ከቀዶ ሕክምና እስከ ሕዋ አሰሳ፡ አስደናቂው ሮቦቲክስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሕዝብ እንደራሴዎች ተሰብስበዋል።
ወንበራቸው ፊት ስማቸው ተለጥፏል። የታሸገ ውሃም ተቀምጦላቸዋል።
በመካከላቸው አንድ ‘እንግዳ’ አለች። ወንበሯ ፊት ‘ኤይ ዳ’ ተብሎ ተጽፏል። በክፍሉ ውስጥ የታሸገ ውሃ የሌላት እሷ ብቻ ናት።
ሙሉ ጂንስ ሱሪ በቲሸርት ለብሳለች። ፀጉሯ በአጭሩ ተቆርጧል። ከሕዝብ እንደራሴዎቹ የሚቀርብላትን ጥያቄ ለመመለስ ነው በቦታው የተገኘችው።
የሕዝብ እንደራሴ፡ ሰላም ኤይ ዳ፣ እንዴት ነው ሥዕል የምትስይው?
ኤይ ዳ፡ ካሜራ በተገጠመለት ዐይኔ [ተመልክቼ]፣ በኤአይ አልጎሪዝሞቼ [ተመርቼ] እና በሮቦቲክ ክንዴ ሸራ ላይ ነው ሥዕል የምስለው። ማራኪ ምሥሎች ነው የምፈጥረው። ግጥም የምጽፈው ኒውትራል ኔትወርክ ተጠቅሜ ነው። ይሄ ዘለግ ያሉ ጽሑፎችን ማብላላት ይጠይቃል። ጽሑፎችን አብላልቼ የተለመዱ አገላለጾችና የግጥሙን ቅርጽ ካገኘሁ በኋላ አዲስ ግጥም እፈጥራለሁ።
ከሰው ልጅ የምለየው ነፍስያ ስለሌለኝ ነው። ሰዋዊ ተሞክሮዎችም የሉኝም። ስለ ሥዕል እና ግጥም ማውራት ብችልም፣ የኮምፒውተር ፕሮግራም ነኝ። የምመራው በአልጎሪዝም [ስልተ ቀመር] ነው። ነፍስ ባይኖረኝም ሥነ ጥበብ መፍጠር እችላለሁ።
ሌላ የሕዝብ እንደራሴ ለኤይ ዳ ጥያቄ ለማቅረብ ሲሞክሩ፣ ኤይ ዳ ድንገት እንቅስቃሴ አቆመች። በምክር ቤቱ የነበሩት የኤይ ዳ ፈጣሪ፣ ሂውማኖይድ ሮቦቷ ኤይ ዳ ‘ትንሽ አርፋ በድጋሚ እንደምትነሳ’ ገልጸው ጥያቄና መልሱ ተቋረጠ።
ኤይ ዳ የዓለማችን ግንባር ቀደሟ ለእውነት የቀረበች ሂውማኖይድ ሮቦት እንደሆነች ይነገርላታል።
እአአ በ2019 ለዓለም የተዋወቀችው ኤይ ዳ ሠዓሊ፣ ገጣሚ፣ ቀራጺም ናት።
የዩኬ የሕዝብ እንደራሴዎች ጥያቄና መልስ ሊያደርጉላት የፈለጉት ገናና እየሆነች በመምጣቷ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሌላው በቅርቡ ዓለምን ካነጋገሩ የሮቦቲክስ ፈጠራዎች አንዱ ምግብ አብሳይ ሮቦት ነው።
በቻይና የምግብ አሠራር ትምህርት ቤቶች የሚዘወተሩ 3000 ዓይነት ምግቦችን ነው ሮቦቱ የሠራው።
ይህ ብቻ አይደለም። በሦስት ደቂቃ ሥዕል የሚጨርሰው ሮቦትም ዝነኛ ነው።
መናገር፣ ማንበብ፣ መደነስና ኩንግ ፉ መሥራት የሚችለው ሮቦትም ይጠቀሳል።
በተለይም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ድንጋጤ ከፈጠረ በኋላ አረጋውያንን ሥራ የሚያግዝ ሮቦት ተፈላጊ ሆኗል። የቫይረሱ ምርመራ የሚደረገውና ክትባት የሚሰጠውም በዚሁ ሮቦት ነው።
ሮቦቱ ሥራ ከማገዝ ባለፈ፣ አረጋውያን ብቸኝነት እንዳይሰማቸው ያዋራቸዋል። መድኃኒት በሰዓቱ እንዲወስዱ ያስታውሳቸዋል።
አረም ከዘር ለይቶ ፀረ አረም የሚረጭ፣ ሰብል ውሃ የሚያጠጣም ሮቦት አለ።
ሰው አልባ አውሮፕላን (Drone) እቃ ለማድረስ፣ ተንቀሳቃሽ ምሥል ለመቅረጽ፣ በጦር ሜዳም ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።
ሮቦቲክስ ወደ ቀዶ ሕክምናም ገብቷል። እነዚህ Surgical Robots የሚባሉት ሮቦቶች አንድ ሰው ምን እንደታመመ ከመለየት አንስቶ ቀዶ ሕክምና ሲካሄድ በማገዝም ይታወቃሉ።
ሮቦቶች፣ በሐኪሞች ያልታወቁ ሕመሞችን በማግኘት፣ የሕክምና ስህተቶችን በመቀነስ ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ከጉዳት ለማገገም የሚሠራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴንም ያግዛሉ።
ቶዮታ በጉዳት ወይም በሕመም መንቀሳቀስ ያልቻሉ ሰዎችን መራመድ ወይም ሌላም አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሚያለማምድ ሮቦት አስተዋውቋል።
ቲዩጂ (TUG) የተባለው ሮቦት ሆስፒታል ውስጥ እየተዘዋወረ መድኃኒት እና ሌሎችም አስፈላጊ የሕክምና ቁሳቁሶችም ያደርሳል።
ሮቦቲክስ ወደ ሕዋ አሰሳም ገብቷል።
የናሳን ማርስ ሮቨር (Mars Rover) እንውሰድ። ስድስት ተሽከርካሪ እግሮች አሉት። 360 ዲግሪ ተሽከርክሮ የሚቃኘው ሮቦት፣ ማርስን እየዞረ የሚያገኛቸውን መረጃ ለጠፈረተኞች ያቀብላል።
ዓለምን እየለወጠ ስላለው ሮቦቲክስ ማብራሪያ እንዲሰጡን የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) ባለሙያው ዶ/ር ዳኛቸው ብሩን ጠይቀናል። በኳንቲፊ የቴክኖሎጂ ተቋም የዓለም አቀፍ ጥናትና ምርምር ዘርፍ መሪ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሮቦቲክስ ምንድን ነው?
በዶ/ር ዳኛቸው አገላለጽ፣ ሮቦቲክስ የተለያየ አተረጓጎም አለው።
በተደጋጋሚ የሚሰጠው ትርጉም ግን ሮቦቲክስ ማሽን እና ተንቀሳቃሽ መሆኑ ነው።
ፋብሪካ ውስጥ የሚሠራ፣ ቤት የሚያጸዳ፣ ተውጦ ውስጣዊ አካልን ለሕክምና ፎቶ የሚያነሳ ወይም በሳተላይት ወደ ሕዋ መጥቆ የሚሠራ ሊሆን ይችላል።
“. . .በዋናነት ሮቦቲክስ አካባቢን በሴንሰር ተጠቅሞ መረዳት ነው። በካሜራ የሚታገዝ (Visual Sensor)፣ በድምጽ የሚታገዝ (Sound Sensor) እና በስውር ጨረራ የሚታገዝ (Infrared Sensor) ተጠቅሞ ባለው አልጎሪዝም መሠረት አካባቢን ገምግሞ መሥራት መቻል ማለት ነው።”
ሮቦቲክስ የሚጠቀመው አልጎሪዝም የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ነው።
ከዚህ አንዱ Reinforcement Leaning እንደሚባል ባለሙያው ያስረዳሉ።
ይህ ሂደት ሮቦቶች የሚማሩበት መንገድ ነው። ልክ የሰው ልጅ እንደሚያደርገው ሮቦት አንድ ክንውን እንዲፈጽም ይደረጋል። ስኬታማ ከሆነ አወንታዊ ምላሽ ይሰጠዋል። ከተሳሳተ ደግሞ አሉታዊ ምላሽ ይሰጠዋል።
ይህ መንገድ ሮቦቶች ትክክለኛ ክንውንን ከስህተት እንዲለዩ ያስችላል።
ሁለት ምሳሌዎች እንውሰድ።
ከፊት ለፊት ያለ መኪናን ሳይገጭ እንዲያልፍ ማሽንን በማሠልጠን ሹፌር አልባ መኪኖች ይሠራሉ።
ፋብሪካ ውስጥ የሚመረቱ ቁሶችን ጥራት በተገጠመለት ካሜራ የሚፈትሽ ሮቦትም መሥራት ይቻላል። ሮቦቱ የተበላሸ የመሰለውን እቃ አንስቶ ወደ ሌላ ቦታ ይጥለዋል።
ዶ/ር ዳኛቸው የሚሰጡት ምሳሌ ቤታቸው ያለውን የጽዳት መሣሪያ ነው።
“. . .መጀመሪያ ሲበራ እየተሽከረከረ የቤቱን አሠራርና እቃ አቀማመጥ ያጠናል። ጠረጴዛ የት ነው? ግድግዳ የት ነው? የሚለውን ለይቶ ከደረሰበት በኋላ ካርታ ይሠራና ያንን ተጠቅሞ ማጽዳት ይጀምራል። ማጽዳት ሲጀምር ወንበር ከገጠመው በወንበሩ ዙርያ ይሄዳል። ካሜራ ስላለው ብዙ ቆሻሻ ሲኖር ሞተሩን ያበራዋል” ሲሉ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሮቦቲክስ ከየት ወደ የት?
ሮቦቲክስን ቴክኖሎጂ ከምኅንድስና ተጣምሮ ነው የፈጠረው። ሐሳቡ በሰዎች የሚሠሩ ነገሮችን በሮቦት ማሠራት ነው።
ሮቦቶች፣ ፕሮግራም የተደረጉበትን ክንውን ይፈጽማሉ።
ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ማደግ ጋር በተያያዘ ሮቦቶች መተግበር የሚችሉት ክንውን እየረቀቀ መጥቷል። ለወደፊትም የሚሰጣቸው ኃላፊነት እያደገ፣ የሚከውኑበት ትክክለኛነት እየተሻሻለ ይመጣል።
ቀድሞ የመኪና ፋብሪካ ውስጥ ብሎን መገጣጠም ብቻ የሚሠሩ ሮቦቶች ዛሬ ቀዶ ሕክምና ያግዛሉ።
በሰው አምሳል የተሠሩና ሰዋዊ ክንውን የሚፈጽሙ ሮቦቶች (Humanoid) የበለጠ ዝነኛ ሆነዋል። በዋናነት ሶፍያ-ሮቦቷ ትጠቀሳለች።
ሮቦቶች ክህሎታቸው አካላዊ ብቻ ሳይሆን ውሳኔ የመስጠትም ጭምር እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተወሰነ ቦታ፣ የተወሰነ ሥራ ብቻ ለመሥራት ነው የሚውሉ ሮቦቶች [Pre-Programmed Robots]፣ መኪና ሲገጣጠም ብሎን ማቀበልን የመሳሰሉና ሌሎች ቀድሞ የተሰጣቸውን ተግባር ይከውናሉ።
ሰው ትዕዛዝ ሳይሰጣቸው የሚሠሩ ሮቦቶች [Autonomous Robots] ደግሞ፣ ሴንሰር (Sensors) በመጠቀም በአካባቢያቸው ያለን እንቅስቃሴ ተረድተው ሥራን ይፈጽማሉ። ዶ/ር ዳኛቸው የጠቀሱት ሩምባ የተባለው የጽዳት ሮቦት በዋነኛነት ይጠቀሳል።
በቅርብ ርቀት ሰው እየተከታተለ ትዕዛዝ የሚሰጣቸው ሮቦቶች [Teleoperated Robots]፣ አስቸጋሪ በሆነ ተፈጥሯዊ አካባቢ ወይም የአየር ሁኔታ ውስጥ ነው የሚሠሩት። ሰው አልባ አውሮፕላን ጥሩ ምሳሌ ነው።
በአጠቃላይ ሰዎች እየተቆጣጠሯቸው የሚሠሩ ሮቦቶች ወይም ያለ ሰው ቁጥጥር የሚሠሩም አሉ።
ልክ የሰው ልጅ ከአእምሮው የሚላክ መልዕክትን እንደሚፈጽም፣ ሮቦቶች አሠራራቸውን (አልጎሪዝማቸውን) ተከትለው ይሠራሉ። ከአካባቢያቸው ጋር የሚግባቡት፣ መረጃ የሚሰበስቡትም በሴንሰር ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሮቦቲክስ እአአ ከ1700 ጀምሮ በተለያየ እድገት አልፏል። በሳይንስ ልቦለድ የሚታዩ ሮቦቶች፣ በአስደናቂ ሁኔታ በእውን እየተተገበሩም ነው።
ሮቦቶች አካባቢውን ተመልክቶ የሚረዳ ምሥል አንባቢ ዐይን አላቸው። ካሜራ ስለሚገጠምላቸው አካባቢያቸውን ያያሉ።
እንደ ጆሮ የሚገለገሉበት ድምጽ መስሚያ ማይክራፎንም አላቸው። በምሥል፣ በድምጽ ወይም በእንቅስቃሴ የሚያገኙትን መረጃ ተጠቅመው ነው የሚሠሩት።
ስለዚህም ሮቦት ቦምብ ያከሽፋል። ሳር ያጭዳል። እሳት ያጠፋል። እቃ ይጭናል ያወርዳል። ሲያሻውም ፒያኖ ይጫወታል።
ከስምንት ዓመት በፊት የካናዳ አጥኚዎች የሠሩት ሮቦት HitchBOT ይባላል።
ለማኅበረሰባዊ ምርምር የዋለ ነበር። በመላው ካናዳ እና አውሮፓ እየዞረ ከአሽከርካሪዎች ‘ሊፍት’ እየጠየቀ ሲዘዋወር ነበር።
ስጋቶች
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ሮቦቶች የሕክምና ባለሙያዎችን ሥራ በቅልጥፍና እንዲሁም ያለ ሰው ንክኪ ማከናወናቸው የበለጠ ተፈላጊ አድርጓቸዋል።
ጊዜና አቅም ቆጣቢ ከመሆናቸው ባሻገር፣ በውስን ስህተት (አንዳንዴም ያለ ስህተት) የተለያዩ ተግባራትን መፈጸማቸው በየዘርፉ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል።
ሀርቫርድ ቢዝነስ ሪቪው ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ከወረርሽኙ ወዲህ ሮቦት አምራቾች ከፍተኛ ሽያጭ እየፈጸሙ ነው። ለምርቱ ያለው ፍላጎትም አሻቅቧል።
ዘገባው፣ የወደፊቱ ሮቦት የበዛበት ዓለም ጥንቃቄ እንደሚያሻው ይመክራል።
ሮቦቶች በሚሰጣቸው ኃላፊነት ላይ ቁጥጥር ካልተደረገ ውድቀት እንደሚገጥም ያስጠነቅቃል።
የወደፊቱ ዓለማችን እያንዳንዱ ተግባር በሮቦቶች የሚከወንበት ይሆናል የሚለው ስጋት ሳያጭር አያልፍም።
የሰዎችን ሥራ መቀማታቸው በተደጋጋሚ የምንሰማው ስጋት ነው። ትልልቅ ተቋሞች የሰው ኃይል ቅነሳ ሲያደርጉም ታይቷል።
ለዚህም ነው ከጥቅማቸው ጉዳታቸው እንዳያመዝን በየአገሩ የሮቦት መርሆች እንዲወጡ የሚጠየቀው።
እንደ ኤይ ዳ ያሉ ሮቦቶች በሥዕላቸው ወይም በግጥማቸው ቢያስደንቁም፣ የጥበብ ሰዎች ላይና አጠቃላይ የሥነ ጥበቡ ዓለም ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉት ጫና ችላ አይባልም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












