ፀሐይ ለምን ቢጫ አልሆነችም?

ቢጫ የተቀባች ፀኃይን የሚያሳይ በልጅ የተሳለ ስዕል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከልጅነታችን ጀምሮ ፀሐይን ሳሉ ስንባል ቢጫ ቀለምን መርጠን ቀብተናል። የፀሐይ መውጣትን ወይም የፀሐይ መጥለቅን ለማሳየት ደግሞ ምናልባት ትንሽ ብርቱካንማ ወይም ቀይ ቀለም እናክልበታለን።

ሆኖም በፀሐይ መሐል ላይ ያለው ቦታ ቢጫም፣ ብርቱካናማም ወይም ቀይም አይደለም።

ከዚህ ይልቅ ሦስቱ ቀለሞች አንድ ላይ የተዋሃዱበት እና ሌሎችንም የያዘ ነው።

ፀሐይ በተከታታይ የቀለማት ብርሃን ትፈነጥቃለች።

ፕሪዝም ተጠቅመው የፀሐይ ብርሃንን ከተመለከቱ ወደ ቀይ፣ ብርቱካናማ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ፣ ሰማያዊ፣ ኢንዶጎ እና ቫዮሌት የተከፋፈለ መሆኑን ያስተውላሉ።

ልክ እንደ ቀስተደመና ሁሉ እነዚህ ህብረቀለማት ናቸው የሚታዩት።

እንደ እውነቱ ከሆነ ቀስተ ደመናዎች እንደ ጥቃቅን ፕሪዝም በሚሠሩ በከባቢ አየር ውስጥ ባሉ የውሃ ጠብታዎች ውስጥ እንደሚያልፈው የፀሐይ ብርሃን ለዓይኖቻችን ይታያሉ።

ሆኖም ብዙ ቀለም ያለው ፀሐይ በእርግጠኝነት አስደሳች ቢመስልም ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደለም።

በዚህም ነው ፀሐይ የምትለቃቸው ሁሉም የብርሃን ቀለሞች ሲቀላቀሉ አንድ ቀለም ብቻ የምናገኘው።

ምን እንደሆነ ለማወቅ ከፈለግን ሰማይ ላይ ፍንጭ አለ።

የፀሐይ ብርሃን ለእኛ የሚያንፀባርቁት እነዚያ ለስላሳ ደመናዎች ቢጫም ሆነ ሌላ ቀለም አይደሉም።

ነጭ ናቸው። ምክንያቱም ፀሐይ የምትለቀው እውነተኛ ቀለም ነውና።

በሕዋ ላይ ፀሐይ እውነተኛ ቀለሟ ይስተዋላል፤ ነጭ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሕዋ ላይ ፀሐይ እውነተኛ ቀለሟ ይስተዋላል፤ ነጭ

ለምን ታዲያ ቢጫ እናያለን?

በፀሐይ ጨረር ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ቀለም የተለየ የሞገድ ርዝመት አለው።

በአንደኛው ጫፍ ረዥም የሞገድ ርዝመት ያለው ቀይ ነው።

ከዚያ የቀለሞቹ የሞገድ ርዝመት ከቀይ ወደ ብርቱካናማ፣ ወደ ቢጫ፣ ወደ አረንጓዴ፣ ሰማያዊ፣ ኢንዶጎ እና ቫዮሌት እየቀነሰ ወደ አጭሩ የሞገድ ርዝመት ያለው ቀለም ያመራል።

በአጫጭር የሞገድ ርዝመቶች ላይ ያሉ ቀለሞች ፎቶኖች በረዥም የሞገድ ርዝመት ከሚገኙት ይልቅ በከባቢ አየር ውስጥ ተበታትነው ይረበሻሉ።

ብርሃን ሳይቋቋም በሚንቀሳቀስበት ጠፈር ውስጥ ፎቶኖቹን (photons) የሚያዛባ ምንም ነገር የለም። ፀሐይ እንደ ነጭ ብርሃን ኳስ ትታያለች። ይህም የእኛ ኮከብ "እውነተኛ ቀለም" ነው።

ሆኖም የፀሐይ ጨረር በምድር ከባቢ አየር ውስጥ ሲያልፍ በአየር ውስጥ ያሉት ሞለኪውሎች የፎቶኖቹን የአጭር የሞገድ ርዝመት ያዛባሉ።

ረዘም ያለ የሞገድ ርዝመት ባለው ፕሪዝም ላይ ያሉት ቀለሞች በቀላሉ ወደ ዓይኖቻችን ይደርሳሉ።

ዘ አስትሮኖመርስ ዲያሪ የተባለ ድረ ገጽን የሚያስተዳድረው ኤንጅል ሞሊና "ከባቢ አየር እጅግ በጣም ኃይለኛ የሆነውን የብርሃን ጨረር ክፍልን ያግዳል። በተለይም ደግሞ ከአልትራቫዮሌት እና ከሰማያዊው የሚሆነውን" በማለት ይገልጻል።

"ስለዚህ እንደ ሞቃታማ አምፖል፣ ፀሐይ በከባቢ አየር የተወገዱ ቀዝቃዛ ቀለሞች ሳይኖራት በምድር ላይ ትታያለች። ሞቅ እያለች ወደ ቢጫ እየተጠጋች ትታያለች።"

በኡራጓይ የሪፐብሊክ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ፈለክ ትምህርትን የሚያስተምሩት ጎንዛሎ ታንክሬዲ ለቢቢሲ እንደገለፁት ከአረንጓዴ እስከ ቫዮሌት ያሉ የአጭር ሞገድ ርዝመቶች ቀለሞች ከተዋጡ በኋላ የፀሐይ ብርሃን ቢጫ በሆነው በቀለም ህብረ ህዋሱ መካከል ላይ ይቀመጣል።

አረንጓዴ ፀሐይ?

ፀሐይ አረንጓዴ ናት የሚሉ የበይነመረብ ወይም የማህበራዊ ሚዲያ ጽሑፎች አጋጥሞት ይሆናል።

ጎንዛሎ ታንክሬዲ ይህ የመነጨው እኛ የፀሐይ ህብረቀለም ያለው የሶላር ስፔክትረም ብንሠራ በአረንጓዴው ቀለም አካባቢ ከፍታ ያለው ተራራ መስሎ በመታየቱ ነው ይላሉ።

የሰው አይን የፀሐይ ጨረር ቀለሞች መለየት አይችልም። ልዩነቱን ሊያሳዩ የሚችሉ መሣሪያዎች ግን አሉ። ውጤቱ በአረንጓዴ ውስጥ በጣም ኃይለኛ እንደሆነ ያዩታል።

ጎንዛሎ ታንክሬዲ "ሆኖም እኛ እንደ ሰማያዊ ያሉ አጫጭር የሞገድ ርዝመቶችን ከዚያ ካስወገድን ጫፉ ወደ ቢጫ ቀለም ይዛወራል" ብለዋል።

"ይህ ዝርዝርም ለምን ቢጫ ፀሐይ በምድር ላይ እንደምንመለከት ለማብራራት ይረዳል።"

የፀሐይ መጥለቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እና ቀዩስ የፀሐይ መጥለቅ?

ፀሐይ ሲወጣ ወይም ሲጠልቅ በአድማስ ቅርብ በሆነ ቦታ ላይ ይገኛል። ይህም የፀሐይ ጨረሮችን ብዛት ባለው የከባቢ አየር ሞለኪውሎች ውስጥ እንዲያልፍ ያደርገዋል።

ይህም የሰማያዊ ቀለምን የበለጠ ማዛባት በማስከተል ረዣዥም የሞገድ ርዝመት ያላቸው ቀይ እና ብርቱካናማው የበለጠ የፀሐይን ገጽታ እንዲቆጣጠሩ ያስችላቸዋል።

ክስተቱ ስም አለው። በአስራ ዘጠነኛው ክፍለዘመን የብሪታንያ የፊዚክስ ሊቅ ሎርድ ሬይሌይ የተሰየመ ሬይሌይ ስካተሪን ይባላል።

ፀሐይ በሰማይ ላይ ሲጓዝ ከምድር ጋር ያለው ማዕዘኗ ያለማቋረጥ ይለወጣል። ይህም የቀይ የፀሐይ መጥለቅን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ቀለሞችን ይሰጠዋል።

ይህ ጽሑፍ ስለአስደናቂ ኮከባችን አንድ አስደሳች ነገር እንዳስተማርዎት ተስፋ እናደርጋለን። እባክዎን ቴሌስኮፕ ወይም አጉሊ መነጸርም እንኳን ተጠቅመውም ቢሆን ፀሐይን ግን በቀጥታ ማየት የለብዎትም። ምክንያቱም ይህ በእይታዎ ላይ የማይጠገን ጉዳት ከማስከተል አልፎ ዓይነ ስውርነትን ሊያስከትል ይችላል።