የካማላ ሃሪስ እና የዶናልድ ትራምፕ ወሳኝ የፖሊሲ አቋሞች ምን ይመስላሉ?

አሜሪካውያን መራጮች ከዴሞክራቷ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ እና ከሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ መካከል ይበጀኛል የሚሉትን በምርጫ ይወስናሉ።
በሁለቱ ዕጩዎች መካከል ያለውን ልዩነት እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ፖሊሲዎቻቸው ምን እንደሚመስሉ ተመልክተናል።
ምጣኔ ሀብት
ሃሪስ ቅድሚያ የሚሰጡት ለሠራተኛ ቤተሰቦች የምግብ እና የቤት ወጪን ለመቀነስ መሞከርን እንደሆነ ተናግረዋል።
የፍጆታ ዕቃዎች የዋጋ ንረትን መከልከል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤት የሚገዙትን መርዳት እና የቤት አቅርቦትን ለመጨመር ማበረታቻዎችን ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው “የዋጋ ግሽበትን በማስቆም እና አሜሪካንን በድጋሚ ተመጣጣኝ ለማድረግ” ቃል ገብተዋል።
ፕሬዚዳንቱ የማይቆጣጠሩት ቢሆንም ዝቅተኛ የወለድ ተመንን ለመተግበር ቃል ገብተዋል። ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞችን ማባረር በመኖሪያ ቤቶች ላይ ያለውን ጫና ይቀንሳል ሲሉም አክለዋል።
ፅንስ ማቋረጥ
ሃሪስ ጽንስ ማቋረጥን የምርጫ ዘመቻቸው ማዕከል አድርገውታል። በአገር አቀፍ ደረጃ መብቶችን የሚያከብር ሕግ እንዲወጣ በመሞገት ላይ ይገኛሉ።
ትራምፕ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በዚህ ጉዳይ ላይ ወጥ የሆነ መልዕክት ለማስተላለፍ ሲቸገሩ ታይተዋል።
ቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሥልጣን ላይ እያሉ ፅንስ የማቋረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብትን ሲሽሩ ብይን በመስጠት ወሳኝ ሚና የተጫወቱትን ሦስት ዳኞች መሾማቸው ይታወሳል።
ስደት
ሃሪስ የደቡባዊውን የድንበር ቀውስ ዋና መንስኤዎችን የመፍታት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ወደ ሰሜን የሚደረገውን ፍሰት ለመግታት ያለመ ክልላዊ ኢንቨስትመንት እንዲኖር በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ገንዘብ ለማሰባሰብ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
እአአ በ2023 መጨረሻ ላይ ከሜክሲኮ የተሻገሩ ሰዎች ክብረ ወሰን በሆነ ደረጃ ቁጥሩ ቢጨምርም፤ ከዚያ ወዲህ ግን ቀንሷል።
በካሊፎርኒያ ዐቃቤ ሕግ ሆነው ሲያገለግሉ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ የወሰዱትን ልምድ አፅንኦት ሰጥተው በምርጫ ዘመቻ ወቅት አቋሟቸውን አስታውቀዋል።
ትራምፕ የአጥር ግንባታውን በማጠናቀቅ እና ማጠናከሪያዎችን በመጨመር ድንበሩን ለመዝጋት ቃል ገብተዋል። ሪፐብሊካኖች በካማላ ሃሪስ የተደገፈውን የድንበር ሕግ ውድቅ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በአሜሪካ ታሪክ ትልቁን ሰነድ አልባ ስደተኞች የማበራር ውሳኔ እንደሚተገብሩ ቃል ገብቷል። ይህ ግን ሕጋዊ ፈተና እንደሚገጥመው ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ግብር
ሃሪስ በዋና ዋና የአገሪቱ ተቋማት እና ሀብታም አሜሪካውያን ላይ ግብር ጭማሪ በማድረግ በዓመት እስከ 400 ሺህ ዶላር መሰብሰብ ይፈልጋሉ።
በተጨማሪም ልጆች ያሏቸውን በቤተሰቦችን ለመደገፍ ያለባውን የግብር ጫና የሚያቃልሉ በርካታ እርምጃዎችንም ይፋ አድርገዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው እአአ በ2017 ያደረጓቸውን የታክስ ቅናሾች ማራዘምን ጨምሮ በትሪሊዮን የሚገመቱ የግብር ቅነሳ ሃሳብን አቅርበዋል።
ተንታኞች ሁለቱም የግብር ዕቅዶች የአገሪቱን የበጀት ጉድለትን ይጨምራል ያሉ ሲሆን፣ የትራምፕ ከፍተኛ እንደሚሆን ገምተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ
ሃሪስ “የፈጀው ጊዜ ቢፈጅም” ዩክሬንን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል። ከተመረጡ “የ21ኛው ክፍለ ዘመን ውድድርን” ቻይና ሳትሆን አሜሪካ ማሸነፏን ለማረጋገጥ ቃል ገብተዋል።
በእስራኤላውያን እና በፍልስጤማውያን መካከል የሁለት አገር መፍትሔ እንዲተገበር ለረዥም ጊዜ ተሟግተዋል። በጋዛ ያለው ጦርነት እንዲቆምም ጠይቀዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው የማግለል የውጭ ፖሊሲን ስለሚከተሉ ዩናይትድ ስቴትስ ራሷን በዓለም ላይ ካሉ ግጭቶች እንድትገለል ይፈልጋሉ።
ከተመረጡ ከሩሲያ ጋር በሚደረግ ድርድር በዩክሬን ያለውን ጦርነት በ24 ሰዓታት ውስጥ እንደሚያስቆሙ ተናግረዋል። ይህ እርምጃ ቭላድሚር ፑቲንን የሚያገዘፍ ነው ሲሉ ዴሞክራቶች ተችተዋል።
ትራምፕ ራሳቸውን የእስራኤል ጠንካራ ደጋፊ አድርገው ይቆጥራሉ። በጋዛ ያለውን ጦርነት እንዴት እንደሚያስቆሙ ግን ብዙም አልተናገሩም።
ንግድ
ሃሪስ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ታሪፍ ለመጣል ትራምፕ የያዙትን ዕቅድ ተችተዋል። ይህ ዕቅድ እያንዳንዱን ሠራተኛ ቤተሰብ በዓመት 4 ሺህ ዶላር የሚያስወጣ ብሔራዊ ግብር በማለት ጠርተውታል።
ትራምፕ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ምርቶች ላይ የበለጠ ግብር በመጣል ላይ ያነጣጠረ አካሄድ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።
ትራምፕ ታሪፍን ምርጫ ዘመቻቸው ዋና ማዕከል እንደሚሆንቃል ገብተዋል። በአብዛኞቹ የውጭ ምርቶች ላይ ከ10 እስከ 20 በመቶ አዲስ ታሪፍ ለመጣል ሃሳብ አቅርበዋል። ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጥሉት ታሪፍ በጣም ከፍ ያለ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የአየር ንብረት
ሃሪስ በምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው “ኢንፍሌሽን ሪዳክሽን አክት” የተሰኘው ሕግ እንዲያልፍ ደግፈዋል። ይህም በቢሊዮን ሚቆጠር ዶላር ለታዳሽ ኃይል እና ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ድጋፍ ማድረግን ያካትታል።
የአካባቢ ተቆርቋሪዎች የሚቃወሙትን የጋዝ እና የነዳጅ መልሶ ማውጣት ሥራ መጀመርን ተቃውመዋል።
ትራምፕ ዋይት ሐውስ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ከኃይል ማመንጫዎች እና ከተሽከርካሪዎች የሚለቀቀውን የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት መቀነስን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካባቢ ጥበቃዎችን ውድቅ አድርገዋል።
በዚህ የምርጫ ዘመቻም የአርክቲክ የነዳጅ ማውጣት ቁፋሮዎችን ለማስፋፋት እና የኤሌክትሪክ መኪናዎችን የማስፋፋት ፍልጎትን እንደሚያቀዘቅዙት አሳውቀዋል።
ጤና
ሃሪስ በሐኪም የታዘዙ መድኃኒቶች ወጪን የቀነሰውን እና የኢንሱሊን ዋጋን በ35 ዶላር የሚገድበው የዋይት ሃውስ ውሳኔ አካል ናቸው።
ትራምፕ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የጤና መድንን ያራዘመውን “አፎርደብል ኬር አክትን” ለማቆም የሚያደርጉትን ጥረት እንደማይቀጥሉ ተናግረዋል።
በግብር ከፋዮች የገንዘብ ድጋፍ የመካንነት ህክምና እንዲደረግ ቢጠይቁም ግን ይህ በኮንግረስ ውስጥ በሚገኙ ሪፐብሊካኖች ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል።
ወንጀል
ሃሪስ ዐቃቤ ሕግ በነበሩበት ወቅት የነበራቸውን ልምድ እና ትራምፕ ወንጀለኛ ከመባላቸው እውነታ ጋር በማነጻጸር ለማቅረብ ሞክረዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው በወንጀል የተጨናነቁ ናቸው ያሏቸውን የአደንዛዥ ዕፅ መረቦችን ለማፍረስ፣ የቡድን ወንጀልን ለመከላከል እንዲሁም በዲሞክራቶች በሚተዳደሩ ከተሞች ያለውን ወንጀል ለመከላከል ቃል ገብተዋል።












