ከኢትዮጵያ ታፍነው እየተወሰዱ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚቸበቸቡት የዱር ድመቶች

የፎቶው ባለመብት, Nichole Sobecki/National Geographic
መገኛቸው በዋናነት ከኢትዮጵያ፣ ከሶማሊላንድ እንዲሁም ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገራት የሆኑ የዱር ድመቶች ታፍነው ተወስደው በአረብ አገራት ውስጥ እንደ ቤት እንስሳ እየተቸበቸቡ ነው።
በተለይ ደግሞ አቦ ሸማኔዎች ከኢትዮጵያ በሶማሊላንድ በኩል ወደ የመን አቅንተው በባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ ላሉ ባለሃብቶች በሺህ ዶላሮች እየተሸጡ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ቶማስ ሞሌ፤ ላለፉት አራት ዓመታት ከአፍሪካ ቀንድ ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት በሕገ ወጥ መንገድ የሚጓጓዙ የዱር እንስሳትን ጉዳይ ሲከታተሉ ቆይተዋል።
"ምንም እንኳ አቦ ሸማኔ አፍሪካ ውስጥ ካሉ የዱር ድመቶች መካከል አደጋ ላይ ያለ እንስሳ ቢሆንም በአፍሪካ ቀንድ ስለዚህ ጉዳይ ያለው እውቀት አናሳ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ አማርኛ ተናግረዋል።
ባለሙያው፤ አብዛኛዎቹ አቦ ሸማኔዎች ከኢትዮጵያ ታፍነው እንደሚወሰዱና በሶማሊላንድ በኩል አድርገው ነው የመን የሚገቡት ይላሉ።
ቶማስ፤ ቶሪድ አናሊቲክስ ለተሰኘ ተቋም የሚሠሩ ሲሆን ይህ ድርጅታቸው ናሽናል ጂኦግራፊክ ከተሰኘው ጣቢያ ጋር በጥምረት አደጋ ላይ ስለወደቁ የአፍሪካ ቀንድ አቦ ሸማኔዎች መረጃ ይሰጣል።
እነዚህ ድርጅቶች ባለፈው ዓመት ሶማሊላንድ ውስጥ ሕገ ወጥ የዱር እንስሳት ንግድን ያቀላጥፋል የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር እንዲውልና ቅጣት እንዲያገኝ አድርገዋል።
በየወሩ ቢያንስ አራት የአቦ ሸማኔ ግልገሎች በሕገ ወጥ መንገድ በዱር እንስሳት አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ከአገር ሊወጡ ሲሉ ደንበር ላይ እንደሚያዙ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ባለፈው ዓመት ማሳወቁ አይዘነጋም።
የዓለማችን በርካታ አቦ ሸማኔዎች የት ይገኛሉ?
በአሁኑ ወቅት በዓለማችን 7 ሺህ ገደማ አቦ ሸማኔዎች ጫካ ውስጥ እንደሚገኙና ይህ ቁጥር ከቀን ቀን እያሽቆለቆለ እንደሆ ቶማስ ይናገራሉ።
አቦ ሸማኔዎች ብዙ ጊዜ ደረቅ የሆነና በአየር ንብረት ለውጥ የተጎዳ ቦታ ሰለሚመርጡ ይህ የአኗኗር ሁኔታቸውን አዳጋች ያደርግባቸዋል ሲሉ ያክላሉ።
ለምሳሌ ይላሉ ቶማስ "ለምሳሌ ሴሬንጌቲና መሳይ ማራ በተሰኙት የምሥራቅ አፍሪካ ሥፍራዎች ከ3 ሺህ በላይ አናብስት ሲኖሩ፤ በዚህ ሰፊ ቦታ ላይ የሚገኙ አቦ ሸማኔዎች ቁጥር ግን ከ300 አይበልጥም።"
አሁን ዱር ውስጥ ካሉት 7 ሺህ ገደማ አቦ ሸማኔዎች መካከል አብዛኞቹ በአፍሪካ ቀንድና፣ በምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም በደቡባዊ አፍሪካ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
ምንም እንኳ አብዛኞቹ አቦ ሸማኔዎች በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው ቢገኙም የዚህ ሕገ-ወጥ ንግድ ዋነኛ ተጠቂዎች ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ናቸው ይላሉ ቶማስ።

የፎቶው ባለመብት, Nichole Sobecki/National Geographic
ቶማስ እንደሚሉት ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት አዘዋዋሪዎቹ የዱር ድመቶቹን የሚይዟቸው በየአካባቢው ባሉ አርብቶ አደሮች ትብብር ነው።
"አዘዋዋሪዎቹ አርብቶ አደሮች ሲያገኙ በመንገዳችሁ የዱር ድመቶች ካገኛችሁ ያዟቸው እኛ እንገዛችኋለን ይሏቸዋል። ከዚያም ገና ግልገል የዱር ድመቶችን ከአርብቶ አደሮቹ ወስደው ይሸጣሉ።"
'ካብስ' በመባል የሚታወቁት ግልገል አቦ ሸማኔዎች በባሕላዊ መንገድ ማለትም በቅርጫት አሊያም ቀዳዳዎች ባሉት ፕላስቲክ ማንጠልጠያ ከቦታ ቦታ በቀላሉ እንደሚጓጓዙ ሙያተኛው ያስረዳሉ።
ቢያንስ 10 አቦ ሸማኔዎች ሰብሰብ ተደርገው ወደ የመን ካቀኑ በኋላ ዋነኛ ገበያቸው የሚሆኑት እንደ ሳዑዲ አራቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ ባህሬይንና ኦማንን የመሳሰሉ የባሕረ ሰላጤው አገራት ናቸው።
ሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹ አቦ ሸማኔዎችን ወደ የመን ሲወስዱ በምትኩ ረብጣ ዶላሮች አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የጦር መሣሪያዎችን እንደሚያገኙ ናሽናል ጂኦግራፊ የተሰኘው መጽሔት ያሳተመው አንድ ፅሑፍ ያመለክታል።
ቶማስ ሞሌም ይህንን ለቢቢሲ አማርኛ ያረጋግጣሉ።
"ብዙ ጊዜ አዘዋዋሪዎቹ የዱር ድመቶቹን በገንዘብ ነው የሚሸጧቸው፤ ነገር ግን እንደሚታወቀው በየመንና በአፍሪካ ቀንድ መካከል ሕገወጥ የሰዎችና የጦር መሣሪያ ዝውውር አለ። ለዚህ ነው አንዳንድ ጊዜ የጦር መሣሪያም እንደመገበያያ ሆኖ የሚያገለግለው።"
የግልገል አቦ ሸማኔዎች ዋጋ ከቦታ ቦታ ይለያያል። ለምሳሌ አቦ ሸማኔዎቹ በዋናነት የሕገወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ ሥር በሚገቡባቸው ሶማሊላንድና ኢትዮጵያ የአንድ ግልገል አቦ ሸማኔ ዋጋ ከ250 እስከ 500 ዶላር ሊያወጣች ይችላል። አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ 500 ዶላር እስከ 23 ሺህ ብር ሊመነዘር ይችላል።
ነገር ግን እንደ ቶማስ ከሆነ ጤናማ ግልገል አቦ ሸማኔዎች ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ሲደርሱ ከ6 ሺህ ዩሮ እስከ 8 ሺህ ዩሮ [430 ሺህ ብር ገደማ] ያወጣሉ።
ኢትዮጵያ ምን እየሠራች ነው?
አብዛኞቹ ግልገል አቦ ሸማኔዎች መነሻቸው ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ነው። በተለይ ደግሞ ከኦሮሚያ፣ ከአፋር እና ከሶማሊ ክልሎች ነው ይላሉ ባለሙያው።
ምንም እንኳ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢጋድ አማካይነት ይህንን ሕገወጥ የእንስሳት ዝውውር ለመግታት ጥረት እያደረገ ቢሆንም ማስፈፀም ላይ ክፍተት አስተውለናል ባይ ናቸው ባለሙያው።
ጨምረውም ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት ሕገ-ወጥ የእንስሳት ዝውውርን በተመለከተ ጠንከር ያለ ሕግ ቢኖራትም ሕጉን በማስፈፀም ረገድ ኬንያ የተሻለ ተሞክሮ አላት ይላሉ ቶማስ።
ነገር ግን ባለሙያውም ሆኑ የሚሠሩለት ተቋም በቀጣይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የበለጠ ተባብሮ ለመሥራትና ጉዳዩን ለመግታት እንደሚጥሩ ይናገራሉ።
በባሕረ ሰላጤው አገራት የዱር እንስሳትን ይዞ መታየት እንደሃብት መገለጫ ስለሆነ ይህንን ችግር መቅረፍ ብዙ ሥራዎች ይጠይቃል ይላሉ።
አብዛኛዎቹ መጨረሻቸው የባሕረ ሰላጤው አገራት የሆኑ የዱር ድመቶች በማኅበራዊ ሚድያ አማካይነት ነው የሚሸጡት ይላሉ ባለሙያው።
ምንም እንኳ ይህ ጉዳይ ሕግ አስከባሪዎች በዚህ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ለመቆጣጠር ቀላል ቢሆንላቸው ቢገባም በባሕረ ሰላጤው አገራት ያለው ቸልተኝነት እንቅፋት እንደሆነ አይክዱም።
እንደ ቶማስ ከሆነ ምንም እንኳ አቦ ሸማኔ እየተመናመነ ያለ የዱር እንሰሳ በመሆኑ ጉዳዩ አሳሳቢ ይሁን እንጂ ሌሎችም እንደነብርና አንበሳ ያሉ ግዙፍ የዱር ድመቶች ከኢትዮጵያና ሶማሊላንድ እየተወሰዱ በባሕረ ሰላጤው አገራት በበርካታ ሺህ ዶላሮች እንደሚቸበቸቡ መረጃው አለ።
ቢሆንም ኬንያና ሶማሊላንድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዚህ ሕገወጥ ዝውውር ላይ ሲሳተፉ የተገኙ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረጋቸው ሕገወጡን የዱር እንስሳት ንግድ ለመቆጣጠር ተስፋ ሰጪ ነው ባይ ናቸው።
















