በአማራ ክልል ምሁራንን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጅምላ መታሰራቸውን አምነስቲ አስታወቀ

የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባሕር ዳር
የምስሉ መግለጫ, የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባሕር ዳር

በአማራ ክልል በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዘፈቀደ በጅምላ መታሰራቸውን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ አስታወቀ።

ከመስከረም 18 ቀን 2017 ዓ. ም. ጀመሮ ምሁራንና ሲቪል ሠራተኞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጅምላ መያዛቸውን የሚጠቁሙ ሪፖርቶች እንደደረሱት አምነስቲ ገልጿል።

አምነስቲ መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ. ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳለው ይህ የዘፈቀደ የጅምላ እስር “የሕግ የበላይነት ማጣትን የሚያባብስ” ነው።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠናዊ ኃላፊ ቲጌሬ ቻጉታ፣ “የኢትዮጵያ ወታደሮችና ፖሊሶች በአማራ ክልል የከፈቱት የዘፈቀደ እስር ዘመቻ፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ሙሉ በሙሉ ችላ ማለቱን ያሳያል” ማለታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።

የመንግሥት ባለሥልጣናት “የስም ዝርዝር” ይዘው በአማራ ክልል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎችን ማሰራቸውን የዓይን እማኞች መናገራቸውን አምነስቲ ገልጿል።

ቲጌሬ ቻጉታ እንዳሉት የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ሰዎቹን ከመያዛቸው አስቀድሞ “የእስር ማዘዣም ይሁን ፍተሻ ለማድረግ ፈቃድ አላቀረቡም”።

“የታሰሩት ሰዎች በ48 ሰዓታት ውስጥም ፍርድ ቤት አልቀረቡም” ብለዋል።

የዓይን እማኞች ለአምነስቲ እንደገለጹት፣ በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ያሉ ምሁራን ከታገቱት መካከል ይጠቀሳሉ።

“አንዳንድ እገታዎች የተፈጸሙት በወታደሮች፣ ምሽት ላይ ነው” ሲልም ሁኔታውን ገልጿል።

“የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የዘፈቀደ የጅምላ እስር በአፋጣኝ ማቆም አለበት። በታሰሩት ሰዎች ላይ ሕግን ተከትሎ ክስ መመሥረትና የሕግ ሥርዓትን መከተል ይገባዋል። ካልሆነም ሰዎቹን መልቀቅ አለበት። መንግሥት የዘፈቀደ እስርን ለጭቆና ማዋል ማቆም አለበት” ሲሉም የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠናዊ ኃላፊ ተናግረዋል።

ባለፉት ጥቂት ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት በጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ማስፈራሪያ፣ ተከታታይ ጥቃትና ትንኮሳ ማድረጉን አምነስቲ እንደመዘገበ በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቅሷል።

“በዚህም ምክንያት ብዙዎች እየተሰደዱ ነው” ብሏል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ።

“እነዚህ ጉልህ ሚና ያላቸው ሰዎች ከአገር በመሰደዳቸው ምክንያት በተለይም እንደ አማራ ክልል ባሉ በግጭት ውስጥ ያሉ አካባቢዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዘገባና ስነዳ ቀንሷል።”

በመግለጫው እንደተባለው፣ የምሁራን እና ሲቪል ሠራተኞች የዘፈቀደ እስር የንግግር ነጻነትን የበለጠ የሚያፍን ነው።