ከ‘ፍሬንድስ’ ተዋናይ ማቲው ፔሪ ሞት ጋር በተያያዘ አንድ ሐኪም ጥፋተኛ መሆኑን አመነ

ዶ/ር ማርክ ቻቬዝ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከ‘ፍሬንድስ’ ተከታታይ ፊልም ተዋናይ ማቲው ፔሪ ሞት ጋር በተያያዘ ዶ/ር ማርክ ቻቬዝ የተባለው ሐኪም ጥፋተኛ መሆኑን አመነ።

ከመድኃኒት ዝውውር ጋር በተያያዘ ክስ የተመሠረተበት ሐኪሙ በማቲው ፔሪ ሞት ጥፋተኛ መሆኑን በሎስ አንጀለስ ፍርድ ቤት አምኗል።

ኬታሚን የተባለውን መድኃኒት ለማዘዋወር በመመሳጠር ነው ጥፋተኛ መሆኑን ያመነው።

የ54 ዓመቱ ዶክተር ኬታሚን የሚሸጥበት ክሊኒክ ያለው ሲሆን፣ ለማቲው መድኃኒቲን ለሰጠው ዶ/ር ሳልቫዶር ፕላስኒካ ኬታሚኑን የሸጠውም እሱ ነው ተብሏል።

ዶክተሩ ከማቲው ሞት ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ መሆናቸውን ካመኑ አምስት ሰዎች አንዱ ነው።

ተዋናዩ በካሊፎርያ በሚገኝ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ባለ መዋኛ ገንዳ ውስጥ ሞቶ ነበር የተገኘው።

አስከሬኑ ላይ በተደረገ ምርመራ ከፍተኛ መጠን ያለው ኬታሚን የተሰኘ መድኃኒት ተገኝቷል።

በደሙ ውስጥ የተገኘው ኬታሚን ለኅልፈት እንደዳረገውም ተገልጿል።

መድኃኒቱ ለድባቴ እና ለጭንቀት እንዲሁም ለአካላዊ ህመም ማስታገሻነት የሚውል ነው።

ዶ/ር ማርክ ለፍርድ ቤት እንደተናገረው፣ ኬታሚን ያገኘው ከቀድሞ ክሊኒኩ እና መድኃኒቱን በሐሰተኛ ማዘዣ በጅምላ ከሚያከፋፍሉ ሰዎች ነው።

ዐቃቤ ሕግ እንዳለው፣ የማቲው ፔሪ ተቀጣሪ የሆነው ኬኔት ኢዋማሳ ከሁለት ሐኪሞች ጋር በመሆን ለተዋናዩ 50 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ኬታሚን አቅርበዋል።

ሁለቱ ሐኪሞች በተለዋወጡት አጭር የጽሑፍ መልዕክት ተዋናዩ ምን ያህል ገንዘብ ለመድኃኒቱ እንደሚከፍል ተጻጽፈዋል።

“ይሄ ቂላቂል ምን ያህል ለመድኃኒቱ እንደሚከፍል ማየት እፈልጋለሁ” ይላል አንደኛው የጽሑፍ መልዕክት።

ጥፋተኛ መሆኑን ያመነው ሐኪም ለፖሊስ ምርመራ እገዛ በማድረግ ፍርዱ እንዲቀነስለት ተስማምቷል።

ቢዘህም እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስራት ሊፈረድበት ይችላል።

ዐቃቤ ሕግ “ጥፋተኛነቱን አምኖ እየተባበረን ነው” ሲል ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።

ሐኪሙ በዋስ የተለቀቀ ሲሆን፣ ፓስፖርቱን እና የሕክምና ፈቃዱን ለፖሊስ አስረክቧል።