በውዝግብ ውስጥ ሆኖ ቡዳፔስት ያቀናው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ድል ይቀናው ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአፍሪካ አትሌቲክስ አድናቂዎች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለመከታተል ትኩረታቸውን ወደ ሃንጋሪዋ መዲና ቡዳፔስት አድርገዋል።
ባለፈው ዓመት በአሜሪካዋ ኦሬገን በተካሄደው ውድድር ከዓለም ኢትዮጵያ ሁለተኛ፣ ኬንያ ደግሞ አራተኛ ሆነው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።
ነገር ግን ሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራት በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተገኝተው ነበር።
በኦሬገኑ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ሰባት የአፍሪካ አገራት 28 ሜዳሊያ ሲከፋፈሉ ከኢትዮጵያ እና ከኬንያ ውጪ ቢያንስ አንድ ወርቅ ማምጣት የቻሉት ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ እና ኡጋንዳ ናቸው።
ቡዳፔስት የምታሰናዳው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቅዳሜ ነሐሴ 13/2015 ዓ.ም. ይጀምራል።
በመጀመሪያው ቀን ውድድር በወንዶች የ3000 ሜትር መሰናክል ማጣሪያ የሚካሄድ ይሆናል። የርቀቱ የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ለሜቻ ግርማ ተጠባቂ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በ1500 ሜትር የሴቶች ማጣሪያ እንዲሁም በወንዶች የ10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ይከናወናሉ።
በእነዚህ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የውድድር መስኮች የአገራቸውን ባንዲራ ከሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውስጥ ያካትታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ለመሆኑ በዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች እነማን ናቸው? የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተወዳዳሪዎችን ለማሳወቅ ጊዜ የወሰደበትስ ለምን ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, World Athletics/fb
የፌዴሬሽኑ እና የአሠልጣኞች ውዝግብ
ለዘጠኝ ቀናት በሚቆየው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርካታ የአፍሪካ አገራት ይሳተፋሉ።
ከእነዚህ መካከል በረዥም ርቀት የዓለም ቁንጮ የሆኑት ኢትዮጵያ እና ጎረቤት አገር ኬንያ ይጠበቃሉ።
ባለፈው ዓመት በአሜሪካዋ ኦሬገን ግዛት በዩጂን ከተማ በተካሄደው ውድድር፣ ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛ በመውጣት ከዓመታት በኋላ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧ ይታወሳል።
በአንፃሩ ብዙ የተባለላት ኬንያ ከዓለም አራተኛ ደረጃን ብትይዝም፣ ውጤቱ የአገሪቱን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አንገት ያስደፋ ነበር።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከወራት ልምምድ በኋላ የመጀመሪያ ዙር አትሌቶችን ማክሰኞ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወደ ቡዳፔስት ልኳል።
ለወትሮው በየዘርፉ የሚወዳደሩ አትሌቶች እና ተጠባባቂዎችን ስም በጊዜ የሚያሳውቀው ፌዴሬሽን፣ ዘንድሮ ግን ወደ ቡዳፔስት መብረራቸውን ከማሳወቅ ውጪ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
ፌዴሬሽኑ በኦፊሴላዊ ቴሌግራም ገፁ የመጀመሪያ ዙር ተሳታፊዎች ወደ ውድድሩ ስፍራ መጓዛቸውን ሲያሳውቅ በ3000 ሜትር መሰናክል በወንዶች፣ በ1500 እና በ10 ሺህ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች አትሌቶች መሸኘታቸውን ገልጿል።
ነገር ግን ፌዴሬሽኑ የትኞቹ አትሌቶች በየትኛው ዘርፍ ይሳተፋሉ የሚል ማብራሪያ አሊያም የተጠባባቂዎችን ስም ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ይህ ብዙዎች “ለምን?” ብለው እንዲጠይቁ ምክንያት ሆኗል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአትሌቶች ቡድን ዝግጅትን በቅርበት ሲከታተል የነበረው የአገር ውስጥ ጋዜጠኛ “ፌዴሬሽኑ ውዝግብ አላጣውም” ይላል።
ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው ጋዜጠኛ “የአትሌቶቹ የግል አሠልጣኞች ለብሔራዊ ቡድኑ ተገዢ አለመሆናቸው” ዋነኛው ምክንያት ነው ይላል።
ጋዜጠኛው በተደጋጋሚ የአትሌቶቹን ልምምድ ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አቅንቶ፣ አትሌቶቹ ብቻቸውን ልምምድ ያደርጉ እንደነበር ታዝቧል።
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ስለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን እና ተይይዘው ስለሚነሱ ጉዳዮች የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ እና የቡድኑ የሥልጠና አስተባባሪ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱን ለመጠየቅ ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

“እነዚህ አትሌቶች የጎዳና ላይ ሩጫ [ሮድ ሬስ] እንዲሁም ዳይመንድ ሊግን የመሳሰሉ ውድድሮች ላይ ውጤት የሚያመጡት በግላቸው ሮጠው ነው” የሚለው ምንጫችን “የግል አሠልጣኞች ከአትሌቶቻችን ጋር መሄድ አለብን” የሚል ጥያቄ እንደሚያነሱ ይናገራል።
“የአሠልጣኞች የገቢ ምንጭ አትሌቶቹ ናቸው። አትሌቶቹም ብዙውን ጊዜ የሚመርጡት የግል አሠልጣኞቻቸውን ነው።”
ጋዜጠኛው ልምምድ ለመታደም በሄደበት ወቅት ዮሚፍ ቀጀልቻ በግሉ፤ ሰለሞን ባረጋ እና በሪሁ አረጋዊ በሌላ ወገን፤ ድርቤ ወልተጂም በግሏ ልምምድ ሲያደርጉ መመልከቱን ይገልጻል።
እንደምንጫን በሻለቃ ደራርቱ ቱሉ የሚመራው ፌዴሬሽን ወደ ቡዳፔስት የሚሄደውን ቡድን በጊዜ አለማሳወቁ ዋነኛው ምክንያት ይህ ነው ብሎ ያምናል።
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 200 ገደማ አገራት ይሳተፋሉ። አብዛኛዎቹ አገራት ቡድናቸውን ያሳወቁት ቀደም ብለው ነው። ለምሳሌ ኬንያ በጠቅላላው 57 ሯጮች ወደ ቡዳፔስት እንደምትልክ የገለጸችው ከአንድ ወር ቀደም ብሎ ነው።
የኔዘርላንድስ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቡድኑን ይፋ ሲያደርግ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፋን ሐሰን በ1500፣ በ5000 እና 10000 እንደምትወዳደር ገልጿል።
በተቃራኒው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የመጀመሪያው እና ሁለተኛው ዙር ተጓዦች የትኞቹ እንደሆኑ የታወቀው በዚህ ሳምንት ነው።
አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ለልምምድ የጠራቸው አትሌቶች አንድ ላይ ሥልጠና እንዲያካሂዱ ለማድረግ ተቸግሮ እንደነበር ይታወሳል።
ፌዴሬሽኑ ሐምሌ 6/2015 ለዕጩ አትሌቶች እና አሠልጣኞች በላከው ደብዳቤ “ጥቂት የፌዴሬሽኑን ከሚያከብሩ አትሌቶች በቀር አብዛኛዎቻችሁ የተላለፈውን አገራዊ ጥሪ አክብራችሁ ወደ ካምፕ [አራራት ሆቴል] አልገባችሁም” ማለቱ ይታወሳል።
በዚህ ደብዳቤው አትሌቶች ትጥቃቸውን ይዘው ወደ ካምፕ ካልገቡ እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቁም የሚዘነጋ አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሚጠበቁ አትሌቶች እነማን ናቸው
ምንም እንኳ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተወዳዳሪዎቹን ይፋ ባያደርግም በመካከለኛ እና ረዥም ርቀት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይጠበቃሉ።
በመክፈቻው ቀን ውድድር በ10 ሺህ ሜትር የወንዶች ፍፃሜ ይካሄዳል። ባለፉት ሦስት ውድድሮች ወርቅ ያመጣው ኡጋንዳዊው ጆሹዋ ቼፕቴጌ በርቀቱ የሚጠበቅ አትሌት ነው።
ይህ አትሌት በርቀቱ ዘንድሮም ውጤት ማምጣት ከቻለ ኢትዮጵያውያኑ ጉምቱ የርቀቱ አትሌቶች የኃይሌ ገብረ ሥላሴን እና የቀነኒሳ በቀለን ስኬት ሊደግም ይቃረባል።
በዚህ ርቀት ይወዳደራሉ ተብለው የሚጠበቁት በሪሁ አረጋዊ፣ ሰለሞን ባረጋ እና ይስማውድ ድሉ፤ ቼፕቴጌን ሊፈትኑ እንደሚችሉ እሙን ነው።
በሴቶች ደግሞ የአምናዋ የወርቅ ባለቤት ለተሰንበት ግደይ እና የ5 ሺህ ሜትር ርቀት አሸናፊዋ ጉዳፍ ፀጋይ ትልቅ ግምት የተሰጣቸው ናቸው።
በ5 ሺህ ሜትር የወንዶች ውድድር ጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ቁመተ መለሎው ዮሚፍ ቀጀልቻ ከፍተኛ ተፎካካሪ እንደሚሆን ግምት ተሰጥቶታል። ሐጎስ ገብረሕይወት እና ጥላሁን ኃይሌም ኢትዮጵያን ወክለው ውጤት እንደሚያመጡ ይገመታል።
በሴቶች የ5 ሺህ ሜትር ውድድር የዓለም ሻምፒዮናዋ ጉዳፍ ፀጋይ በምትመራው ቡድን እጀጋየሁ ታዬ፣ መዲና ኢሳ እና ፍሬወይኒ ኃይሌ ተካተዋል። ለተሰንበት ግደይ ተጠባባቂ ሆናለች።
በሴቶች የ1500 እና 5000 ሜትር ውድድሮ ዘንድሮ ድንቅ ብቃቷን ያሳየችው ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕዬጎ ከብዙዎች የአሸናፊነት ግምትን አግኝታለች።
በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ተጠባቂው የ3000 ሜትር መሰናክል ሲሆን፣ የርቀቱ ክብረ-ወሰን ባለቤት ለሜቻ ግርማ ኢትዮጵያ ብዙም ስኬታማ ባልነበረችበት ውድድር ለአገሩ ሜዳሊያ ያመጣል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
በ3000 ሜትር እና 1500 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ተካተዋል።
የሃንጋሪዋ ዋና ከተማ ቡዳፔስት የአየር ፀባይ ለአትሌቶች ከባድ ሊሆን እንደሚችል ምንጫችንን ጨምሮ አትሌቶች እና አሠልጣኞች ከዚህ በፊት ገልጸዋል።
ነገር ግን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በግላቸው በተለያዩ ውድድሮች ስኬታማ መሆናቸው የአትሌቲክሱ ቤተሰብ ተስፋ ሰንቆ እንዲጠብቅ ያደርገዋል።












