ሴቶች በአደባባይ ድምጻቸው እንዳይሰማ የሚከለክለው አዲሱ የታሊባን ሕግ

የጠመጠመች አፍጋናዊት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአፍጋኒስታን ገዢ ታሊባን በቅርቡ “የሥነ ምግባር ዕሴቶችን ለማበረታት እና የብልግና ድርጊቶችን ለማስወገድ” ያስችላል ያለውን አዲስ ሕግን አጽድቋል።

ሴቶች በአደባባይ ላይ ጮክ ብለው እንዳይናገሩ እንዲሁም ፊታቸውን ከመኖሪያ ቤታቸው ውጭ እንዳይገልጡ መከልከልን ጨምሮ ሌሎች ጨቋኝ ዝርዝሮችን ይዟል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕጉን አውግዞ በአተገባበሩ ላይ ያለውን ስጋት ገልጿል።

የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሕጉ “በአፍጋኒስታን መጻዒ ዕጣ ፈንታ ላይ አሳዛኝ ሁኔታዎችን ደቅኗል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሕጉ የጸደቀው በታሊባን ታላቁ መሪ ሃይቡትላህ አክሁንድዛዳ ነው።

መልካምነትን ለማስፋፋት እና መጥፎ ድርጊቶችን ለመከላከል የተቋቋመው የሥነ ምግባር ሚኒስቴር በአገሪቱ ያለ ማንኛውም ነዋሪ ይህ ሕግ ይመለከታቸዋል ብሏል።

በእዚህ ሕግች መሠረት ሞህታሳቢን ተብለው የሚጠሩት የታሊባን የሞራል ፖሊሶች በአፍጋኒስታናውያን የአደባባይ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ ያስችላቸዋል።

በሕዝባዊ ቦታዎች ላይ የሚለበሱ አልባሳትን፣ መጠጥ፣ ምግብ እና ሌሎች ጉዳዮችን ለመቆጣጠርም ያስችላል።

ሕጉ ስለ ሴቶች ምን ይላል?

በአዲሱ ሕግ መሠረት የሴቶች ድምጽ በሕዝባዊ ቦታዎች ላይ መሰማት እንደ “ብልግና” ወይም መጥፎ ባህርይ እንደሆነ ተደንግጓል።

“አንዲት ሴት በአስቸጋሪ ምክንያት ከመኖሪያ ቤት ስትወጣ ድምጿ መሰማት የለበትም። ፊቷን እና አካሏን መደበቅ አለባት” ሲል ሕጉ ያትታል።

ሚኒስቴሩ የእስልምና ሃይማኖት ማዕከል ያደረገውን የሸሪዓ ሕግን መሠረት አድርጎ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን ከዚህ ቀደም እያስፈጸመ ይገኛል። እነዚህን መመሪያዎች የተላለፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።

ታሊባን ይህ አዲስ ሕግ ከሸሪዓ ሕግ ትርጓሜ ጋር የሚጣጣም እና በሥነ ምግባር ሚኒስቴር የሚተገበሩ ናቸው ብሏል።

ሕጉ ሴቶች “ወንዶችን አማልለው ወደ ፈተና እንዳያስገቧቸው እና ወደ መጥፎ ነገር እንዳይመሯቸው” ፊታቸውን ጨምሮ መላ አካላቸው ሙሉ በሙሉ መሸፈን እንዳለበት ዝርዝር አስቀምጧል።

በዚህም መሠረት፦

  • አካሏን (ገላዋን) ሙሉ በሙሉ መሸፈን አለባት።
  • እንዳታማልል ወይም ወደ ፈተና ውስጥ እንዳታስገባ ፊቷን መሸፈን አለባት።
  • የሴት ድምጽ እንደ ‘አውራህ’ ስለሚቆጠር በአደባባይ መሰማት የለበትም። አውራህ የሚለው የአረብኛ ቃል ለሴቶችም ይሁን ለወንዶች መሸፈን ያለባቸው የሰውነት የአካል ክፍሎችን ያመለክታል።
  • ሴቶች በመኖሪያ ቤታቸው ጭምር ጮክ ብለው ሲዘፍኑ ወይም ሲያነቡ መሰማት የለባቸውም።
  • የሴቶች ልብስ የሳሳ፣ አጭር ወይም ጠበብ ያለ መሆን የለበትም።
  • ሴቶች በደምም ሆነ በጋብቻ ዝምድና ከሌላቸው ወንዶች ገላቸውን እና ፊታቸውን መደበቅ አለባቸው።

ወንዶችም ቢሆን የሴቶችን አካል እና ፊት እንዳይመለከቱ የተከለከሉ ሲሆን ሴቶችም እንዲሁ ተከልክለዋል።

አፍጋናውያን ሴቶች በመንገድ ላይ

የፎቶው ባለመብት, QUDRATULLAH RAZWAN/EPA-EFE/REX/Shutterstock

በወንዶች ላይ የተጣሉ አዳዲስ ገደቦች

የአፍጋኒስታን አዲሱ የሥነ ምግባር ሕግ በወንዶች ላይ አንዳንድ ገደቦችን ጥሏል።

የወንዶች ከእምብርታቸው እስከ ጉልበታቸው ያለው የሰውነት ክፍላቸው እንደ “አውራህ” ስለሚቆጠር ከቤታቸው ውጭ እንዲሸፍኑ ይገደዳሉ።

ወንዶች ፀጉራቸውን ከሸሪዓ ሕጉ ጋር በሚጻረር መንገድ እንዲስተካከሉ አይፈቀድላቸውም። እንዲያውም ታሊባን አዲሱ ሕግ ከሸሪዓ ሕጉ ጋር የሚሄድ ነው በማለት በበርካታ ግዛቶች የሚገኙ ጸጉር አስተካካዮች ጺም እንዳይላጩ ወይም እንዳይከረክሙ ከልክሏል።

በአዲሱ ሕግ መሠረት የወንዶች ጺም ረዥም መሆን አለበት። የሥነ ምግባር ሕጉ ወንዶች ክራባት እንዳያስሩ ይከለክላል።

የአፍጋኒስታን የስነ ምግባር አስከባሪዎች እነማን ናቸው?

ሞህታሳቢን ይህንን ሕግ በመላው አገሪቷ ባሉ ግዛቶች የማስከበር ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። ሕጉ መጠበቁን ይቆጣጠራሉ እንዲሁም የተላለፉትን ወደ ፍርድ ቤት ያመጣሉ።

ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ጮክ ብለው የሚሰሙ ሴቶችን ዝም ማሰኘት፣ እንዲሁም ወንዶች መመሪያዎቹን ካላከበሩ ፀጉራቸውን እንዲላጩ ወይም እንዲቆርጡ ማስገደድ ይችላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ሕጉ የታክሲ አሽከርካሪዎች በወንዶች ቤተሰቦቻቸው ላልታጀቡ እና በሸሪዓው ሕግ መሠረት ሂጃባቸውን ላልለበሱ ሴቶች አገልግሎት እንዳይሰጡ የማድረግ ሥልጣንን ለሞህታሳቢን ሰጥቷል።

በመኪና ውስጥ ወንዶች እና ሴቶች ጎን ለጎን መቀመጥ አይፈቀድላቸውም።

የሰዎች እና የእንስሳት ፎቶዎች አይፈቀዱም።

አዲሱ ሕግ የህያዋን ለምሳሌ የቤተሰብ አባል፣ የወፎች፣ ወይንም የእንስሳት ፎቶዎችን ማንሳት፣ ማሳተም ወይም በመኖሪያ ቤትም ሆነ በየትኛውም ስፍራ መሸጥ ይከለክላል።

ፎቶዎችን ብቻ ሳይሆን ሃውልቶችን መግዛትም ሆነ መሸጥ የተከለከለ ነው።

በሸሪዓ ሕግ “ሃራም” የተባሉ ሙዚቃዎችን ማጫወት እንዲሁም በሬድዮ ላይ መስማት መከልከልን እነዚሁ የሞራል ፖሊሶች ያስከብራሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎችም ሆነ እንስሳት የተሳተፉበትን ፊልሞችን መቅረጽ፣ ማየት እንዲሁም ማሳየት የተከለከለ ነው።

ነገር ግን ከአዲሱ ሕግ ጋር በተቃረነ መልኩ የሥነ ምግባር ሚኒስትሩ መሐመድ ሃሊድ ሃናፊን ጨምሮ በርካታ የታሊባን መንግሥት ባለሥልጣናት በቅርቡ በቪዲዮ ታይተዋል።

በሞተር ሳይክል እየተጓዙ ያሉ ግለሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቅጣቶቹ ምንድን ናቸው?

ሕጉ፣ ግለሰቦች በግልጽ “የሚያስወቅሳቸውን (የሚያስወግዛቸው) ተግባር ከፈጸሙ የአምላክን መለኮታዊ ቅጣት እንዲፈሩ” መምከር እንዲሁም የገንዘብ ቅጣት እና ለቀናት እስራት ይጠብቃቸዋል።

ሕጉ በርካታ ትችቶችን እያስተናገደ ይገኛል።

አገሪቱ ከአስርት ዓመታት ጦርነት በኋላ እንዲሁም በአስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ እየዳከረችበት ባለበት ሁኔታ የአፍጋኒስታን ሕዝብ ማስፈራራት፣ ቅጣት እና እስራት ሳይሆን የተሻለ ነገር ያስፈልገዋል ሲሉ በአፍጋኒስታን የተባበሩት መንግሥታት የአፍጋኒስታን ተልዕኮ ኃላፊ ሮዛ ኦቱንባየቫ ተናግረዋል።

አዲሱ ሕግ ዋና ከተማዋን ካቡልን ጨምሮ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አልሆነም።

የሥነ ምግባር ሚኒስቴር ምንጭ ለቢቢሲ ፓሽቶ እንደገለጹት አዲሶቹን ድንጋጌዎች ተግባራዊ ለማድረግ ማዕቀፍ እየተዘረጋ መሆኑን ነው።

እንደ ምንጩ ከሆነ ይህ ማዕቀፍ ከተጠናቀቀ በኋላ በሕጉ አፈፃፀም ላይ የበለጠ ግልጽነት እንደሚኖረው ነው።

ሆኖም በሕጉ ስር ያሉ አብዛኛዎቹ አንቀጾች በተቀረው የአገሪቱ ክፍል እየተተገበሩ ናቸው።

በአፍጋኒስታን ውስጥ ንቁ ከሆኑት አንዱ የሆነው የሥነ ምግባር ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት የሸሪዓ ሕግን ያላከበሩ ከ13 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በጊዜያዊነት ታስረው እንደነበር አስታውቋል።