የሄዝቦላው መሪ ሐሳን ናስራላህ መገደል ኢራንን ምን ያህል አስደንግጧል?

የሐሳን ናስራላህ መገደል የኢራን ባለሥልጣናትን በከፍተኛ ሁኔታ አስደንግጧል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሐሳን ናስራላህ መገደል የኢራን ባለሥልጣናትን በከፍተኛ ሁኔታ አስደንግጧል

ዐርብ ዕለት የቴህራን ከተማ ማዘጋጃ ቤት ደጅ በሐሳን ናስራላህ ፎቶ ደምቆ ነበር።

ምናልባት የኢራን ባለሥልጣናት ወዳጃቸው ናስራላሕ ስለመገደሉ ቀደም ያለ መረጃ ነበራቸው። ሄዝቦላህ የመሪውን ሞት ያረጋገጠው ቅዳሜ ነው።

የሄዝቦላህን ይፋዊ ማረጋገጫ ተከትሎ ደግሞ የኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዥን በናስራላሕ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ተሞላ። ''መስዋዕቱ፣ ሰማዕቱ'' እየተባለ ተዘከረ።

የኢራን ባለሥልጣናት በበኩላቸው የኢራን አብዮታዊ ሪፐብሊካን ዘብ ምክትል የእዝ ኮማንደር አባስ ኒልፎሩሻን በጥቃቱ መገደሉን አምነዋል። ሐዘኑም ድርብ ሆኖባቸዋል።

ለዓመታት የኢራን ሪፐብሊክ ባለሥልጣናት ሐሳን ናስራላህ፣ ‘የጀግኖች ቁንጮ’ አድርገው ነው ለዜጎቿ የሰበኩት።

ሄዝቦላህ ድርጅትንም ለሽንፈት ያልተፈጠረ፣ በጦርነት የሚረታው አንዳችም ምድራዊ ኃይል የሌለ ሆኖ ነው የተሳለው።

ላለፉት በርካታ ዓመታት ኢራን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ለአጋሮቿ ሰጥታለች። በየመን የሺዓ ሚሊሻዎችን፣ በሊባኖስ ሄዝቦላህን፣ በኢራቅና በኢራን መንግሥታትንና ታጣቂዎችን ደጉማለች።

ሄዝቦላህ ደግሞ የኢራን ጠላቶችን የገቡበት ገብቶ የሚያጠፋ ኃይል ተደርጎ ነበር ሲነገር የነበረው።

በኢራናዊያን አእምሮ የተሳለው ግዙፉ ሄዝቦላህ በዚህ ፍጥነት ሸብርክ ይላል ያለ አልነበረም። ኢራናውያንን ያደናገጠውም ይኸው ሐቅ ነው። ለዓመታት የተሳለው ምሥል በሳምንት ፈረሰ።

በዘጠኝ ቀናት ውስጥ፣ እስራኤል የሄዝቦላህን መሪ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ኮማንደሮቹን አንድ በአንድ አጥፍታቸዋለች።

'ፔጀር' በተሰኘው የመስክ ስልክ እና ዎኪ ቶኪ በሁለት ቀናት ብቻ የሄዝቦላህ ቁልፍ ሰዎችን ጨምሮ 39 ዜጎችን እስራኤል ገድላለች።

በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቆስለዋል። ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ ከደረሰባቸው አንዱ በቤይሩት የኢራን አምባሳደር ናቸው።

ምናልባት እስራኤል ሄዝቦላህን ለማሽመድመድ የወሰደባት አጭር ጊዜ ሲታይ ሞሳድ እጅግ የተደራጀ፣ እጅግ የረቀቀ፣ የማያወላዳ መረጃን ለዓመታት ቃርሞ-አደራጅቶ እንደነበር የሚጠቁም ነው።

የእስራኤል ደኅንነት መሥሪያ ቤት

ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ዒላማ አድርጎ ሳይሳሳቱ መግደል ቀላል ተግባር አይደለም። የካበተ መረጃን ይፈልጋል።

ባለፉት ቀናት የታየው ስኬታማ የሚባል ጥቃት ምን ያህል የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ የሄዝቦላህ አመራሮች ላይ ሲያነፈንፍ እንደቆየ ማስረጃ ነው።

አሁን ኢራንን እያሳሰበ ያለው ነገር እስራኤል ተመሳሳይ መረጃን በኢራን ባለሥልጣናት ሰብስባ ከሆነስ የሚል ነው።

ይህ ፍርሃት ኢራኖች ያልተጠበቀ እርምጃ እንዲወስዱ አድርጓቸዋል።

ሮይተርስ ትናንት ቅዳሜ እንደዘገበው ኢራን ነገሩ አስጨንቋት መንፈሳዊ መሪዋን ወዳልታወቀ ቦታ ሸሽጋቸዋለች።

ባለፉት በርካታ ዓመታት የኢራን የኑክሊየርና የሚሳይል ሳይንቲስቶች በእስራኤል ተገድለዋል። ወሳኝ የሚባሉ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ቀጠናዎች በእስራኤል ቅኝት ይደረግባቸዋል።

ሞሳድ ቴህራን ቤቱ ሆኗል። የሐማሱ የፖለቲካ መሪ በቴህራን የእንግዳ ማሪፊያ ሳሉ ነው የተገደሉት። ይህ ነገር የኢራን ባለሥልጣናትን ክፉኛ እያስጨነቀ ይገኛል።

እአአ በ2012 የቀድሞ የኢራን ደኅንነት አገልግሎት ሚኒስትር አሊ ዩኔሲ እንዳሉት የእስራኤል ስለላ ተቋም የኢስላሚክ ሪፐብሊክን የመረጃ ሥርዓት ጥሶ ገብቷል። በዚህ ምክንያት ሁሉም የኢራን አመራሮች ለደኅንነታቸው መስጋት አለባቸው።

የኢራን አመራር አሁንም ቀውስ ውስጥ ገብቷል። የአብዮት ጠባቂው ኮማንደር ቤሩት ውስጥ መገደላቸው ነገሩን አባብሶታል።

እስካሁን ኢራን በይፋ እስራኤል ላይ አልዛተችም። ከዚህ ቀደም እስራኤል ደማስቆ ውስጥ ስምንት ከፍተኛ የኢራን አመራሮችን ስትገድል ኢራን በፍጥነት ወደ እስራኤል የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃት ሰንዝራ ነበር።

የአያቶላ አሊ ኻሜኒ ምላሽ

የኢራን ከፍተኛ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ ቅዳሜ ባደረጉት ንግግር የሄዝቦላህን ጥንካሬ አንስተዋል።

ሙስሊም አገራት እስራኤል ላይ እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

ኢራን በቀጥታ ሄዝቦላህን ለመደገፍ ፍላጎት አለማሰየቷ፣ ምናልባትም ሌሎችም የቀጠናው አጋሮች ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ሲገቡ በቀጥታ ከመደገፍ ይልቅ የራሷን ደኅንነት ቅድሚያ ልትሰጥ ትችላለች የሚል መልዕክት ያስተላለፈ ነው።

ከሁሉም በላይ ኢራናዊያን እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን እንዲያሳልፉ የሚያደርጋቸው የሞሳድ ኃያልነት ነው። የትኛውም የኢራን ባለሥልጣን ከእስራኤል ዕይታ ውጭ አይደለም። አያቶላህም ቢሆኑ።