ለግዞት የተዳረጉት የቢቢሲ ጋዜጠኞች

ሻዚያ ሃያ አፍጋኒስታን በነበረችበት ወቅት
የምስሉ መግለጫ, ሻዚያ ሃያ አፍጋኒስታን በነበረችበት ወቅት

ከሩሲያ እስከ አፍጋኒስታን በርካታ ጋዜጠኞች በየአገራቸው ስራቸውን ለማከናወን ባለመቻላቸው ለግዞት ተዳርገዋል።

ከነዚህም ውስጥ ወደ አገራቸው መመለስ የማይችሉ የቢቢሲ ጋዜጠኞች በርካቶች ናቸው።

ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው አኃዝ ጋር ሲነጻጸር ለስደት የተዳረጉ የቢቢሲ ጋዜጠኞች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል። ቢቢሲ ካሉት ጋዜጠኞች ውስጥ 310 የሚሆኑት በየአገራቸው ስጋት የተጋረጠባቸው እና በስደት ሆነው ስራቸውን ለመስራት የተገደዱ ናቸው።

ዓለም የፕሬስ ነጻነት ዕለትን ከምታከብርበት ዕለት በፊት ይፋ የሆነው መረጃ በሩሲያ፣ አፍጋኒስታን እና ኢትዮጵያ በርካታ ጋዜጠኞች ለእስር መዳረጋቸውን ያሳያል።

ኢራንን ጨምሮ ለቢቢሲ የሚሰሩ የሌሎች አገራት ጋዜጠኞች በውጭ አገራት መኖሪያቸውን ካደረጉ ከአስር ዓመት በላይ አስቆጥረዋል።

በርካታዎቹ አገራቸው ውስጥ በሌሉበት የእስር ብይን፣ የግድያ ዛቻዎች እና ትንኮሳዎች በበይነ መረብ እንዲሁም ከዚያ ውጭ ያስተናግዳሉ።

“ሪፖርት በማድረግ መቀጠል የሚችሉት ተሰደው ለግዞት በተዳረጉበት አገራት ነው። በግዞት ላይ ጋዜጠኞች ቁጥር ማሻቀብ ለፕሬስ ነጻነት እጅግ አሳሳቢ ነው” ሲሉ የቢቢሲ ወርልድ አገልግሎት ዳይሬክተር ሊሊያን ላንዶር ያስረዳሉ።

ከሶስት ዓመት በፊት ታሊባን አፍጋኒስታንን መቆጣጠሩን ተከትሎ ቢቢሲ በርካታ ጋዜጠኞቹን ከአገሪቱ አስወጥቷል። ታሊባን ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ሴት ጋዜጠኞች በስራ እንዳይሰማሩ ያገደ ሲሆን ወንድ ጋዜጠኞች ደግሞ ዛቻዎች ይገጥሟቸው ጀመር።

በእነዚህ አገራት ብቻ አይደለም በማይናማር እና ኢትዮጵያ በጋዜጠኞች ላይ ያሉ ጫናዎች እየጨመሩ በመምጣታቸው ስራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ አድርጓቸዋል።

“ጀርባዬን ሁልጊዜም እንደተጠራጠርኩ ነው” ሲል የቢቢሲ ፐርዢያ ኢራናዊው ጋዜጠኛ ጂያር ጎል ይናገራል። አንድ ቦታ በሚሄድበት ወቅት መጀመሪያ የሚያየው የማምለጫ በሩን ነው። “ በቤቴ ውስጥ በርካታ የደህንነት ካሜራዎች አሉኝ። የልጄን ትምህርት ቤት መቀየር እንዳለብኝ ከምክር ጋር የተያያዘ ማስጠንቂያ ደርሶኛል” ይላል።

ጂያር ከአውሮፓውያኑ 2007 ጀምሮ ለ17 ዓመታት ወደ ኢራን አልሄደም። እናቱ በሞተች ጊዜ መቅበር አልቻለም። ነገር ግን መቃብሯን ለመጎብኘት ድንበሩን በሚስጥራዊ ሁኔታ አቋርጦ ገብቶ ነበር።

ነገር ግን ባለቤቱ ከአራት ዓመት በፊት በካንሰር ማለፏን ተከትሎ የበለጠ ጥንቃቄ እያደረገ ይገኛል።

“በእኔ ላይ አንድ ነገር ቢደርስብኝ የልጄ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ይሄ ሁልጊዜም የሚያሳስበኝ ነገር ነው” ሲልም ጋዜጠኛው ያስረዳል።

“የኢራን ገዥ መንግሥት የበለጠ ደፋር እየሆነ መጥቷል። ጥብቅ ማዕቀብ ቢጣልበትም ዓለም አቀፉ ማህረሰብ ስላለው አስተያየት ብዙም ደንታ የለውም። ተገሎ ነው የሚገኘው” ይላል።

የቢቢሲ ሩሲያ ጋዜጠኛ ኒና ናዛሮቫ ከባለቤቷ እና ከልጃቸው ጋር
የምስሉ መግለጫ, የቢቢሲ ሩሲያ ጋዜጠኛ ኒና ናዛሮቫ ከባለቤቷ እና ከልጃቸው ጋር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ ሰራተኛ የሆኑት ጆዲ ጊንስበርግ እንደሚናገሩት ባለፉት ሶስት ዓመታት ለግዞት የተዳረጉ እና ተቋማቸው የገንዘብ እና የህግ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ጋዜጠኞች ቁጥር 225 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል።

“በእስር ያሉ ጋዜጠኞች በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል። የጋዜጠኞች ግድያ ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል” ሲሉ አክለዋል።

እንደ ሩሲያ፣ ኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ ያሉ መንግሥታት ደግሞ በአገርም ሆነ ከአገር ውጭ ያሉ ትረካዎችን ለመቆጣጠር የማይጭሩት ነገር እንደሌለም ጆዲ ያስረዳሉ።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ አገራቸውን ለቀው ከወጡ ጋዜጠኞች መካከል የቢቢሲ ሩሲያጋዜጠኛ ኒና ናዛሮቫ አንዷ ናት። በረራዋ ከሞስኮ ሲነሳ ጋዜጠኛ የሆነውን ባለቤቷን ስትመለከተው እያለቀሰ ነበር። “ በድን ሆንኩ” ትላለች።

በወቅቱም ሩሲያ አዲስ የሳንሱር ህግ ስራ ላይ ያዋለችበት ወቅት ነው። “ጦርነትን ጦርነት በማለቴ በቀላሉ ልታሰር እችል ነበር” ትላለች።

ሁለት ሻንጣዎችን ይዘው፣ የ16 ወር ጨቅላ ልጃቸውን በጋሪ ውስጥ አድርገው፣ በርካሽ ቲኬት ወደ ቱርክ ተጓዙ። ለአንድ ሳምንት በቱርክ በኋላ በዱባይ ሌላ አንድ ሳምንት ከቆዩ በኋላ ወደ ሞንቴኔግሮ፣ በመቀጠል ቢቢሲ በግዞት ለሚገኙ የሩሲያ ሰራተኞች ቢሮ ወዳቋቋመበት የላቲቪያ ዋና ከተማ ሪጋ ተዛወሩ።

በዚህ ዓመት በሚያዝያ ወር የኒና የስራ ባልደረባ የሆነው የቢቢሲ ሩሲያ ጋዜጠኛ ኢሊያ ባርባኖቭ “ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት” እና ጦርነቱን በመቃወም ክስ “የውጭ ወኪል” በሚል ተፈርጇል። ጋዜጠኛውም ሆነ ቢቢሲ ይህንን ፍረጃ ውድቅ አድርገው በፍርድ ቤት እየተከራከሩ ይገኛሉ።

በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ዛቻዎች ከአገር ከወጡ በኋላም ሊቀጥል ይችላል። ከጥቂት ወራት በፊት ኢራን ኢንተርናሽናል የተሰኘው ነጻ ሚዲያ አቅራቢ ከለንደን ከሚገኘው መኖሪያው ውጭ እግሩ ላይ በስለት የተወጋ ሲሆን የብሪታንያ ጸረ ሸብር ተቋም በቅርቡ በዩኬ የሚኖሩ የቢቢሲ ፐርዢያ ኢራናውያን ጋዜጠኞች ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደተደቀነ አስጠንቅቋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የቢቢሲ ፐርዢያ አቅራቢ ራና ራሂምፑር መኪናዋን ሰብረው ገብተው የማዳመጫ መሳሪያ እንደቀበሩባት ትጠረጥራለች። ከእናቷ ጋር ያደረገችው ውይይት በኢራን የመንግሥት ሚዲያ ተቀርጾ ታተመ። በቀረጻው ላይ አገዛዙን እንደምትደግፍ ለማስመሰል የአርትዖት ስራ ተሰርቶበታል።

የቢቢሲ ፐርዢያጋዜጠኞቹ ፈርናዝ ጋዚዛዴህ እና ራና ራሂምፑር
የምስሉ መግለጫ, የቢቢሲ ፐርዢያጋዜጠኞቹ ፈርናዝ ጋዚዛዴህ እና ራና ራሂምፑር

ተቀናቃኝ ሚዲያዎች ይህንን ቃለ መጠይቅ በመጠቀም እሷን ለማጥላላት ሲያውሉት ራና ከጋዜጠኝነት ህይወት ራሷን አርቃ እረፍት ለመውሰድ ወሰነች።

“ገዥው መንግሥት በስልቱ እየተራቀቀ መጥቷል። በእኔ ላይ የደረሰው ነገር እኛን ለማጣጣል፣ ለማስፈራራት እና በመጨረሻም ዝም ለማሰኘት ከሚሞክሩባቸው በርካታ መንገዶች አንዱ ነው” ትላለች ራና

በዚህም የተነሳ ጓደኞቿ እና ባልደረቦቿ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ጥሏቸዋል።

“እናቴ ጋር ኢራን በደወልኩ ቁጥር አንድ ሰው እየሰማን እንደሆነ አውቃለሁ” ትላለች ሌላኛዋ የቢቢሲ ፐርዢያ ጋዜጠኛ ፈርናዝ ጋዚዛዴህ

“አንቺን ለማጥፋት መንገድ እንደሚያገኙ ማወቅ ያስፈራል” ስትል ታስረዳለች

እሷም ለ21 ዓመታት ወደ ኢራን ተመልሳ የማታውቅ ሲሆን እሷ እና ዘጠኝ ባልደረቦቿ በሌሉበት የአንድ ዓመት እስር እንደተፈረደባቸው በቅርቡ ሰምታለች። ይህንን የሰማችው መረጃ መንታፊዎች ከኢራን የፍትህ አካላት መረጃ አሾልከው በማወጣታቸው ነው።

ከዚህ ቀደም የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢቢሲ ፐርዢያ ጋዜጠኞች ብጥብጥ፣ የጥላቻ ንግግር እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያነሳሳሉ በሚል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

የፋርናዝ ባለቤት በጻፈው ጽሁፍ ምክንያት ለ25 ቀናት ለእስር መብቃቱን ተከትሎ የስድስት ወር ልጃቸውን ይዘው ከአገር ወጡ።

ሆኖም በአገር ቤት ውስጥ ያሉት አባቷ በኢራን የደህንነት አገልግሎት እየተጠሩ ማስፈራሪያዎች ይደርሷቸው ነበር። ፋርናዝ እንድትመለስ እንዲነግሯት እንዲሁም የልጅ ልጃቸው የት እንደሚማር እንደሚያውቁ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋቸዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት የፋርናዝ ወንድም በጠና ሲታመም የማስታመሙ ኀላፊነት የወደቀው በእድሜ ባለጸጎቹ ወላጆቿ ላይ ነበር። ከስድስት ሳምንት በኋላ ወንድሟ ሞተ፤ በስድስት ወር ውስጥም አባቷም ተደገሙ።

“ያ መቼም ቢሆን የማይወጣልኝ ነገር ነው። ከቤተሰቤ፣ ከእናቴ ጋር አብረን ማዘን አልቻልንም” ትላለች።

ለቢቢሲ ፓሽቶ አገልግሎት የምትሰራው ሻዚያ ሃያ የስደት ህይወት የጥፋተኝነት ስሜት የተሞላበት ነው ትላለች

ከሁለት ዓመት በፊት ታሊባን አፍጋኒስታንን ሲቆጣጠር ወላጆቿን እና ወንድሟን ትታ እሷ ወደ ዪናይትድ ኪንግደም ተወሰደች።

“ከቤት ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ከቤት ስወጣ ምክንያቱን ባላውቅም ታናሽ ወንድሜን አቅፌ አልተሰናበትኩትም። አሁንም ድረስ ይህ ሁኔታ ይጸጽታኛል። “ የምትለው ሻዚያ አክላም “እኔ እዚህ ነጻ ነኝ ነገር ግን እነሱ የሚኖሩበት ሁኔታ እስር ቤት በሉት” ስትል ታስረዳለች

ከአገሯ ብትርቅም በኢንተርኔት የማያቋርጥ ትንኮሳዎች ይገጥሟታል።

ፋርናዝም በተመሳሳይ እንዲሁ ማስፈራሪያዎች ይደርሷታል “የግድያ ዛቻዎች ይሁኑ ወሲባዊ ጥቃቶች ማስፈራሪያዎች በአሁኑ ወቅት ማየት አቁሜያለሁ” ትላለች።

ከአገራቸው ውጭ ሆነው የሚሰሩ ሌላ ጋዜጠኛ የአገራቸውን መንግሥት በመፍራት ስማቸው እንዳይጠቀስ ገልጸው፣ እሳቸውና ባልደረቦቻቸው የሚያስፈራቸው ትልቁ ጉዳይ መንግሥታቸው ፓስፖርት ለማደስ ፈቃደኛ ካልሆነ አገር አልባ የመሆናቸው ጉዳይ ነው።

እነዚህን ጋዜጠኞች ከማስፈራሪያዎች በላይ የሚያበሳጫቸው ጉዳይ ስለ አገራቸው ጉዳይ ከሩቅ መዘገባቸው ነው።

ሻዚያ በአፍጋኒስታን በነበረበች ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውራ ስለ ሰዎች በተለይም የሴቶች ህይወት ላይ የሚያጠነጥኑ ዘገባዎች ትሰራ ነበር። አሁን ግን በርቀት ሆና በስልክ ማናገር አለባት እሱም እምነታቸውን ከጣሉባት ነው። በአፍጋኒስታን እና ኢራን ተራ ሰዎች ቢቢሲን በማናገራቸው ብቻ ዛቻ ይደርስባቸዋል። ኒናም ቢሆን ከአገሯ ርቃ በስልክ ቃለ መጠይቅ ማድረግ በጣም እንደከበዳት ትናገራለች። ቤተሰብ፣ ወዳጅ አዝማዱ የሚሰባሰቡባቸው በዓላት ይናፍቋታል። “ፍቅሩ አሁንም ቢኖር ሩቅ ነው” ትላለች።

በስደት መኖር እና መስራት ግማሽ ህይወት ነው ትላለች ፋርናዝ። “በእዚህ ዓይነት ስሜት ህይወት መምራት ከባድ ነው። አሁን እንግሊዛዊ ነኝ እዚህ አገር እየኖርኩ ነው። ነገር ግን በዚህ መንገድ አይደለም የማየው። በግዞት ላይ ነኝ፣ ነገር ግን አገሬም ላይ ነኝ” ትላለች።