የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 ለተጨማሪ አንድ ዓመት አብሮን ሊቆይ ይችላል አለ

ኮቫክስ ክትባት ስርጭት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመላው ዓለም የሚገኙ ድሃ አገራት የኮቪድ-19 ክትባትን በተገቢው ጊዜና መጠን እያገኙ ባለመሆናቸው ወረርሽኙ መቆየት ከሚገባው በላይ አንድ ተጨማሪ ዓመት አብሮን ይኖራል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ብሩስ አሊዋርድ በዚሁ ችግር ምክንያት የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ እስከ አውሮፓውያኑ 2022 ድረስ ይቆያል ብለዋል።

እስካሁን 5 በመቶ ብቻ የሚሆነው የአፍሪካ ሕዝብ ክትባቱን ማግኘት የቻለ ሲሆን በሌሎች አህጉራት ደግሞ እስከ 40 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ክትባቱን አግኝቷል።

ዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን 10 ሚሊዮን ክትባቶችን ለድሃ አገራት ያደረሰች ሲሆን አጠቃላይ እቅዷ 100 ሚሊዮን ክትባቶችን ማድረስ ነው።

ሀብታሞቹ አገራት ክትባቱን ለማግኘት የሚያደርጉትን እሽቅድድም ገታ አድርገው ትልልቅ መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ላይ ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ እንዲፈቅዱላቸው ዶክተር ብሩስ ጠይቀዋል።

አክለውም "ሀብታም አገራት በያዝነው ዓመት የቡድን 7 ስብሰባ ላይ እርዳታ ለማድረግ የገቡትን ቃል መልሰው ሊቃኙት ይገባል" ብለዋል።

"እውነታውን ልንገራችሁ፤ ከእቅዳችን በጣም ወደኋላ ቀርተናል። ቃል የተገባውን ገንዘብ በፍጥነት ልንጠቀምበት ይገባል። አለበለዚያ ግን ይህ ወረርሽኝ ለተጨማሪ ዓመት አብሮን እንዲቆይ ይሆናል።''

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጥምረት የሆነው 'ፒፕልስ ቫክሲን' ባወጣው መረጃ መሰረት የበለጸጉት አገራትና ትልልቅ የመድኃኒት አምራች ድርጅቶች ለመስጠት ቃል ከገቡት የክትባት መጠን ቢያንስ ከእያንዳንዱ 7 ክትባት አንዱ ብቻ ነው ወደ ድሃ አገራት እየደረሰ የሚገኘው።

በተቃራኒው ክትባቶቹ ከፍተኛ ገቢ ላላቸውና በበለጸጉት አገራት ለሚኖሩ ዜጎች ነው በስፋት እየተዳረሱ የሚገኙት። አፍሪካም ቢሆን እስካሁን ከመላው ዓለም ካለው ፍላጎት 2.6 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው የቀረበላት።

በተጨማሪም እንደ ኦክስፋም እና ዩኤንኤይድ የመሳሰሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን የያዘው ጥምረት ዩናይትድ ኪንግደም እና ካናዳ በኮቫክስ በኩል የሚመጡ ክትባቶን ለዜጎቻቸው አከፋፍለዋል በማለት ተችቷል።

ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዩናይትድ ኪንግደም በኮቫክስ በኩል 536 ሺህ 370 የፋይዘር ክትባቶችን የተረከበች ሲሆን ካናዳ ደግሞ ለአንድ ሚሊዮን የቀረቡ የአስትራ ዜኔካ ክትባቶችን ወስዳለች።

ኮቫክስ የኮቪድ-19 ክትባት ለደሃ አገራት እንዲደርስ የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ጥምረት ነው። የበለጸጉት አገራት ለኮቫክስ ኢኒሺዬቲቭ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

በተለይ ደግሞ 92 ደሃ የሚባሉ አገራት ከሌሎች 98 አቅም ካላቸው አገራት እኩል ክትባቱን እንዲቀበሉ ይደረጋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ናቸው።

ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ደግሞ በኮቫክስ በኩል የተገኙ 2.2 ሚሊዮን የኮቪድ-19 ክትባቶች ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን ክትባቱም አስትራዜኔካ ሠራሽ ነው።

ኮቫክስ መጀመሪያ ላይ በመላው ዓለም 2 ቢሊየን የክትባት ብልቃጦችን ለማድረስ እቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ግን ማሳካት የቻለው 371 ሚሊየን ክትባቶችን ብቻ ነው።