ከጂቡቲ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ የሞቱት 48 ስደተኞች ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ተረጋገጠ

ባለፈው ማክሰኞ ከጂቡቲ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ባሕር ውስጥ ሰምጠው የሞቱት እና ደብዛቸው የጠፋው ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አይኦኤም ለቢቢሲ አረጋገጠ።
ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አይኦኤም ለቢቢሲ ሐሙስ አመሻሽ ላይ እንዳረጋገጠው በጀልባዎቹ ላይ የነበሩት እና በአደጋው የሞቱት 48 ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው።
በሁለት ጀልባዎች ከየመን ተነስተው ወደ ጂቡቲ ሲመለሱ የነበሩት 320 ሰዎች ወደ ባሕር ዳርቻው ከመድረሳቸው በፊት ጀልባዎቹን በሚያንቀሳቅሱት የሰዎች አዘዋወሪዎች ተገደው ወደ ባሕሩ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ አሰቃቂ አደጋ መድረሱን ታውቋል።
በክስተቱ ቢያንስ 48 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ደብዛቸው የጠፋውን 75 የሚሆኑትን ስደተኞች ለማግኘት ፍለጋ እየተካሄደ መሆኑን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል።
በጂቡቲ የአይኦኤም የኮምዩኒኬሽን ረዳት ካውሰር ሳዓድ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት በጀልባዎቹ ላይ ተሳፍረው ከየመን ወደ ጂቡቲ ሲመለሱ የነበሩት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ስለዚህም በባሕሩ ውስጥ ሰምጠው መሞታቸው የታወቀው እንዲሁም የደረሱበት ያልታወቀው ሰዎች በሙሉ ከየመን ወደ ጂቡቲ በመጓዝ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ስደተኞች እንደነበሩ ተገልጿል።
በአሰቃቂው አደጋ ከሞቱት እና የደረሱበት ካልታወቀው ሰዎች ባሻገር 197 ሰዎች ተርፈው ኦቦክ ውስጥ የህክምና እና ሌሎች ድጋፎች እየተደረጉላቸው እንደሆነ በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንስላ ክፍል ሚኒስትር አማካሪ የሆኑት አቶ አደራ ተመስገን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አይኦኤም እና አቶ አደራ ረቡዕ ዕለት እንዳሳወቁት በደረሰው አደጋ ቢያንስ 45 ስደተኞች በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከተሳፈሩባቸው ጀልባዎች ላይ ተገፍትረው ለሞት መዳረጋቸውን ተገለጸ ነበር።
አቶ አደራ ለቢቢሲ እንደገለጹት አደጋው የደረሰባቸው ስደተኞች በባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች እንዳይያዙ ወደ ባሕር ዳርቻው ሳይደርሱ ከጀልባው “እንዲወርዱ በመደረጉ [ወደ ውቅያኖሱ ዘልለው እንዲገቡ በመገደዳቸው] አብዛኞቹ ዋኝተው መውጣት ባለመቻላቸው ለሞታቸው ምክንያት ሆኗል” ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አይኦኤም በበኩሉ በጂቡቲዋ ኦቦክ የባሕር ዳርቻ ላይ ያጋጠመው አሰቃቂው አደጋ ስደተኞቹ በኃይል ከጀልባዎቹ ላይ ወደ ባሕሩ እንዲገቡ በአዘዋዋሪዎች በመገደዳቸው ነው ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Djibouti Coast Guard
ከ45 በላይ ስደተኞች የሞቱበት እና በርካቶች ደብዛቸው በጠፋበት በዚህ አደጋ ተሳፍረው የነበሩ ስደተኞች ከየመን ወደ ጂቡቲ በራሳቸው ፍላጎት እየተመለሱ የነበሩ ሲሆን “አንዳንዶቹ በሄዱበት ጀልባ የሚመለሱ” እንዳሉ ጨምረው ተናግረዋል።
ስደተኞችን ከየመን አሳፍረው ወደ ጂቡቲ ሲጓዙ የነበሩት ሁለቱ ጀልባዎች ከ320 በላይ ሰዎችን ይዘው ነበር። በዚህም አንደኛው 100 ሁለተኛው ደግሞ 220 ስደተኞችን አሳፍረው ወደ ጂቡቲ ሲያመሩ እንደነበር ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ተናግረዋል።
አይኦኤም እንዳለው በጀልባዎቹ ላይ የነበሩት ስደተኞች ወደ ጂቡቲ የባሕር ጠረፍ ሲቃረቡ የመናዊ በሆኑት የሰው አዘዋዋሪዎች ወደ ባሕሩ እንዲገቡ እና በዋና ወደ ዳርቻው እንዲደርሱ አስገድደዋቸው በርካቶች ለሞት ተዳርገዋል።
ከአደጋው የተረፉ ሰዎች እንደተናገሩት አንዲት ሴት ባሕሩ ውስጥ ሰምጣ ስትሞት የአራት ወር ልጇ ከሌሎች 98 ሰዎች ጋር በመጀመሪያው የነፍስ አድን ጥረት በሕይወት ሊተርፍ ችሏል።
በዓለማችን በርካታ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ የሚጓጓዙባቸው ናቸው ከሚባሉ አስፈሪ የባሕር መተላለፊያዎች አንዱ የሆነው ይህ ሥፍራ በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች አህጉሪቱን ጥለው ለመውጣት ይጠቀሙበታል።
ከሰኞ ጠዋት ጀምሮ በአደጋው ደብዛቸው የጠፋውን ሰዎች ለማግኘት “መጠነ-ሰፊ ፍለጋ” እየተደረገ መሆኑን ያሳወቀው የጂቡቲ ባሕር ጠረፍ ጥበቃ ከአይኦኤም ጋር በመተባበር እስካሁን 115 ሰዎችን ማዳን መቻሉን ገልጿል።
የባሕር ጠረፍ ጥበቃው አክሎ እንዳስታቀው ጀልባዎቹ ተገልብጠው የሰመጡት ሰሜን ምዕራብ ጂቡቲ ከምትገኘው ኾር አንጋር ግዛት 150 ሜትር ርቀት ላይ ነው።
በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች ቀይ ባሕርን ተጠቅመው በነዳጅ ሀብት ወደ በለፀጉ የባሕረ ሰላጤ አገራት ይጓዛሉ። ስደተኞቹ በአገሮቻቸው ያሉ ግጭቶችን፣ ተፈጥዊ አደጋዎችን እና የኑሮ ውድነትን በመሸሽ ነው የሚሰደዱት።
ባለፈው ዓመት ሰኔ በተመሳሳይ የመን ድንበር አቅራቢያ ቀይ ባሕር ላይ አንዲት ጀልባ ተገልብጣ 56 ሰዎች መሞታቸውን 140 ሰዎች መጥፋታቸው ይታወሳል።
የአደጋው ሰለባ የነበሩት ስደተኞች ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ የመጡ ነበሩ። ከሟቾቹ መካከል 31 ሴቶች እና ስድስት ሕፃናት ይገኙበታል።
ቀይ ባሕርን ተጠቅመው ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን የሚጓዙ ስደተኞች ቁጥር በአውሮፓውያኑ 2022 ከነበረው 73 ሺህ ወደ 97 ሺህ 200 ማደጉን አይኦኤም አስታውቋል።
አብዛኞቹ ስደተኞች በሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካይነት ነው ይህን ባሕር መስመር ለማቋረጥ የሚሞክሩት።
ስደተኞቹ ብዙውን ጊዜ ለአደጋ የሚጋለጡት በአነስተኛ ጀልባ በከፍተኛ ቁጥር ታጭቀው በአደገኛው ባሕር ላይ ለመጓዝ ሲሞክሩ መሆኑ በተደጋጋሚ ይገለጻል።
አሁን ያጋጠመውን አደጋን በአውሮፓውያኑ 2024 ካጋጠሙት አሰቃቂው መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ በአይኦኤም በተደረገው ምዝገባ በምሥራቁ የስደት መስመር ከ1,300 በላይ ሰዎች ባሕር ውስጥ ሰጥመው የደረሱበት ያልታወቀ ሲሆን፣ ይህ አሃዝም ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት ያጋጠመውን 337 ሰዎችን ይጨምራል።












