በሴቶች የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያ ወርቅ እና ብር አገኘች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ነሐሴ 20/2015 ዓ.ም በተደረገው የሴቶች የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያ ወርቅ እና ብር አገኘች።
በአንደኝነትም ውድድሩን ያጠናቀቀችው አማኔ በሪሶ ሻንኩሌ ስትሆን እሷንም በመከተል ጎይተቶም ገብረ ስላሴ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች።
አማኔ በጠራራማዋ ቅዳሜ ጥዋት በልዩ ጽናት እና ችሎታ 2: 24:23 በሆነ ሰዓት የፍጻሜውን መስመር አልፋ ብቃቷን በአስቸጋሪ ሁኔታ ማሳየቷም ተዘግቧል።
የአምናዋ ሻምፒዮን ጎይተቶም ገብረ ስላሴም 2፡24፡34 ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛነት ስፍራን በመያዝ ድንቅ ብቃት ማሳየቷም ተነግሯል።
ሁለቱ ተወዳዳሪዎች በቡድን ስራ እና ረጅሙን ርቀት በሚያቃጥል ሙቀት ውስጥ ለመሮጥ ያሳዩት ፅናትም አኩሪ እንደነበር ዘገባዎች አስነብበዋል።
አትሌት ጎይተቶም ገብረ ሥላሴ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሴቶች ማራቶን ውድድር 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በመግባት የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች።
ጎይተቶም ገብረ ሥላሴ ከባዱን ውድድር ያሸነፈችው ከዚህ ቀደም በብሪታኒያዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ተይዞ የነበረውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ክብረ ወሰንን በማሻሻል ጭምር ነበር።
በዚህ ውድድር ላይ ሞሮካዊቷ ፋጢማ ጋርዳዲ በሶስተኛነት በማጠናቀቅም ድሉ የአህጉሪቱ እንዲሆን አድርጋዋለች ተብሏል።
በውድድሩ ሌላ ተሳታፊ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ያለምዘርፍ የሁዋላው በአምስተኛነት አጠናቃለች።
የአንደኛነት ስፍራ ያጠናቀቀችው አማኔ በታህሳስ ወር ቫለንሺያ በተካሄደ የማራቶን ውድድር ሶስተኛውን ፈጣን ሰዓትም አስመዝግባ ነበር።
ቅዳሜ ነሐሴ 13/2015 ዓ.ም. በቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10ሺህ ሜትር የሴቶች ውድድር ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።
በውድድሩ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በ31፡27.18 በሆነ ሰዓት የወርቅ ሜዳሊያውን ለአገሯ ስታስገኝ፣ ለተሰንበት ግደይ በ31፡28.16 የዓመቱን የግል ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛ እንዲሁም እጅጋየሁ ታዬ የነሐስ ሜዳሊያ ወስዳለች።
በወንዶች የ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ሰለሞን ባረጋ በሶስተኛነት ስፍራ በማጠናቀቅ ነሐስ አግኝቷል።
በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ኢትዮጵያ ብዙም ስኬታማ ባልነበረችበት የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ለሜቻ ግርማ ብር ያገኘ ሲሆን በ1 ሺህ 500 ሜትር የሴቶች ውድደር ደርቤ ወልተጂ ብር አግኝታለች።
ኢትዮጵያ ከነሐሴ 13- 21 በቡዳፔስት እየተደረገ ባለው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የዛሬውን ጨምሮ ስምንት ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።












