ኢትዮጵያዊቷ አትሌት በምን ምክንያት መንገድ ስታ የ380 ሺህ ብር ሽልማት አመለጣት?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሰምበሬ ተፈሪ በቅርቡ በአሜሪካ በተካሄድ የጎዳና ላይ ሩጫ ስትመራ ቆይታ መንገድ በመሳቷ 380 ሺህ የሽልማት ብር ከእጇ ወጥቷል።
በኦሊምፒክ መድረክ አገሯን ሁለት ጊዜ የወከለችው አትሌት ሰምበሬ፤ ከቀናት በፊት በአትላንታ ጆርጂያ በተካሄደ ውድድር ላይ የ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ውድድርን በረዥም ርቀት ስትመራ ቆይታ ነበር።
ይሁን እንጂ ማክሰኞ ሰኔ 27/2015 ዓ.ም. በተካሄው ሩጫ የውድድሩ ፍጻሜ ላይ ያልታሰበው አጋጥሟታል።
ሰምበሬ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ይህን ውድድር በማሸነፏ ዘንድሮም ውድድሩን በበላይነት እንደምታጠናቅቅ ሰፊ ግምት ተሰጥቷ ነበር።
አትሌቷ እንደተገመተው በሰፊ ርቀት ልዩነት ውድድሩን ስትመራ ቆየች። ወደ ፍጻሜው መስመር ስትቃረብ ግን ያልተጠበቀውን ስህተት ሰርታለች።
አትሌት ሰንበሬ ከሯጮች ፊት ለፊት የሚሄደው ሞተር ሳይክል አቅጣጫ ጠቋሚ መስሏት ተከትላው በመሄድ መንገድ ስታ ድሉ ከእጇ ወጥቷል።
የአትሌት ሰንበሬ አሠልጣኝ ኮማንደር ሁሴብ ሽቦ ለቢቢሲ ሲናገሩ “ውድድሩ ወደ ማብቂያው ሲደርስ ሞተሩ ለመቆም ከመንገዱ ወጣ። እሷ ግን መንገድ የሚያሳያት መስሏት ተከትለችው” በማለት ተናግረዋል።
አትሌት ሰንበሬ ከሳተችው መንገድ እስክትመለስ ድረስ ከኋላዋ ሆነው ሲከተሏት ከነበሩት አትሌቶች መካከል ሁለቱ ቀድመዋት ነበር።
“ትክክለኛውን የሩጫ መስመር ከጠቆሟት በኋላ ተመልሳ ሦስተኛ በመሆን ጨረሰች። መንገድ ባትስት ኖሮ በሰፊ ርቀት ነበር የምታሸንፈው” በማለት አሠልጣኙ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Atlanta Track Club
ሰንበሬ አሜሪካ አትላንት ውስጥ ስላጋጠማት ክስተት እስካሁን ያለችው ነገር የለም። ቢቢሲም ባለፉት ቀናት አትሌቷን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
አትሌት ሰንበሬን ስትከተል የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፎቴን ተስፋዬ 30 ደቂቃ ከ43ሰከንድ በሆነ ሰዓት ውድድሩን በቀዳሚነት አጠናቃለች።
ሰንበሬ ከፎቴን በአራት ሰከንዶች ዘግይታ 30፡43 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
አሸናፊዋ አትሌት ሰንበሬ መንገድ ስታ በመሸነፏ አዝኜላታለሁ ብላለች። ፎቴን “በስህተቷ አዝኛለሁ ምክንያቱም ከፊት ሆና ስትመራ ነበር” ስትል ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተናግራለች።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ አትሌት ሰንበሬ ውድድሩን በቀዳሚነት ብታጠናቀቅ ኖሮ ለአሸናፊ አትሌት የተዘጋጀውን 10 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ትሆን ነበር።
ሰንበሬ ባጋጠማት ስህተት ምክንያት ውድድሩን ቀዳሚ ሆና ለመጨረስ የቻለችው አትሌት የ10 ሺህ ዶላር ሽልማት ስትቀበል፤ ሁለተኛዋ ኬንያዊት አትሌት ደግሞ የ5 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ሆናለች።
ከትክክለኛው የሩጫ መስመር ወጥታ የነበረችው አትሌት ሰንበሬ፣ ተመልሳ ወደ ውድድሩ መስመር በመግባት ሦስተኛ ሆና በመጨረሷ የ3 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ሆናለች።
የውድድሩ አዘጋጆች ሰንበሬ የፖሊስ ሞተር ተከትላ መንገድ ስታ ከመስመር ከወጣችበት ቦታ ላይ የወድድሩ የፍጻሜ መስመር ከርቀት ይታይ ነበር በማለት ለአሸናፊነት ተቃርባ እንደነበር ገልጿል።
በእንዲህ ያሉ ታላላቅ ወድድሮች ወቅት አትሌቶች ውጥረት ውስጥ ሊገቡ ስለሚችሉ መመሪያዎችን እና መንገዶችን ሊስቱ የሚችሉበት አጋጣሚ አለ ብሏል።
ሰንበሬን ባጋጠማት ችግር ምክንያት የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው ኤጂሲ ፒችትሪ የመንገድ ላይ ውድድሩ ባሰበው መልኩ ያለ እንከን ባለመጠቀቁ ቅር መሰኘቱን አመልክቷል።
በውድድሮች ላይ ያሚያጋጥሙ ስህተቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ከባድ ዋጋ ሲያስከፍል ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ከዚህ ቀደም አትሌት ሐጎስ ገብረ ሕይወት ውድድር ከመጨረሱ በፊት ያጠናቀቀ መስሎት የአሸናፊነት ደስተውን ሲገልጽ ከኋላው በመጡ ተፎካካሪዎች ተቀድሟል።
በተመሳሳይ በዚሁ ዓመት አትሌት ድርቤ ወልተጂ 200 ሜትር እየቀራት ውድድር የጨረስ መስሏት ከትራክ ወጥታ እንደነበር ይታወሳል።












