በድርቅ የተጎዱ የቦረና አርብቶ አደሮችን ለመርዳት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው

በቦረና ዞን ያጋጠመውን ድርቅ ተከትሎ ጉዳት ላጋጠማቸው አርብቶ አድሮች የተለያየ ድጋፍ እየተደረገ ነው።
የክልሉ መንግሥት በድርቅ የተጎዳውን የሕብረተሰብ ክፍል ለመርዳት 30 ሚሊዮን ብር መመደቡን ያስታወቀ ሲሆን፤ በርካቶች ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ድጋፍ እያሰባሰቡ ይገኛሉ።
በኦሮሚያ ክልለ ቦረና ዞን ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ሳይዘንብ በመቅረቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤተ እንስሳት መሞታቸውን ነዋሪዎች እና መንግሥት አስታውቀዋል።
የቦረና ዞን ዱብሉቅ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ቱሬ ሊበን በድርቁ ሳቢያ አራት ከብቶች እንደሞቱባቸው ተናግረው፤ "ጎረቤቴ 13 ክብቶች ሞተውበታል። የዘንድሮ ድርቅ ከባድ ነው። ግመሎች እንኳን እየሞቱ ነው" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቦረና አርብቶ አደሮች የግጦሽ ሳር እጥረት በመኖሩ ከብቶቻቸው ከተኙበት መነሳት ስለማይችሉ በሰው ኃይል እየተደገፉ ተነስተው እንደሚቆሙ አስረድተዋል።
ቱሬ ሊበን የከብቶቻቸውን ሕይወት ለማስቀጠል ረዥም ርቀት ተጉዘው ጭድ እየገዙ እየመገቧቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
"ከዱቡሉቅ ተነስቼ ከያቤሎ በአህያ ጭድ ገዝቼ ነው የማመጣው። 100 ኪሎ ሜትር የሚሆን ርቀት ተጉዤ ነው ገዝቼ እየተመለስኩ ያለሁት። የገጠመን ችግር የከፋ ነው" በማለት የሉበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።
እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች
የኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስጋት ኮሚሽን በቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ 30 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቋል።
የኦሮሚያ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ የክልሉን የአደጋ ስጋት ኮሚሽን ምክትል ኃላፊን ቢሮን ጠቅሶ እንደዘገበው መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድርቁ የከፍ ጉዳት እንዳያስከትል እየሰሩ ይገኛሉ ብሏል።
መንግሥት እና ተቋማት ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር በርካቶች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በድርቅ ለተጎዳው አርብቶ አደሮች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
የባንክ ሂሳብ በመክፈት ለቦረና አርብቶ አደሮች ድጋፍ እያሰባሰቡ ካሉት መካከል አንዱ ጃተኒ ቦናያ ነው።
ችግሩን ከመንግሥት በተጨማሪ ሌሎችም እንዲያውቁት እና የተቻላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም እንደጀመሩ ለቢቢሲ ገልጿል።
"በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በርካታ ተከታይ ካላቸው ሰዎች ጋር በመሆን እየሰራን እንገኛለን" ብሏል።
በጎፈንድሚ አማካኝነትም እስካሁን በአርብቶ አደሩ ስም ከ22 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር መሰብሰቡን አመልክቷል።












