ፈረንሳይ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ‘አባያ’ ቀሚስ እንዳይለብሱ ልትከለክል ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
በፈረንሳይ ኢስላማዊው 'አባያ' ቀሚስ በትምህርት ቤቶች ውስጥ መልበስን ልታግድ ነው።
አባያ ከወገቡ ሰፋ ያለ ሙሉ ሰውነትን የሚሸፍን ልብስ ሲሆን ወንድ ሙስሊሞች ከሚለብሱት ጀለቢያ ጋር የሚመሳሰል ነው።
የፈረንሳይ ትምህርት ሚኒስቴር እንዳለው ከሆነ ይህ ክልከላ ከመጪው የትምሀርት ዘመን መስከረም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።
ፈረንሳይ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን አለባበሶች በመከልከል ትታወቃለች።
ከ10 ዓመት በፊትም በተመሳሳይ ሒጃብ በትምህርት ቤቶች እንዳይለበስ ማገዷ ይታወሳል።
“ወደ ክፍል ሲገባ የትኛው ተማሪ የትኛውን ሃይማኖት እንደሚከተል ማወቅ የለብንም” ብለዋል የትምህርት ሚኒስትሩ ጋብሪየል ኣታል።
ሚኒስትሩ ጨምረው ለፈረንሳይ ኢኤፍዋን (TF1) ቴሌቪዥን ሲናገሩ “በዚህ የተነሳ አባያን ከመጪው መስከረም ጀምሮ ከልክያለሁ” ብለዋል።
ሴት ሙስሊሞች የሚያዘወትሩት አባያ ሙሉ ቀሚስ በፈረንሳይ በትምህርት ቤቶችና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሊከለከል ይገባል ወይስ የእምነት ነጻነትን መጋፋት ነው በሚል ሰፊ ክርክሮች ሲደረጉ ቆይተዋል።
ቀኝ አክራሪዎች የፈረንሳይን ከሃይማኖት ነጻ (ሰኪዩላር) የአስተዳደር ፍልስፍናን የሚቃረን ነው ሲሉ፣ ግራ ዘመሞች ግን የእምነት ነጻነትን ይጋፋል ሲሉ ተከራክረዋል።
ፈረንሳይ እንደ አውሮፓዊያኑ በ2010 ጀምሮ ሙሉ ፊት የሚሸፍን ኢስላማዊ ልብስ እንዳይለበስ መከልከሏን ተከትሎ ተቃውሞ መቀስቀሱ አይዘነጋም።
ፈረንሳይ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሃይማኖታዊ ምልክቶች በትምህርት ቤቶች አካባቢ እንዳይንጸባረቁ ስትከለክል ቆይታለች። ቀደም ባሉ ዘመናት ትልልቅ የአንገት መስቀሎች በትምህርት ቤቶች አካባቢ እንዳይጠለቁ አግዳ ቆይታለች።
ባለፉት ዓመታት ደግሞ የሙስሊም ሂጃብና የአይሁዳዊያን ኪፓን ከልክላለች። ሆኖም አባያ ቀሚስ ሃይማኖታዊ ምልክት ተደርጎ አይታሰብ ስለነበር ሳይከለከል ዘልቋል።
በኢማኑኤል ማክሮን በቅርብ የተሾሙት የ34 ዓመቱ የፈረንሳይ የትምህርት ሚኒስትር ዉሳኔያቸው የጸና እንደሚሆን አረጋግጠዋል።
የፈረንሳይ ብሔራዊ ሙስሊም ማኅበር (ሲኤሲኤም) አባያ ሃይማኖታዊ ምልክት ተደርጎ መወሰድ አልነበረበትም ሲል ውሳኔውን ተቃውሟል።
ፈረንሳይ ከ5 ሚሊዮን የማያንሱ ሙስሊሞች የሚገኙባት አገር ናት።












