ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና በሴቶች ወርቅ ታግዛ ከዓለም ስድስተኛ ሆና አጠናቀቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እሑድ ምሽት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ በዘጠኝ ሜዳሊያ ከዓለም ስድስተኛ ሆና አጠናቀቀች።
በመጨረሻው የውድድሩ ምሽት በወንዶች 5 ሺህ ሜትር ሩጫ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል ሳይቀናቸው ቀርቷል።
በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከሜዳሊያ ውጭ ሆነዋል።
በ10ሺህ ሜትር ሴቶች ከአንድ ሶስት ተከታትለው የገቡት አትሌቶች እንዲሁም በማራቶን የወርቅና ብር ሜዳሊያ ያመጡት ሴት አትሌቶች ለኢትዮጵያ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
በ5 ሺህ ሜትር ጉዳፍ ፀጋይ ወርቅ፣ ለተሰንበት ግደይ ብር፣ እጅጋየሁ ታየ ደግሞ ነሐስ አምጥተዋል።
በሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች አማኔ በሪሶ እና ጎትይቶም ገብረስላሴ ተከታትለው በመግባት የወርቅ እና ብር ሜዳሊያ አግኝተዋል።
በወንዶች 10 ሺህ ሜትር ውድድር ሰለሞን ባረጋ ሶስተኛ በመውጣት ለሃገሩ የነሐስ ሜዳሊያ ሲያስገኝ፤ በሴቶች 1500 ሜትር ድሪቤ ወልተጂ ሁለተኛ ሆና የብር ሜዳሊያስ አስገኝታለች።
በወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤቱ ለሜቻ ግርማ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ ወርቅ ለማምጣት ቢጥርም ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ብር ማግኘት ችሏል።
በመጨረሻው ቀን በተካሄድ የወንዶች ማራቶን ልዑል ገብረስላሴ ሶስተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ነሐስ አግኝቷል።
ኢትዮጵያ በጠቅላላው ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን ሰብስባ ከአፍሪካ ሁለተኛ ከዓለም ስድስተኛ ሆና አጠናቃለች።
ኬንያ ደግሞ በጠቅላላው 10 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም አምስተኛ ሆና ጨርሳለች። የጎረቤት አገር ኬንያ አትሌት የሆነችው ፌይዝ ኪፕዬጎን በ1ሺህ500 እና 5ሺህ ሜትር የበላይነትን ይዛ እንዲሁም ሜሪ ሞራ በ800 ሜትር ለአገራቸው ወርቅ አስገኝተዋል።
አሜሪካ በ12 ወርቅ፤ በጠቅላላው ደግሞ 29 ሜዳሊያዎችን በማከማቸት ከዓለም ቁንጮ ሆና ስታጠናቅቅ ካናዳ፣ ስፔን እና ጃማይካ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
የሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ያዘጋጀችው የዓለም ሻምፒዮና በርካታ አስደናቂ ትዕይንቶች ታይተውበታል።
በ5 ሺህ ሜትር ከ1-3 ተከታትለው የገቡት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በ19ኛው የዓለም ሻምፒዮና ሶስቱንም ሜዳሊያ የወሰዱ ብቸኛ አትሌቶች ናቸው።
ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕየጎን ደግሞ በ1500 እና 5 ሺህ ሜትር ውድድር ወርቅ በማምጣት ታሪክ ፅፋለች።
በመጨረሻው ቀን ውድድር አራት በአራት መቶ ሜትር ውድድር ኔዘርላንዳዊቷ ፌምኬ ቦል በመጨረሻው 20 ሜትር በአስገራሚ ፍጥነት በመግባት ብዙዎችን አስገርማለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቡዳፔስ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የውድድሩ ፈርጥ የነበረው አሜሪካዊው የአጭር ርቀት ተወዳዳሪ ኖዋ ላይልስ ነው።
ላይልስ 100 ሜትር፣ 200 ሜትር እንዲሁም በቡበድን 4X100 ሦስት ወርቅ ይዞ ተመልሷል።
አሜሪካዊቷ ሻካሪ ሪቻርድሰን ከቡዳፔስ ሦስት ሜዳሊያዎችን ይዛ ተመልሳለች። በ100 ሜትር እና በቡበድን 4X100 ሁለት ወርቅ ስታገኝ በ200 ሜትር ደግሞ የነሐስ ባለቤት ሆናለች።
የኖርዌው አትሌት ጃኮብ ኢንገብሪግስተን ኢትዮጵያዊያን እና ኬንያዊያን በሚታወቁበት 5 ሺህ ሜትር ሩጫ የወርቅ ባለቤት ሆኗል።
በ1500፣ በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትሮች ድል ለማግኘት ሙከራ ያደረገችው ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሐሰን በ1500 ነሐስ፤ በ5 ሺህ የብር ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች።












