ትራምፕ፤ ኩባ "ሳይረፍድ በፊት ስምምነት ላይ እንድትደርስ" አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የቬንዙዌላ አጋር የሆነችው ኩባ "ስምምነት ላይ እንድትደርስ" አሊያም የሚያጋጥማትን መዘዝ እንድትጋፈጥ አሳሰቡ።
ፕሬዝዳንቱ፤ ከቬንዙዌላ ወደ ኩባ ሲገባ የነበረው የነዳጅ እና የገንዘብ ፍሰት እንዲቆም እንደሚደረግም አስጠንቅቀዋል።
የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ሲያስጠነቅቁ ከቆዩ በኋላ በድንገተኛ ጥቃት እንዲያዙ ያደረጉት ዶናልድ ትራምፕ፤ ከዚህ ዘመቻ በኋላ ትኩረታቸውን ወደ ኩባ መልሰዋል።
የኩባ የረጅም ጊዜ ወዳጅ የሆነችው ቬንዙዌላ በቀን ወደ 35,000 በርሜል ዘይት ወደ ደሴቷ እንደምትልክ ይታመናል።
የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ አገራቸው "ያለ ጣልቃ ገብነት" ነዳጅ የማስመጣት መብቷ የተጠበቀ መሆኑን በመግለጽ ለትራምፕ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጥተዋል። የአገሪቱ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው "ማንም የምናደርገውን አይወስንልንም" ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር እየተከተለ ያለው፤ ማዕቀብ የተጣለባቸውን የቬንዙዌላ የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን የመያዝ አካሄድ፤ ኩባ ውስጥ ያለውን የነዳጅ እና የኤሌክትሪክ ቀውስ ማባባስ ጀምሯል።
የአሜሪካ መንግሥት ባለፈው አርብም ማዕቀብ የተጣለበትን የቬንዙዌላ ነዳጅ እያጓጓዘ ነው ያለውን አምስተኛ የነዳጅ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ስር አውሏል።
ትራምፕ እሁድ ዕለት 'ትሩዝ ሶሻል' በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ "ኩባ ለብዙ ዓመታት ከቬንዙዌላ በሚመጣ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ እና ገንዘብ ኖራለች። በምላሹም ኩባ ላለፉት ሁለት ለቬንዙዌላ አምባገነኖች 'የደህንነት አገልግሎት' ሰጥታለች፤ ነገር ግን ከእንግዲህ አይቀጥልም" ብለዋል።
አክለውም፤ "ከእንግዲህ ወደ ኩባ የሚሄድ ነዳጅም ሆነ ገንዘብ አይኖርም፤ ዜሮ! ጊዜው ሳይረፍድ ስምምነት እንዲያደርጉ አጥብቄ እመክራቸዋለሁ" በማለት አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ እንዲፈጸም ስለሚፈልጉት ስለ ስምምነት ዝርዝር ወይም ኩባ ሊገጥማት ስለሚችለው መዘዝ የገለጹት ነገር የለም።
የኩባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ ግን አገራቸው "ያለ አሜሪካ ጣልቃ ገብነት ወይም አንድ ወገን የግዴታ እርምጃዎች ተገዢነት" ከማንኛውም ፈቃደኛ ምርት ላኪ "ነዳጅ የማስገባት ፍጹም መብት" አላት ብለዋል።
ኩባ፤ ከአሜሪካ በተቃራኒ "በሌሎች አገራት በማስፈራራት ወይም በወታደራዊ እርምጃ ጫና ተጽእኖ" አታደርግም ሲሉም አክለዋል።
ትራምፕ፤ ከኩባ ጋር በተያየዘ አስተያየት ሲሰጡ አሜሪካ ውስጥ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እና በሌሎች ወንጀሎች ክስ በተመሰረተባቸው ማዱሮ እና ባለቤታቸው ሲሊያ ፍሎሬስን ለመያዝ የተወሰደውን እርምጃ አንስተዋል።
ኩባ ለዓመታት ለማዱሮ የግል ደህንነት ጥበቃ ስታደርግ ቆይታለች። የኩባ መንግሥት፤ አሜሪካ በቬንዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ ባካሄደቸው ዘመቻ 32 ዜጎቹ መገደላቸውን መገለጹ ይታወሳል።
ትራምፕ ስለዚህ ጉዳይ በሰጡት አስተያየት፤ "አብዛኞቹ እነዚህ ኩባውያን ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ጥቃት ሞተዋል፣ ቬንዙዌላም ለብዙ ዓመታት አግተው ከያዟት ወንበዴዎች እና ቀማኞች ጥበቃ አያስፈልጋትም" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮድሪጌዝ በበኩላቸው ኩባ "ለማንኛውም አገር ለቀረበችው የደህንነት አገልግሎት ምንም አይነት የገንዘብ ወይም የቁሳቁስ ካሳ ተቀብላ አታውቅም" ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ የኩባ መሪዎች እየተፈጠረ ያለው ሁኔታ ሊያሳስባቸው እንደሚገባ ባለፈው ሳምንት ጠቁመው ነበር። እርሳቸው በኩባ መንግስት ውስጥ ቢሆኑ ኖሮ "እንደሚጨነቁ" የተናገሩት ሩቢዮ፤ አገሪቱ መሪዎች "ከፍተኛ ችግር ውስጥ" ናቸው ብለዋል።















