በየድረ ገጹ የሚከተሉን ‘ኩኪስ’ ምንድን ናቸው? አሉታዊ ጎንስ አላቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
‘ከኩኪ ጋር ይስማማሉ?’ የሚለውን ጥያቄ ማንበብ ሳያሰለችዎ አይቀርም።
እየጎበኙት ያለው ድረ ገጽ ‘ኩኪስ’ የሚል አማራጭ ያመጣል።
አንዳንድ ድረ ገጾች ለጥያቄው መልስ ሳይሰጡ እንዲያልፉ አይፈቅዱም።
Cookies ወይም ኩኪዎች አንድን ድረ ገጽ የሚጎበኙ ሰዎችን ሳይታክቱ ይከታተላሉ።
በድረ ገጹ ላይ ምን እንደሠሩ፣ የት ሆነው ድረ ገጹን እንደጎበኙ፣ ድረ ገጹን ለመጎብኘት ምን ዓይነት ስልክ እንደተጠቀሙ፣ ከአንዱ ድረ ገጽ ወደ የትኛው እንደሄዱ እና ሌሎችም መረጃዎችን ይሰበስባሉ።
ኩኪስ ለምን አስፈለጉ? ለሚለው ጥያቄ አወንታዊም አሉታዊም መልስ አለው።
አወንታዊው፣ ኩኪ በመጠቀም ድረ ገጽ ሠሪዎች ሰዎች ምን ዓይነት መረጃ እንደሚፈልጉ በመገንዘብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላቸዋል።
አሉታዊው፣ ኩኪ በመጠቀም ሰዎች በድረ ገጾች ላይ የሚያስሱትን መረጃ መሠረት በማድረግ፣ በፍላጎታቸው ላይ ያነጣጠረ ማስታወቂያ (Targeted Advertisement) ለማዘጋጀት እና ለመቅረብ ጥቅም ላይ ይውላል።
ለምሳሌ የቴክኖሎጂ ዘገባ ማንበብ ቢያዘወትሩ፣ ቴክኖሎጂ ነክ ይዘቶች በብዛት ወደ ገጽዎ እንዲመጡ ይደረጋል። ወይም ደግሞ እንደ ክሮም ያሉ ኢንተኔት ማሰሻ መተግበሪያ ተጠቅመው የሚሸጥ ስልክ ብለው ቢፈልጉ ፌስቡክ ላይ የሚመጣልዎ የስልክ ሽያጭ ማስታወቂያ ሊሆን ይችላል።
ኩኪ አልፈልግም ካሉ ድረ ገጹ የበይነ መረብ እንቅስቃሴዎን መመዝገብ አይችልም።
ስለ ኩኪዎች አስፈላጊነት ማብራሪያ የሰጠን የአይኮግ ላብስ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ጌትነት አሰፋ እንደሚለው፣ ኩኪ ዳታዎች “መረጃ አከማች” ናቸው።
“ጥቃቅን መረጃ የያዙ የጽሑፍ ፋይሎች” ሲል ይገልጻቸዋል።
በሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) እንዲሁም ተያያዥ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ የሚሠራው ተቋም መሥራች የሆነው ባለሙያው እንደሚያስረዳው፣ ኩኪዎች የአሰሳ ታሪክ (Search History) መዝጋቢ ሆነው ያገለግላሉ።
ምን አነበብን? ምን ሠራን? የትኛውን ማስፈንጠሪያ ተጫንን? የቱ ትኩረታችንን ሳበን? የሚለውን እንደ አንድ መረጃ አድርገው ያስቀምጣሉ።
ከግል መረጃ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ግን ጥያቄ ይነሳባቸዋል።
‘ኩኪስ’ ምን ይጠቅማሉ?
ኩኪዎችን የሚጠቀሙት ድረ ገጾች ናቸው።
መረጃ ስናስስ ብቻ ሳይሆን ማስፈንጠሪያ ስንጫን እንዲሁም ከአንድ ድረ ገጽ ማስፈንጠሪያ ተከትለን ወደ ሌላ ድረ ገጽ ስንሄድም ‘ዱካችንን’ ተከትለው መረጃ (Data) ያስቀምጣሉ።
ጌትነት ‘Data Keeper’ ሲል ነው የሚገልጻቸው።
ፕሮግራመሮች፣ መረጃ ማሰሻ ድርጅቶች እና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ያንን መረጃ ተመርኩዘው “ለተጠቃሚዎች ተስማሚ የሆነ መረጃ ይሰጣሉ” ሲል ያስረዳል።
“በመልካም ከታየ ጥሩ ነው። ስለ አንድ ነገር ጥናት ስናደርግ ስለዚያ ጥናት ድረ ገጹ ከጀርባ መረጃ ይኖረዋል። የፈለግነውን መረጃ ይዞ ሌላ መረጃ ስንፈልግ ቶሎ ይሰጠናል። በፍጥነት የምንፈልገውን መረጃ እናገኛለን ማለት ነው።”
የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን እንዲሁም የተለያዩ አገራት ሕግ አውጪዎችን የሚያሳስበው የግል መረጃ ባልተገባ ሁኔታ መሰብሰቡ፣ መከማቸቱ እና ጥቅም ላይ መዋሉ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
‘ኩኪስ’ ያሰጉናል?
በኦስትሪያዊው የግል መረጃ ደኅንነት ባለሙያ ማክስ ሸርምስ የሚመራ የመረጃ ደኅንነት ቡድን ከሁለት ዓመት በፊት ኩኪዎችን በተመለከተ ቅሬታ አሰምቷል።
በተለይም ‘ኩኪስ አንፈልግም’ የሚሉ ሰዎችን አማራጭ የሚያሳጡ ድረ ገጾችን ወቅሷል።
ጉግል ለማስታወቂያ የሚውሉ ኩኪዎች የሚያቀርቡ ድረ ገጾች ላይ ገደብ ጥሏል። ወደ ሦስተኛ ወገን የሚሻገሩ ኩኪዎችን እስከነጭራሹ እንደሚያስወግድም ማስታወቁ ይታወሳል።
ተጠቃሚዎችን ከድረ ገጽ ወደ ድረ ገጽ የሚከተሉ የሦስተኛ ወገን ኩኪዎች በአፕል፣ ማይክሮሶፍት እና ሞዚላ ታግደዋል።
ጌትነት እንደሚለው፣ ኩኪዎች የሰዎችን መረጃ መዝግበው ምርት እና አገልግሎት ለመሸጫነት መዋላቸው አሉታዊ ጎናቸው ነው።
ለምሳሌ ጫማ ለመግዛት ድረ ገጽ ላይ ፈለጉ እንበል። ይህንን ፍለጋ አጠናቀው ጥሩ ሬስቶራንት ሲፈልጉ፣ ያልጠበቁት የጫማ ማስታወቂያ ይመጣል።
“ባንፈልገውም ማስታወቂያው ይመጣል” የሚለው ጌትነት፣ “ያንን ጫማ እንድገዛ በተቻለ መጠን ቀኑን ሙሉ ‘ይጨቀጭቁናል’። በከፈትነው ቁጥር ያ ጫማ ነው የሚመጣው። ይህም የሚሆነው ቀደም ብለን በይነ መረብ ላይ ጫማ ስለፈለግን ብቻ ማለት ነው” ሲል ያክላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህ ከፍ ሲል ደግሞ የግል መረጃችን ያለእኛ ፈቃድ መከማቸቱ ነገሩን አሳሳቢ ያደርገዋል።
ኩኪዎች ድረ ገጾች እንዲያስታውሱን ይጠቅማሉ። ለምሳሌ የበይነ መረብ ግብይትን ለማሳለጥ ይውላሉ።
የበይነ መረብ መረጃ መንታፊዎች የግል መረጃችንን እንዲመዘብሩት ሊያጋልጡንም ይችላሉ።
ጌትነት የሚገልጸው “ባለ ሁለት ስለት ቢላ ነው። ቢላ ሽንኩርት ይከፋል፤ ሰውም ይጎዳል። እንደ አጠቃቀማችን ነው የሚወሰነው” በማለት ነው።
ድረ ገጾች በቀጥታ የሚያዘጋጇቸው ኩኪዎች ‘First-party Cookies’ የሚባሉ ሲሆን፣ ታማኝ ድረ ገጽ እየተጠቀሙ እስከሆነ ድረስ የተሻለ አማራጭ ያቀርባሉ።
አንድ ሰው ከሚጠቀመው ድረ ገጽ ውጭ የሆነና አብዛኛውን ጊዜ ለሦስተኛ ወገን ማስታወቂያ የሚያጋልጠው ደግሞ ‘Third-party Cookies’ ይባላል። ይህም የግል መረጃችንን ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ በመስጠት ይተቻል።
በሌላ በኩል ‘Zombie Cookies’ የሚባሉት ተጠቃሚዎች ፈቀዱም፣ አልፈቀዱ የሚከታተሉ ናቸው። ተጠቃሚዎች ቢያጠፏቸው እንኳን ተመልሰው ይመጣሉ።
በስልካችን ‘ሴቲንግ’ ውስጥ ‘ፕራይቬሲ’ ወደሚለው ክፍል በመግባት ፈቃድ መከልከል የሚቻል ሲሆን፣ ከኮምፒውተራችን ላይ ‘ኩኪስ’ በየጊዜው ማስወገድም ሌላው አማራጭ ነው።












