘቱ ባጋጠመው ድርቅ በአካባቢው የሚኖሩ የአርብቶ አደር እንዲሁም የአርሶ አደር ማህበረሰቦች ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰም እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኦቻ ታኅሣሥ ወር ላይ ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
የሶማሌ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ቢሮን ዋቢ አድርጎ እንደገለጸው በሶማሌ ክልል ፋፋን እና ሲቲ ዞኖች ከፍተኛ ከፍተኛ ምርት መታጣቱም ተገልጿል።
ከእነዚህም መካከል እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የማሽላ እና የበቆሎ ምርት፣ ከተጠበቀው የስንዴ ምርት 30 በመቶ እንዲሁም ከታሰበው የሽንኩርት እና የቲማቲም ምርት 30 በመቶው ታጥቷል። በተመሳሳይ በደቡብ ኦሮሚያ 70 በመቶ ምርት እንደታጣም ተገልጿል።
በደቡብ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በእንስሳት መኖ እና ውሃ እጥረት ቢያንስ 267 ሺህ ከብቶች መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በተጨማሪም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለአደጋ ተጋልጠዋል ተብሏል። ከብቶቹ አስቸኳይ መኖ፣ ውሃ እና ክትባትም ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።
በርካታ አርብቶ አደሮችና፣ አርሶ አደር አርብቶ አደሮች በዋናነት ከቆራሄይ፣ ጃረር፣ ኤረር እና ኖጎብ ዞኖችና በፋፋን ዞን በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ለግጦሽ ሳርና ውሃ ፍለጋ መሰደዳቸውን ኦቻ ጠቅሶ የተፈናቀሉ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር እስካሁን አልታወቀም ብሏል።
በአሁኑ ወቅት በሶማሌ 2.3 ሚሊዮን እና ከ870,000 በላይ ደግሞ በደቡብ ኦሮሚያ በአጠቃላይ ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለውሃ እጥረት መጋለጣቸውን ኦቻ በሪፖርቱ አስፍሯል።
በድርቁ ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው እና የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር ባለመኖሩ በሶማሌ 99 ሺህ ተማሪዎች እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ 56 ሺህ ተማሪዎች በአጠቃላይ 155 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በድርቁ ምክንያት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በእጥፍ የጨመረ ሲሆን ከአምስት ዓመት በታች ባሉ ህጻናት ላይ የተቅማጥ በሽታ ተጠቂዎች እየተመዘገቡ መሆኑም የዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ ጠቅሷል።
በአጠቃላይ በሁሉም ድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ከ6.4 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ ሰዎች የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውም ኦቻ አስታውቋል።
ከእነዚህም መካከል በሶማሌ ክልል 3 ሚሊዮን፣ በምሥራቅ ኦሮሚያ 2.4 ሚሊዮን እና በደቡብ ኦሮሚያ 1 ሚሊዮን ዜጎች ይገኙበታል።
የውሃ ማጓጓዣ፣ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎች አቅርቦት፣ የህጻናት እና ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ ሴቶች የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ቅድመ ዝግጅት፣ የሞባይል ጤና እና የሥነ ምግብ ክሊኒኮችን ወደሚደረስባቸው አካባቢዎች ማሰማራት፣ የእንስሳት መኖ እና የእንስሳት ሐኪሞች ማሰማራትን ጨምሮ በርካታ ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልግም ገልጿል።
አሁን ካጋጠመው ሁኔታ አንፋር አስቸኳይ ወቅታዊ ምላሽ ካልተሰጠም ሁኔታዎች ሊባባሱ እንደሚችሉም ጠቁሟል።












