ሾልኮ የወጣ ሰነድ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ያላቸውን አቋም አጋለጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቢቢሲ የተመለከተው አንድ ሾልኮ የወጣ ሰነድ አገራት በጣም ጠቃሚ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ ዘገባን ለመለወጥ እየሞከሩ እንደሆነ አጋለጠ።
ሾልኮ የወጣው ሰነድ እንዳረጋገጠው ሳዑዲ አረቢያ፣ ጃፓን እና አውስትራሊያ የተባበሩት መንግሥታት በካይ ጭስ የሚያመነጩ የኃይል ምንጮች ያላቸውን የጉዳት መጠን አሳንሶ እንዲያቀርብ እየጎተጎቱ ይገኛሉ።
በተጨማሪም ሰነዱ እንዳጋለጠው ሃብታም የሚባሉት አገራት ደሃ ለሚባሉቱ ወደ አረጓዴ ቴክኖሎጂ እንዲሸጋገሩ የሚያዋጡት ብር እያሳሰባቸው እንደሆነ ሰነዱ አሳይቷል።
የሾለከው ሰነድ በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ወር በሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ ጥላ ያጠላበታል ተብሎ ተሰግቷል።
እነዚህ በጎን የተባበሩት መንግሥታትን እየጎተጎቱ ያሉ አገራት በሚቀጥለው ወር ተሰባስበው የዓለማችንን የሙቀት መጠን ወደ 1.5 ሴልሺዬስ ለማውረድ ይመክራሉ።
የሾለከው ሰንድ እንሚያሳየው አገራቱ በመንግሥታት፣ በኩባንያዎችና ያገባናል በሚሉ ድርጅቶች አማካይነት ከ32 ሺህ በላይ ቅሬታዎችን አስገብተዋል።
ታድያ እነዚሁ አገራት ናቸው በሚቀጥለው ወር ለዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ለማምጣት ተሰባስበው የሚመክሩት።
የተባበሩት መንግሥታት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ያሉ ቅሬታዎችን የሚሰማ ተቋም አለው። ይህ ተቋም ነው ባለፉት ስድስትና ሰባት ዓመታት የሰበሰባቸውን ቅሬታዎች የሚገመግመው።
ግምገማው መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ምን እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ለመወሰንና ከመጥቀም አልፎ ግላስጎው ለሚደረገው ስብሰባ እንደ ግብዓት ይሆናል።
ቢቢሲ በዚህ ዘገባ ላይ ያነበባቸው የአብዛኛዎቹ መንግሥታት አስተያየት በጣም ገንቢ ሆነው የሚወሰዱ ናቸው። እነዚህ የመንግሥታት አስተያየቶች ወደ መጨረሻው ዘገባ ከመካተታቸው በፊት በጋዜጠኞች ይታያሉ። ቢቢሲ ይህንን ሾልኮ የወጣ ዘገባ ያገኘው በዚህ ምክንያት ነው።
ሰነዱ ምን ይላል?
ሰነዱ እንደሚጠቁመው በርካታ አገራት ዓለማችን እንደ ነዳጅና ከሰል የመሳሰሉ 'ፎሲል ፊዩል' የኃይል ምንጮችን አጠቃቀም በፍጥነት መቀነስ የለባት ይላሉ።
የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ሚኒስቴር አማካሪ "ፎሲል ፊዩልን ለመቀነስ ፈጣን የሆነ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል" መባሉ ያሳሰባቸው ይመስላል።
አንድ የአውስትራሊያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣንም በከሰል ኃይል የሚሠሩ ድርጅቶች መዘጋት አለባቸው መባሉን ይቃወማሉ።
ኮፕ26 የሚል ስያሜ የተሰጠው በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አዘጋጀነት የሚካሄደው ጉባዔ አንዱ መወያያው በከሰል ኃይል የሚሠሩ ድርጅቶች ዕጣ ፈንታን መወሰን ነው።
ሳዑዲ አረቢያ የዓለማችን ቁጥር አንድ ነዳጅ አምራች ስትሆን አውስትራሊያ ደግሞ ከሰል አምሮቶ በመሸጥ የሚያህላት የለም።
የነዳጅ አምራች አገራት ጥምረት የሆነው ኦፔክ አባላት የሆኑት ሳዑዲ፣ ቻይና አውስትራሊያና ጃፓን እንዲሁም ሌሎች ካርበን ዳይኦክሳይድ ታምቆ ምድር ውስጥ እንዲቀበር የሚለውን ሐሳብ ከሚደግፉ መካከል ናቸው።
ካርበንን አምቆ ማስቀመጥ ከኢንዱስትሪዎች የሚወጣውን ከፎሲል ፊዩል የሚለቀቅ ጭስን ለመቆጣጠር ያስችላል ይላሉ።
አርጀንቲና፣ ኖርዌይም እንዲሁ በተባበሩት መንግሥታት የፎሲል ፊዩል ሐሳብ ዙሪያ ቅሬታ ያነሱ አገራት ናቸው። በተለይ ኖርዌይ የመንግሥታቱ ሳይንቲስቶች ካበርንን ምድር ውስጥ ማመቅ የሚለውን ሐሳብ እንዲያጠኑት ትሻለች።
ዘገባው እንደሚያመለክተው ካበርንን ምድር ውስጥ ማመቅ ለወደፈቱ ጠቃሚ ሊሆን ቢችልም እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይችልም።
የሥጋ ፍጆታን መቀነስ
ሁለቱ የዓለማችን ታላላቅ የበሬ ሥጋና የእንስሳት ምግብ አምራቾች ብራዚልና አርጀንቲና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ የሥጋ ፍጆታ መቀነስ አለበት የሚለውን ሐሳብ አይቀበሉም።
ዘገባው እንደሚጠቁመው አረጓንዴ ነገሮችን መመገብ የካርበን ልቀት 50 በመቶ ሊቀንስ ይችላል። ብራዚል ይህን አሃዝ አትቀበለውም።
ሁለቱም አገራት የመንግሥታቱ ድርጅት ይህንን ሐሳብ እንዲሰርዘው አሊያም እንዲቀይረው ጠይቀዋል።
ሁለቱ የደቡብ አሜሪካ አገራት ሥጋ መመገብ የካርበን ልቀትን ይጨምራል እንደሚባለው ሁሉ ሥጋ በል መሆን ካርበን ሊቀንስ እንደሚችል ጥናት አለ ይላሉ።
ብራዚል የካርበን ልቀት ጉዳይ ከምግብ ወደ ሌሎች ጉዳዮች መሸጋገር አለበት ባይ ናት።
ሌላው በዘገባው ላይ አነጋጋሪ ሆኖ የቀረበው ጉዳይ በማደግ ላይ ላሉ አገራት የሚሰጠው ገንዘብ ነው።
ስዊትዘርላንድ በዚህ ሰነድ ላይ ካስቀመጠቻቸው አስተያየቶች አብዛኛዎቹ የሚያተኩሩት የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ለእነዚህ አገራት ገንዘብ መሰጠት አለበት ወይ በሚለው ላይ ነው።
አውስትራሊያም እንደ ስዊትዘርላንድ "ታዳጊ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ካደጉት አገራት በሚሰጥ ገንዘብ ላይ ጥገኛ መሆን የለባቸውም" ትላለች።












